በክልሉ ባለፉ 6 ወራት ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገለፀ
ሀዋሳ: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት አመቱ 6 ወራት ከመደበኛ እና ከማዘጋጃ ቤቶች ገቢ 14 ቢሊየን 080 ሚሊየን 652ሺህ 787 ብር መሰብሰብ መቻሉን ለክልሉ ምክር ቤት የፕላን መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርት ተመላከተ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የፕላን መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ገቢዎች ቢሮ የግማሽ ዓመት እቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምሽ ደመቀ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፥ ተቋሙ ከመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት በ2018 በጀት ዓመት ጠቅላላ ገቢ ብር ሰላሳ ቢሊዮን ስምንት መቶ ሚሊየን በመሰብሰብ የክልሉን በጀት 57 በመቶ በውስጥ ገቢ ለመሸፈን በየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በተገባው የግብ ስምምነት መሠረት በመስራታቸው በግማሽ አመቱ የዕቅዱን 91 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
ኦዲት መደረግ ከሚገባቸው ታክስ ከፋዮች መካከል 519 በስጋት ደረጃ በመለየት 352(68%) ታክስ ከፋዮች ኦዲት መደረጋቸውን ጠቁመው፥ በኦዲት ግኝት የተሰወረ የመንግሥት ገቢ 433 ሚሊየን 035ሺህ 316 ብር መገኘቱን ገልፀዋል።
በሁሉም ዞኖች የታክስ ስወራና ማጭበርበርን ለመቀነስ በታክስ ከፋዮች ደረሰኝ አሰጣጥ ላይ ጥናት መካሄዱን ያስረዱት የቢሮ ኃላፊዋ፥ በ9 ታክስ ከፋዮች ላይ የታክስ ኦፕሬሽን የተሰራ ሲሆን፥ በዎላይታ ዞን 5 እና በጎፋ ዞን 4 ታክስ ከፋዮች ላይ ኦፕሬሽን መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ የገቢ መሠረትን የማስፋት፣ የውዝፍ ዕዳ አመላለስ ፣ ለቀረቡ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ የመሰጠት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የፕላን መሠረተ ልማት እና ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ቢሮዉ ገቢን በመሰብሰብ ለክልሉ ልማት የሚዉል ሀብት ለመፍጠር ያከናወናቸዉ ተግባራትና ያስመዘገባቸዉ ዉጤቶች በከፍተኛ አድናቆት ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት፥ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በሀብት አሰባሰብ፣ በውዝፍ ዕዳ አመላመስ፣ ሊመዘበር የነበረ የመንግስትን ሀብት በማዳን እና በኦዲት ግኝት የተሰሩ ስራዎች አፈጻጸም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፥ ቢሮው ለቀረቡ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ያሳየው ቁርጠኝነት፥ ተገልጋዩ በተቋሙ ላይ ያለውን አመኔታ ያሳድጋል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ፕላን መሠረተ ልማት እና ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዕንቁ ዮሐንስ በበኩላቸው የገቢ አማራጮችን በመለየት ለአካባቢ ልማት የሚውል ገቢ በመሰብሰብ ቢሮዉ ላሳየው ከፍተኛ ዉጤት ቋሚ ኮሚቴው እውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት ከተሰበሰበዉ ዓመታዊ ገቢ በላይ በዘንድሮው የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት መሰብሰብ መቻሉ ክልላዊ ገቢ የመሰብሰብ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን አቶ እንቁ ተናግረዋል።
ቢሮው በታችኛው መዋቅር የሚታዩ የአፈፃፀም ጉድለቶችን በመለየት የድጋፍና ክትትል አግባቡን አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ ግማሽ ዓመትም የተሻለ አፈጻጸም እንደሚያስመዘግብ ያላቸዉን እምነት ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ

More Stories
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የህግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የግማሽ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ገመገመ
ዘመናዊ የግብርና ግብአት እና ቴክኖሎጂን በተገቢው በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ
በክልሉ አጠቃላይ የትምህርት ጥራት፣ ቁጥጥርና የደረጃ ምዘና የአሰራር ስርዓት ለውጥ እየታየበት መምጣቱ ተገለጸ