የቡና ግብይት እና ጥራት ቁጥጥር

በኢያሱ ታዴዎስ

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚነገርለት የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን መሰረት ያደረገ ነው። ሀገሪቱ በምታመርታቸው ምርቶች ከፍተኛ ገቢ ታገኝባቸዋለች። በተለይም ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች።

ከእነዚህ ምርቶች መካከል ደግሞ ቀዳሚው ቡና ነው። የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) እንዳስታወቀው፣ በአውሮፓዊያኑ 2023 አምስተኛዋ ከፍተኛ የቡና አምራች ሀገር ናት።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን እንዳስታወቀው ደግሞ፣ በ2015 በጀት ዓመት ሀገሪቱ በቡና ምርት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አግኝታለች። በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ 350 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት እየሰራች እንደሆነ ባለሥልጣኑ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ታዲያ በዚህን ያህል ደረጃ ለሀገሪቱ ጥቅም እያስገኘ ያለው የቡና ምርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ችግሮች እየተጋረጡበት እንደሆነ ባለሥልጣኑ ይፋ አድርጓል። ከችግሮቹ በዋነኛነት የሚነሳው የምርቱ ጥራት ነው። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በዘንድሮ በጀት ዓመት በትኩረት እየተሰራ ነው።

ለማንኛውም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ቡና በጥሬው፣ ወይም ደግሞ እሴት ተጨምሮበት በጥራትና በከፍተኛ መጠን እንዲሁም የቡና ግብይትን ዘመናዊነት፣ ህጋዊነትና ፍትሃዊነት በማሻሻል ዘርፉ ዕድገት እንዲኖረው ለማስቻል አዋጅ ማውጣቱ አስፈላጊ ሆኗል።

ከዚህም መነሻ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 28 /2009 ዓ.ም አዋጅ አውጥቷል። ይህም “የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1051/2009” ተብሎ ይጠራል።

የአዋጁ አንቀጽ 4፣ የቡና ጥራት ቁጥጥር አሰራርን የተመለከተ ሲሆን በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 (ሀ) ስር፣ በመጀመሪያ ደረጃ ወይም በሌሎች በተፈቀዱ የግብይት አማራጭ ቦታዎች የሚካሄደውን ቀይ እሸት እና የጀንፈል ቡና (ከነቆዳው ያለን ወይም ያልተፈለፈለ ቡና) ግብይት በጥራት ላይ ተመስርቶ መፈጸሙን ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርገው በክልል ሥልጣን የተሰጠው የቡና ጥራት ተቆጣጣሪ አካል ስለመሆኑ ይደነግጋል።

ከዚሁ በተጨማሪ በንኡስ አንቀጽ 1 (ለ) ስር ደግሞ ይኸው አካል ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ አስፈላጊውን ብቃት ያለው ዝግጅት ማድረጉን፣ በተፈቀደ የቴክኒክ አሰራር ቡና ስለመዘጋጀቱ፣ የቡና አያያዝና አከመቻቸት ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ይጠቅሳል።

በአንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ የቡና ጥራት ምርመራና ደረጃ ምደባ ማዕከል የደረሰ የአቅርቦት ቡና በአግባቡ ታሽጎ መድረሱን በማረጋገጥና ወካይ ናሙና በመውሰድ አስፈላጊውን የጥራት፣ እንዲሁም የጣዕም ምርመራ በማድረግ ደረጃ እንደሚመድብም ያትታል።

በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 3 ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የጥራት ደረጃ የተሰጠውንና አስፈላጊው መረጃ የተሟላለትን ቡና የግብይት ሂደቱ ሲጠናቀቅ ወደ የውጪ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች  በአግባቡ አሽጎ እንደሚሸኝና መድረሱንም ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ደንግጓል።

በተጨማሪም ወደ ውጪ ገበያ የሚላከውን ቡና እያንዳንዱን የጥራትና የዝግጅት ሂደት በመከታተል አሽጎ ወደ ወደብ መሸኘቱን፣ መድረሱን መከታተሉን፣ እንዲሁም የመቆጣጠሩንም ስራ ባለሥልጣኑ እንደሚሰራም በአዋጁ ተጠቅሷል።

ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውልን ቡና በተመለከተ ደግሞ የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላቱን በማረጋገጥ የደረጃ ምደባ እና የምስክር ወረቀት በመስጠት  ወደ ተጠቃሚ አካባቢዎች የሚሸኘውና መድረሱን የመቆጣጠር ወይም የመከታተል ኃላፊነት ያለው ባለሥልጣኑ፣ አሊያም በባለሥልጣኑ የተፈቀደለት ሌላ የምርመራ ማዕከል መሆኑን የሚገልጸው አንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ 6 ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ ባለሥልጣኑ ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ በተዘጋጀ ቡና በተሰጠ የጥራት፣ ምርመራና የደረጃ ምደባ ዙሪያ በሚቀርቡ ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥም ተደንግጓል።

የአዋጁ አንቀጽ 8 የቡና አምራች ግዴታዎች ዙሪያ ያትታል። ይኸው አንቀጽ ከ1 እስከ 6 ድረስ ከአርሶ አደር በስተቀር ከሚመለከተው የመንግስት አካል የተሰጠ የጸና የብቃት ማረጋገጫ እና ንግድ ፈቃድ የመያዝ፣ ያመረተውን ቡና በሀገር ውስጥ የሚገበያይ ከሆነ ለቡና ጥራት ምርመራና ደረጃ ምደባ ማዕከል አቅርቦ ደረጃ የማሰጠት ግዴታዎች ቡና አምራቾች እንዳሏቸው ተደንግጓል።

በተጨማሪም ያመረቷቸውን ወይም በልማትና ግብይት ትስስር የገዟቸውን ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም በሌላ ህጋዊ የግብይት አማራጭ የምርት ዘመኑ ሳያልፍ የመሸጥ፣ አሊያም ወደ ውጭ አዘጋጅቶ የመላክ ግዴታዎች እንዳለባቸው ተጠቅሷል።

ሌላው የቡና አቅራቢዎችን የተመለከተ ግዴታ ነው። አንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ 1፣ ቡና አቅራቢ ቀይ እሸት ወይም ጀንፈል ቡና በተፈቀደለት አካባቢ ብቻ የመግዛት፣ የማዘጋጀት፣ የማጓጓዝ፣ የበቀለበትን አካባቢ ቡና ባህሪና ስያሜ የመጠበቅ፣ ከሌላ ስነምህዳር ዓይነት ቡና ጋር ሳይቀይጥ ወይም ከማንኛውም ሌሎች ባዕድ ነገሮች ሳይደባለቅ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ያትታል።

የሚያዘጋጀውን የአቅርቦት ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም በሌላ ህጋዊ የግብይት አማራጭ የምርት ዘመኑ ሳያልፍ የመሸጥ ወይም ወደ ውጭ አዘጋጅቶ የመላክ ግዴታ እንዳለበትም አትቷል።

አንቀጽ 10 ደግሞ በዋነኛነት የቡና ላኪ ግዴታዎች ዙሪያ የሚደነግግ ሲሆን ጥቅል ግዴታዎቹ ማንኛውም ቡና ላኪ ከሚመለከተው የመንግስት አካል የተሰጠ የጸና የብቃት ማረጋገጫ እና ፈቃድ የመያዝ፣ እንዲሁም ውጪ የሚልከውን ቡና የሀገሪቱን የጥራት ደረጃ መስፈርት ጠብቆ የማዘጋጀት ግዴታ እንዳለበት ያመለክታል።

አዋጁ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ቡና ጋር በተገናኘ እንዲሁ አንቀጽ 11 እና አንቀጽ 12 ላይ አስፍሮ ይገኛል። በእነዚሁ አንቀጾች የሀገር ውስጥ ፍጆታ ጅምላ እና ችርቻሮ ነጋዴዎች ከሚመለከተው የመንግስት አካል የተሰጠ የጸና የብቃት ማረጋገጫ እና የንግድ ፈቃድ የመያዝ፣ እንዲሁም የውጪ ገበያ ቡና አለመግዛት ወይም አለማጓጓዝ፣ አሊያም አለመሸጥ ግዴታ እንደተጣለባቸው ደንግጓል።

ከእነዚህ ግዴታዎች ባሻገር የተከለከሉ ተግባራት እና የሚያስከትሉት ቅጣቶች ተደንግገው ይገኛሉ በአዋጁ። አንቀጽ 19 ንኡስ አንቀጽ 1:-

“ማንኛውም ቡና የሚያዘጋጅ አካል ቡና ሲያዘጋጅ በባለሥልጣኑ ወይም በክልል አግባብ ያለው አካል ከተፈቀደ የቴክኒክ አሰራር ውጭ በማዘጋጀት በቡናው ጥራት ላይ እና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፣ ማዘጋጃ ኢንዱስትሪው መታሸጉና ምርቱ ለግብይት እንዳይቀርብ መደረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአንድ ዓመት በሚያንስና ከሶስት ዓመት በማይበልጥ እስራት፣ እንዲሁም ከብር 20 ሺህ እስከ አርባ ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል።” ይላል።

አንቀጽ 19 ንኡስ አንቀጽ 2 ደግሞ ማንኛውም በንግድ ግብይት የተሰማራ ሰው ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም ባለሥልጣኑ ከሚወስናቸው ሌሎች የግብይት አማራጮችና ስፍራዎች ሲሸጥም ሆነ ሲገዛ የተገኘ እንደሆነ ቡናው መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሶስት ዓመት በማይበልጥ እስራት፣ እንዲሁም ከብር ሀያ ሺህ እስከ አርባ ሺህ በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ አስቀምጧል።

በዚሁ አንቀጽ ስር ሌሎች ክልከላዎችና ቅጣቶችም ተደንግገው ይገኛሉ። በአጠቃላይ አዋጁ በመሰረታዊነት የቡና ምርት አመራረት፣ ጥራት፣ ቁጥጥር፣ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች፣ ግዴታዎች፣ ክልከላዎች እና ቅጣቶች ዙሪያ ደንግጓል። ይህም ዘርፉ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለሀገር ትልቅ አበርክቶ እንዲኖረው አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ነው።