“በህብረት ችለናል”
በደረጀ ጥላሁን
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዘመናት ሲቆጭ ለዘለቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ተስፋን የሰጠ ነው፡፡ ይህ የህዝብ ሃብት የዘመናት ምኞታቸውን እንደሚያሳካ የተማመኑ ዜጎች ከድህነት አረንቋ የመውጣት ጥረት ውጤት በመሆኑ÷ ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ለስኬቱ ተረባርበዋል። በዚህም ምክንያት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁሉም የሀገራችን ህዝብ በስስት የሚመለከተው ነው።
ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን ያሳረፉበት የማንነታቸው መገለጫ የሆነው “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” የሀገራችን ህዳሴ ማብሰሪያ፣ ብሎም የማንነታችን አሻራ መገለጫ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ የማኖር ሥነ- ሥርዓትን ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተንጸባረቀው ስሜትም ከፍተኛ ነበር፡፡
ቀስቃሽ ሳያስፈልገው፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጾታና ዕድሜ ሳይገድበው የምንጊዜም የማንነቱ መገለጫ በሆነው ሰንደቅ ዓላማው ደምቆ ወደየአደባባዩ በመትመም ያለውን ቁርጠኝነት እና የ“ይቻላል” ምላሹን በመስጠት ታሪክ የማይዘነጋው ተግባር አከናውኗል፡፡
የግድቡ ግንባታ ለዘመናት ዓባይን የመገደብ አይሞከሬነት አስተሳሰብ ያከተመበትና የ“ይቻላል” አስተሳሰብ ለውጥ የተፈጠረበት ነው፡፡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ድርሻውን ለመወጣት ቃል የገባበት እና ምላሹን የሰጠበት ፕሮጀክት መሆኑ እንዲሁም በዜጎች ገንዘብና ባለቤትነት የሚገነባ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ስራው በተፈለገው ሁኔታና ፍጥነት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የግድቡ ግንባታ ሥራ የተለያዩ ምዕራፎችን የሚያካትትና ደረጃ በደረጃ የሚከናወን መሆኑን የዘርፉ ሙያተኞች ሲያስረዱ ቆይተዋል፡፡
ከሰሞኑ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ሃሳብ ሲከበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በአከባበሩ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የ13 ዓመታትን ጉዞ የሚያሳይ የስዕልና የፎቶ ዐውደ-ርዕይ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የተዘጋጀ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስታወሻ ቴምብር መመረቁን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እምቅ ሀብትን አውጥቶ ለብልጽግና ማዋል የመንግስት ቁልፍ አጀንዳ መሆኑንና የዚህ ማሳያ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ላለፉት 13 ዓመታት በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም ልዩነት በጋራ በመተባበር በተደረገው ጥረት ራሳችን በራሳችን የማልማት ጥበባችን ወደ ራሳችን መልሰናል ነው ያሉት፡፡ ልማታችንን የማይፈልጉ ሀይሎች መሰረተ ቢስ ምክንያቶችን በማንሳት የግድቡን ሥራ ለማደናቀፍ ቢታገሉም፣ በአለም መድረኮች ቢከሱም ሊያስቆሙን ግን ባለመቻላቸው አለም አቀፍ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
በዲፕሎማሲው ሂደት ፈተናዎችን ማለፍ የተቻለው እንደ አድዋ ዘመቻ በህብረ ብሔራዊ አንድነት በመነሳታችን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም የሚገጥሙንን የሰላምና ከድህነት የመውጣት ትልቅ ፈተናዎች በህብረ ብሔራዊ አንድነት ከተነሳን የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የምንደርስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግሉ ዘርፍ የቦንድ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌታሁን ታገሰ ለኢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን መሰረት ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድባችን በስኬት መቋጨት “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” የሚለውን ቃላችንን በመጠበቅ ዛሬም ከትናንቱ በበለጠ ሁኔታ በግድቡ ዙሪያ ተሰባስበን የህዳሴያችንን ጥርጊያ መንገድ ይበልጥ መክፈት ይኖርብናል ብለዋል። በተለይም የሀገራችንን ዕድገት የማይሹ የውስጥም ይሁን የውጭ ሃይሎችን ውዥንብር ወደ ጎን በማለት በተግባራዊው የግድቡ ሥራ ላይ መረባረብን ለነገ መተው የለብንም ብለዋል።
ይህም በጉጉት ሲጠብቁት ለነበሩት ኢትዮጵያውያን ድጋፋችን ውጤት አምጥቷል፤ ህልማችን ተሳክቷል፤ “ዓባይ ግንድ ይዞ ይዞሯል” ሳይሆን “ኃይል ይዞ ይዞራል“ የሚባልበት ምዕራፍ መሆኑን ነው የገለጹት።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ ግድብ ብቻ ሳይሆን የነገ ልማት ማስፈንጠሪያ መሻገርያ ድልድይ፤ የዜጎች በራስ የመስራት አቅም ማስረጃ ነው ያሉት ኢንጂነር ጌታሁን፣ የአንድነት ማሳያ አስታራቂ ሽማግሌያችንም ጭምር ነው ሲሉ ገልፀውታል።
“ግብፅና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ አሉታዊ ሃሳቦችን ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን በግድቡ ትሩፋት በትልቁ ተጠቃሚዎችም እነሱ ናቸው። ሱዳን በየዓመቱ ለጎርፉ ደለል ጠረጋ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ የሱዳን የደለል ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል” ሲሉም ኢንጂነር ጌታሁን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን አቅም፣ ጉልበት እና የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት ለነገ ትውልድ እንደ ህዳሴ ግድብ ዓይነት ተሻጋሪ ቅርሶችን በመተጋገዝ መስራት አሁንም ሊቀጥል እንደሚገባም ኢንጂነር ጌታሁን ገልጸዋል።
በተለይም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ የጠየቁት ኢንጂነር ጌታሁን፤ “በተዘዋወርንባቸው ሀገራት ያለው ኢትዮጵያዊ ስሜት የሚያስቀና ነው” በማለት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዋጣታቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።
በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባላሀብቶችም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ እስኪገባ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ኢንጂነር ጌታሁን ታገሰ አንስተዋል።
የዓባይ ወንዝ የዛሬ 13 ዓመት ነበር ፊቱን ወደ ህዝቡ ያዞረው። አንዳንዶች “ኢትዮጵያዊያን ይህንን ትልቅ ወንዝ ሊገድቡት አይችሉም፤ አቅም የላቸውም” ቢሉም “አይችሉም፤ አይሳካም” የተባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዛሬ ላይ ከ95 በመቶ በላይ ስራው ተጠናቆ ሀገሬውን በብርሃን ሊያደምቅ ትንሽ ቀርቶታል።
ግብጽና አጋሮቿ ይህ ግድብ እውን እንዳይሆን በብዙ ጥረው የነበረ ቢሆንም የተጋረጡበትን ፈተናዎች ተሻግሮ ወደ መጠናቀቅ መቅረቡ ከምንም በላይ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ መሠረተ ድንጋይ ከማኖር ጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ የሰጠው ምላሽ ለስኬታማነቱ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በመሆኑም ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት እየተካሄደ ያለው ሁለንተናዊ ጥረትና መላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እያሳየው የሚገኘው ቁርጠኝነትና ጽናት የተሞላበት ተግባር መቀጠል እንዳለበት ሁላችንንም ያስማማል፡፡
የግድቡን ፋይዳ የሚገነዘብ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ አርቆ የሚመለከት ዜጋ ሁሉ ይህን ሀገራዊ ጥንካሬ በማስቀጠል ለፍፃሜ ጫፍ የደረሰውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው