ጽዱ ከተማ ለመፍጠር የህብረተሰብ ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
ሀዋሳ፣ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ኑ ለኢትዮጵያ ሰላም እንሩጥ” በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደው የኬሮድ 5ኛ ዙር የጎዳና ላይ ሩጫ ከተማዋን ጽዱ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጽዳት ዘመቻ በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።
የወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ጽዱ ከተሞችን ለመፍጠር የህብረተሰቡን ያሳተፈ ሳምንታዊ የጽዳት ስራ እያከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
በከተማው የፅዳት ዘመቻ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅና ነፋሻማና አረንጓዴ አካባቢ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አቶ ሙራድ አስታውቀዋል።
አክለውም አካባቢን ከብክለት መጠበቅ በከተማው የሁል ጊዜ ተግባር ማድረግ እንደሚገባ የገለፁት ከንቲባው ተቋማት ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ቁጥጥር የማድረግና የከተማዋን ገፅታ የሚያበላሹ ተግባራት ላይ ሚናውን መወጣት እንደለበት ገልጸዋል።
የወልቂጤ ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ሳቢና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ በተለይም በከተማው ሁሉን ያሳተፈ የአካባቢ የጻዳት ስራ መስራት፤ ቆሻሻን የሚጸየፍ ማህበረሰብ መፍጠር እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኮማንደር አትሌት ሰለሞን ባረጋ በበኩሉ የወልቂጤ ከተማ ከጊዜ ወደጊዜ ለውጥ እያሳየች እንደሆነ ገልጾ ለኬሮድ 5ኛ ዙር የጎዳና ላይ ሩጫ ለመሳተፍ ወደ ወልቂጤ በመምጣቱ ደስተኛ እንደሆነ ተናግሯል።
በተለይም ለነገ ሩጫ ከተማዋ ፅዱ ለማድረግ እየተከናወነ የሚገኘው የፅዳት ስራ የሚበረታታ መሆኑን የተናገረው ኮማንደር አትሌት ሰለሞን ባረጋ ይህ ተግባር በሌላም ጊዜ መጠናከር እንዳለበት ጠቁሟል።
በዛሬው ዕለት በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ላይ በከተማው የሚገኙ አመራሮች ፣ ታዋቂ አትሌቶች ፣የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ፣የተለያዩ ክበባትና ወጣቶች እንዲሁም ሌሎችም የከተማው ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂደዋል።
ዘጋቢ፦ ደጋጋ ሂሳቦ

More Stories
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ
በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
በሌማት ትሩፋት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ