ጥረተ ብዙ እና ባለራዕዩ ወጣት – ወጣት ሻሚል መሃመድ
ትውልድና እድገቱ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ነው። ወጣት ሻሚል መሃመድ።
በወጣትነት የአፍላ እድሜ ብዙ ጊዜ ወጣቱ ካልተሳተፍኩ የሚልባቸው አሉታዊ ነገሮች እሱ ላይ ጊዜና ቦታ የላቸውም።
ምክንያቱ ደግሞ የሱ የዘወትር ፍላጎትና መሻት በያኔ የጨቅላ የእድሜ ክልል ሳለ ጀምሮ ራሱን ለሰዋዊ ስነምግባርና ለኪነጥበብ ማስገዛት ነበርና ነው።
እናም የወጣት ሻሚል ፅንሰ-ፍላጎት ገቢራዊ ለማድረግም ወደ ስፖርቱና ኪነ ጥበብ ስራዎች አዘንብሎ መስራት መጀመሩን በነበረን ቆይታ አጫውቶናል።
ለማርሻል አርትና ለኪነጥብብ የተለየ ቦታና ፍላጎት ነበረኝ፤ ዛሬም አለኝ ያለን ወጣቱ በተለይም ማርሻል አርት ጤናን ከመጠበቅ እና ስነምግባሩን ይበልጥ ከማነጽ ባለፈ በተወሰነ መልኩ የገቢ ምንጭ እንደሆነለትም ይናገራል።
በተጨማሪም በተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይም ተሳትፎ አድርጓል ወጣቱ።
በዋናነትም ማርሻል አርት ስፖርትን ከተቀላቀለ 10 ዓመታትን የተጠጋው ሻሚል በዚህ ቆይታው ታዲያ ራሱን በስፖርቱ ከማሳደግ ባለፈ ከስሩ ያለውን ትውልድ በአካል ብቃት የዳበረና በስነምግባር የታነፀ ዜጋ ሆኖ እንዲወጣ በመሻት በከተማው ያሉ ታዳጊዎችን የማርሻል አርት በማሰልጠን 1ኛ ዙር ተማሪዎቹን ማስመረቁንና አሁን ላይ እያሰለጠናቸው ያሉ ተማሪዎቹን ለ2ኛ ዙር በቅርቡ ለማስመረቅ ዝግጅት ላይ መሆኑንም ከጣቢያችን ጋር በነበረው ቆይታ ገልፆልናል።
ወጣት ሻሚል ታዲያ ምኑ ይሆን ለ”ወጣት የነብር ጣት” ብሂልን ማሳያ ያደረገው ትሉ ይሆናል።
እርግጥ ነው ይህን ለማለት ያስደፈረኝ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩኝም የተወሰኑትን ለአብነት ሳነሳ በየአካባቢያችን ብዙ ወጣቶች ጊዜያቸውን በእንቶ ፈንቶ ሲያሳልፉ ማየቱ መቼም የአደባባይ ሚስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል።
ይህ ወጣት ግን የማርሻል አርት ስፖርት ተማሪዎቹን ያሰለጥናል፤ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎና አላማን በመጠቀም በርካታ ስራዎችን ይሰራል። ያው ወጣት ነውና ይህን አፍላ እድሜውን በመጠቀም በኢኮኖሚው ዘርፍ ነገውን የተሻለ ለማድረግና ዛሬንም ኑሮውን ከወላጆች ጥገኝነት ለማላቀቅ ባለሶስት እግር ታክሲ ወይም ባጃጅ ያሸከረክራል።
በነገራችን ላይ ይህ የታታሪነትና በሁሉም ዘርፍ የመጣር ልምድ ከልጅነቱ የአህያ ጋሪ ከመስራት ጀምሮ የመጣ መሆኑን ነው ወጣት ሻሚል በነበረን ቆይታ ያጫወተን።
የዚህ ወጣት ፍላጎትና ጥረት መች በዚህ አበቃና። የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ያኔ በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ እያለ “የታይዋኑ ቫንዳም” የተሰኘ ፊልም ሰርቶ አስመርቋል ቢባል ፊልሙን የታደሙ ካልሆኑ በቀር ማንስ ያምናል።
በርግጥ ይሄ ብዙም ላይገርም ይችል ይሆናል። ለኔ ግን ግርምትን ያጫረብኝ ነገሩ ወዲህ ነው። ወጣቱ ፊልም ሰርቶ ማስመሩቁ ሳይሆን የፊልሙ ቀረፃና ኤዲቲንጉን ጨምሮ ሙሉ ስራውን የተጠናቀቀው በእጅ ስልክ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ራሱ ደራሲ፣ መሪ ተዋናይ፣ ኤዲተር፣ ፕሮዲውሰርና በከፊል ካሜራማን ሆኖ የተሳተፈበት ያውም በትውስት ስልክ ጭምር እንደሆነ ሲነግረን አጃኢብ አስኝቶናል።
በስድስት ተዋናይና ያለ ሴት ተሳትፎ የተሰራው የታይዋኑ ቫንዳም ፊልም ሲነሳ ብዙ አዝናኝና አስደንጋጭ ገጠመኞችም ይከተሉታል።
ቀረፃው የተካሄደው ተዋንያኑ ራሳቸው በመቀያየር ነበር።
ቀረፃው ሲካሄድ ታዲያ አንዳንዴም የእንሰሳት ድምፅ አብሮ ሊገባ ይችላል፤ እናም ፊልሙ ለዕይታ በበቃበት ወቅትም ምንአልባት የፍየል ድምፅ እንደ ሳውንድ ትራክ ይገባባቸው እንደነበር ያወሳል።
ሰፈር ላይ በተሰበሰበ ትንሽዬ እቁብ የተሰራ ይህ ፊልም ታዲያ ወጉ ላይቀርበት ባነር ሁሉ ተሰርቶለታል።
ለባነርና ለመግቢያ ትኬት 5 ሺህ 1 መቶ ብር ፈጅቶ ለእይታ የበቃው ፊልሙ በምረቃ ቀኑ ብቻ 16 ሺህ ብር ገቢ ማስገኘቱንም ነው ወጣት ሻሚል የነገረን።
ወጣቱ የነገ ህልሙ ሰፊ ነው። በመሆኑም በማርሻል አርት ስፖርቱም ይሁን በኪነጥበቡ ዘርፍ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መድረስን ውጥኑ ነው።
“ምንም እንኳን ከልጅነቴ ጀምሮ ክበባት አካባቢ ተሳትፎ አደርግ የነበረ ቢሆንም መልካምና ለወጣቱ ይሆናል ብዬ በማስባቸው ነገሮች ላይ በንቃትና በቅንነት እንቅስቃሴ እንዳደርግ ምክንያት የሆነኝ ማርሻል አርት ስፖርቱ ነው” የሚለው ወጣቱ ከዚህ ባለፈም ዘመኑ ባፈራቸው የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በመጠቀም አፍ በፈታበት በመስቃን ቤተ ጉራጌና በአማርኛ ቋንቋዎች ጠቃሚ መልዕክቶችን ያዘሉ ቀልዶች፣ ግጥሞችና የማስታወቂያ ስራዎችን ይሰራል።
በተለይም በፊልሙ ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለመምጣት ስክሪፕት አዘጋጅቶ እንደሚገኝና አጋዥ ካገኘ ለተመልካች ማድረስ እንደሚችል የገለፀው ወጣት ሻሚል ካሜራና መሰል ለሙያው አጋዥ የሆኑ መሳሪያዎችን ቢሟሉለት በዘርፉ ሌሎችንም የኪነ ጥበብ ስራዎች ለተደራሲያን፣ ለአድማጮችና ተመልካቾች የማበርከት አቅም እንዳለው ከቆይታችን ለመረዳት ችለናል።
“ጊዜና ወጣትነትን በአግባቡ አጣጥመው ከተጠቀሙበት የልጅነት ህልምን ለማሳካት ምንም አያግድም” የሚለው ጥረተ ብዙው እና ህልመ ሰፊው ወጣት ሻሚል በተለይም ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያን ለቁም ነገርና ለበጎ አላማ ማዋል ይጠበቅባቸዋል ብሏል።
ስለ ወጣት ሻሚል በቅርብ የሚያውቁት ወጣት መሃመድ አወልና ነስረላ መሃመድ በሰጡን አስተያየት የሱን ሁለገብ ታታሪነትና ስነ ምግባር ለሌሎች ወጣቶች አርዓያ የሚሆን እንደሆነ ገልጸዋል።
በሚያሳየው መልካም ስነ ምግባርና የስራ እንቅስቃሴ የወጣቱ ፈለግ እንዲከተሉ ምክንያት እንደሆናቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
አዘጋጅ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ሮድሪጎ ቤንታንኩር ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ታገደ
በቀቤና ልዩ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ 5ተኛ አመት ምስረታን ምክንያት በማድረግ ማህበረሰብ አቀፍ የማስ ስፖርት በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ጤናማና ንቁ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ