ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ከተስፋ ወደ ሚደነቅ ብርሃን መሸጋገሯን የሚያሳይ የአንድነት መገለጫ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑ ተገለጸ

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ከተስፋ ወደ ሚደነቅ ብርሃን መሸጋገሯን የሚያሳይ የአንድነት መገለጫ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዳዉሮ ዞን አስተዳደር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ፥ ኢትዮጵያ ከተስፋ ወደ ሚደነቅ ብርሃን መሸጋገሯን የሚያሳይ የአንድነት መገለጫ አገራዊ ፕሮጀክት ነው ሲል አስታወቀ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ መመረቁን ተከትሎ “በሕብረት ችለናል፣ የማይናወጽ አንድነት ፈጥረናል፣ ኢትዮጵያ ችላለች” በማለት ደማቅ የደስታ ሰላማዊ ሰልፍ በታርጫ ከተማ ተካሂዷል።

በዞኑ ታርጫ ከተማ በተደረገው ደማቅ የደስታ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንደገለፁት፥ የአንድነት ማሣያና ከዳር እስከ ዳር ያስተሳሰረ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁ በቀጣይም የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀከቶች ለማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሣያ ነው።

የተጀመረው ግድብ በውስጥ ባንዳዎችና በውጪ ጫና ሳይቋረጥ በቁርጠኛ የአመራር ሥርዓት ተገንብቶ መብቃት ላቅ ያለ ስኬት እንደሆነም ገልጸዋል።

በደስታ መግለጫ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙ ልዩ ልዩ የኅብረሰተብ ክፍሎች ሕዳሴ በደም የከበረ፣ በላብ የታጠረ ነው፣ በግደቡ የተባበረ ክንድ ለብልጽግናችን ይተጋል፣ ሕዳሴ ግድብ የኅብረታችን ማኅተም ነው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የመደመር ትእምርት ነው የሚሉ መሰል መልዕክቶች ተንጸባርቀውበታል፡፡

በሰልፉ በክልሉ የማኅበራዊ ክላስተር ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የዞን አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አባላት፣ በክብር ተሰናባች የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ VIP ፖሊስ አባላት ከተለያዩ ማኅበራዊ አደረጃጀት የተገኙ የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን