የሞት ነገር

የሞት ነገር

በይበልጣል ጫኔ

ሠላም ተወዳጆች÷ እንዴት ሰነበታችሁ?÷ ሳምንታችሁ እንዴት አለፈ? …

እኔ የምለው ስለሞት አስባችሁ ታውቃላችሁ?÷ ሞት ጨካኝ መዳፉን ሲዘረጋ (ጨካኝ መሆኑን ግን ማን አየው?)÷ ደርሶ ያዝኩህ ወሰድኩህ ሲል? ሟች ከመሞቱ በፊት ምን የሚሰማው ይመስላችኋል?

የሆነ ጊዜ አንድ ቀለም የዘለቀው ሰው÷ አዛውንቶች ክበብ ተገኘ÷ አሉ። አዛውንቶቹ በአብዛኛው መኖር ደክሞዋቸዋል። እዚያ ክበብ የሚሰባሰቡት ድካማቸውን ለመርሳት ነው። ድራፍታቸውን እየተጎነጩ÷ ዳማ ይጫወታሉ። ባለ ካርታዎችም÷ ባለ ከረንቡላዎችም በዚያ አሉ።

የተቀሩት ደግሞ ከትዝታ ማህደራቸው እየመዘዙ ትላንታቸውን ያወራሉ። ልትጠልቅ ያለች ጀንበር÷ የመሰለ ሳቅ ፊታቸው ላይ ይዘራል። በዚህ መካከል ነው እንግዲህ÷ ሰውዬው አዛውንቶቹ መካከል የተገኘው።

ከአንድ ጥግ ቁጭ ብሎ ጥቂት ሲያስተውላቸው ቆየ። ቆየ ቆየና አጨበጨበ። ሲያጨበጭብ አስተናጋጅ መጣ። እሱ የመጣው አስተናጋጅ በጥቅሻ ከሚጠራበት ሰፈር ነው። ያጨበጨበው አዛውንቶቹ እንዲሰሙት ነበር። ቀድሞ የሰማው ግን አስተናጋጁ ነበር፦

“ምን ልታዘዝ?” አለ÷ በትህትና አንገቱን ዝቅ አድርጎ። አስተናጋጁ እርጥብ እጆቹን በአዳፋ ልብሱ ላይ እየጠረገ ቀና አለ። ሰውዬው ዝም ብሎ ያየዋል እንጂ ምንም አላዘዘውም። አስተናጋጁ ቢቸግረው፦

“ሠላም ነው ጋሼ?!” አለው።

ሰውዬው ከሄደበት ተመልሶ÷ አስተናጋጁን ያለምንም ትዕዛዝ አሰናበተው። ወደ አዛውንቶቹ ጠጋ ብሎ፦

“እንደምን ዋላችሁ አባቶቼ?” ብሎ ዙሪያ ገባውን ቃኘው። ጥቂቶች፦

“እግዚአብሔር ይመስገን” አሉት።

ጥናት እያጠና እንደሆነ÷ በአንድ ጉዳይ ላይ የነሱን ምክር ፈልጎ እንደመጣና ፈቃደኛነታቸውን እየጠየቀ እንደሆነ ነገራቸው።

ሰምተውታል ግን የሰሙት አይመስሉም። የየእጃቸውንና የየአፋቸውን ጨዋታ ቀጥለዋል። ከመካከላቸው አንደኛው፦

“ጥናት አጠናለሁ ነው ያልከው?÷ ለመሆኑ ስለምንድነው የምታጠናው?” የሚል ጥያቄ ሰነዘሩ።

“ስለ ሞት” አለ÷ ቀልጠፍ ብሎ። ሊያብራራ ሲል ተቀደመ።

“እኛ’ኮ አርጅተን እንጂ ሞተን አናውቅም። ስለሞት ለማጥናት እኛ ጋ የመጣኸው ለምን ድ’ነው?” ብለው÷ በግልምጫ አንስተው አፈረጡት።

ግልምጫውን ተከትሎ የአዛውንቶቹ ሳቅ ፈነዳ። አጥኚው ግራ ተጋባ።

አንዳንዴ ጀማሪ መሆን ክፉ ነው። ጉዳያችሁን ማን ጋ ይዛችሁ መሄድ እንዳለባችሁ ይቸግራችኋል። ወይም ደግሞ÷ ትክክለኛው ቦታ ትሄዱና÷ ማንን እና እንዴት መጠየቅ እንዳለባችሁ ካልተረዳችሁ÷ ጉዳያችሁን ውኃ እንደበላው ቁጠሩት።

እነዚህ አዛውንቶች በህይወት ዘመናቸው ብዙ አይተዋል። አንዳንዶቹ ጫፍ ደርሰው÷ ከሞት ጋር ሰላም ተባብለው ተመልሰዋል። ሌሎቹ ደግሞ ወዳጆቻቸውን አሟሙተዋል። አጥበው ገንዘው ቀብረዋል። ሞት ለእነሱ እንግዳ ነገር አይደለም።

አጥኚው የቦታ ምርጫው ትክክል ነው። እንዴት ማውራት እንዳለበት ግን አልገባውም። ለዚያ ነው የተሳቀበት።

በሌላ ቀን እዚያው ክበብ የተገኘው አጥኚ÷ አዛውንቶቹ ሰብሰብ ያሉበት ቦታ መርጦ ተቀላቀላቸው። አስተናጋጁን ጮክ ብሎ ተጣርቶ፦

“ለሁሉም አባቶች የያዙትን መጠጥ ድገማቸው። የዛሬ ወጪያቸው በኔ ነው” አለ።

ፈንጠር ፈንጠር ብለው የተቀመጡት አባቶችም÷ ጅምራቸውን ይዘው ቀረብ ቀረብ አሉ።

በነገራችን ላይ ይኼ የብዙዎቻችን ስህተት ነው። በአካል እንኳን የማንግባባበትን ጉዳይ በስልክ እንጀምራለን። ተቃቅፈን ብናወራው የሚቀለውን÷ ተራርቀን እንጨቃጨቅበታለን። እንደ ሰንበሌጥ ዝቅ ብንል በሰላም በሚያልፈው ጉዳይ÷ እንደ ጅብራ ተገትረን እንሰባበርበታለን። አልጋ ላይ የጀመርነውን ወሬ መሬት ላይ ካልጨረስን ብለን÷ መከራችንን እናያለን።

እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ችግር። በአጥኚው እይታ ሞት መልከ ጥፉ እና ጨካኝ ነው። እንደራሱ ሁሉ ሁሉም ሰው ሞትን ይጠላዋል ብሎ ያስባል። በዚህ እሳቤ ውስጥ ሆኖ÷ ከአዛውንቶቹ ጋር ማውራት ጀመረ፦

“ሞትን እንዴት ታዩታላችሁ?”

“እኔ ስንት ዘመዶቼን ሸኝቼ ብቻዬን ቀርቻለሁ። ሞት ይናፍቀኛል። አሁን ቢመጣ እጁን ጨብጬ እቀበለዋለሁ” አሉት÷ ቀዳሚው አዛውንት። ሁለተኛው ቀጠሉ፦

“ሞትን የመሰለ ፍትሃዊ ዳኛ አይገኝም። ስንቱን ጥጋበኛ በመቃብር ያስተኛው እሱ አይደል?÷ ትንሽ የሚቆጨኝ እዛ ካርታ ጨዋታ ስለሌለ እንጂ÷ እዚህ ምን ይቀርብኛል?” ብለው ፈገግ አሰኙት።

እንደ አጋፋሪ እንደሻው ሞትን የሚፈሩት ሽማግሌ÷ ወሬው አልጥም ስላላቸው ሹልክ ብለው ወደ ቤታቸው ሄዱ።

በሌላ ጊዜ ደግሞ÷ አጥኚው ሌላ ቡድን ሰበሰበ። እዚህ ቡድን ውስጥ ሀኪም፣ የዕድር ሰብሳቢ፣ ጡሩንባ ነፊ፣ መቃብር ቆፋሪ እና የሬሳ ሳጥን ሻጭ ይገኙበታል።

ሀኪሙ ሞት ተፈጥሯዊ እንደሆነ ቢያምንም÷ ከሰዎች ህመም እንጂ ከሞታቸው ትርፍ እንደሌለው ያውቃል። ስለዚህ ጥረቱ ሁሉ እንደምንም እየጠጋገነ÷ ሰዎች በህይወት እንዲቆዩ ማድረግ ነው። የሚገርመው ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ÷ ታማሚው እንደማይተርፍ እያወቁ እንኳን÷ “ይኼን ግዙለት÷ ይኼን አምጡለት” ማለት አለማቆማቸው ነው።

እዚህ ጋ እንቅፋት ጥፍሩን ገንጥሎት እየደማ የሄደን ሰው÷ ሽንትና ሰገራ የሚመረምሩ ሀኪሞች መኖራቸውንም ማስታወስ ይገባል። ሞያቸውን አክብረው ለህሊናቸው የሚሰሩ መኖራቸውም ሳይዘነጋ።

የዕድር ዳኛውም ቢሆኑ÷ አባሎቻቸው ሲሞቱ የዕድራቸው ወጪ ያሳስባቸዋል። ስለዚህ የሰዎችን ሞት ሲሰሙ በተለየ መንገድ ሃዘን ይሰማቸዋል። እነሱ ጋ ደግሞ የሚገርመው ምን መሰላችሁ? …

ለዕድሩ የ2ሺህ ብር ዕቃ ለመግዛት÷ 3ሺህ ብር አበል ሲበሉ አያንቃቸውም። ወይም ደግሞ አሮጌ ዕቃ ለመሸጥ የተቋቋመው ኮሚቴ 700 ብር አስገብቶ÷ 1ሺህ 700 ብር ወጪ ሲያስደርግ ቅር አይለውም።

ምንም አይነት ማስመሰል የማያውቃቸው÷ ቀሪዎቹ ተሳታፊዎች ናቸው። የዕድሩ ጡሩንባ ነፊ፣ መቃብር ቆፋሪ እና የሬሳ ሳጥን ሻጭ÷ እንጀራቸው የተመሰረተው በሰዎች መሞት ላይ ነው። ወደ ፈጣሪያቸው ቀና ብለው፦

“የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ” ሲሉ÷

“አንዱን ምስኪን ድፋውና አፈር እናልብሰው” እያሉ እንደሆነ÷ ለእነሱም ትዝ የሚላቸው አይመስለኝም።

የሆነው ሆነና÷ “አብዛኛው ሰው ሞትን የሚያየው÷ ከሚያስገኝለት ጥቅም አንፃር ነው” ይላል የጥናቱ ግኝት። ክፉኛ የሚያዝኑ ሰዎችስ? ከዚህ አንፃር እንዴት ይታያሉ? የሚል ቢኖር፦

“የእነሱም ክፉኛ ማዘን ከሚቀርባቸው ጥቅም አንፃር የሚታይ ይሆናል” ማለቱ አይቀሬ ነው።

ጥናት ሲባል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ?፦

በአንድ ወቅት÷ ለብርድ ወቅት የሚሆን ሞቃት ፎጣ የሚያመርት ድርጅት÷ የገበያ ጥናት ሊያደርግ አሰበ አሉ። አሰበ እና አጥኚዎችን አዋቀረ።

የጥናት ቡድኑ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዶ አንዲት ቀበሌ ላይ አረፈ። ቀበሌዋ ሲበዛ ብርዳማ ነበረች። ሁኔታውን ተዟዙረው አጠኑ። ለናሙና የያዙትን ፎጣም ለአካባቢው ሰዎች ሰጡ። የሰዎቹ ምላሽ ፈጣን እና አስደሳች ነበር።

አጥኚዎቹ ወደ ሌላ ቀበሌዎች መሄድ አልፈለጉም። ትርፉ ድካም ነው። በዚያ ላይ አበላቸውን ለምን ያባክናሉ፦

“አባዛኞቹ ቀበሌዎች ብርዳማ ናቸው። አካባቢው ለምርታችን ሽያጭ ሁነኛ ቦታ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ተመለሱ።

በጥናቱ ግኝት መሰረት÷ ምርቱ ተጫነ። ከዚያ ከብርዳሙ ቀበሌ መጠነኛ ሽያጭ ውጪ÷ ምንም አይነት ገበያ ሳያገኙ ቀሩ። ለምን ቢሉ?÷ ከዚያች ብርዳማ ቀበሌ ውጪ÷ ሌላው አካባቢ ጨርቅ የሚያስጥል ሙቀት ያለበት ነው።

ለዚህ ነው÷ አስር ሰው እያነጋገሩ በህዝብ ስም የሚያወጧቸው ጥናቶች የማይመቹኝ። ከላይ ስለሞት የተጠቀሰው ጥናትም÷ ማንን እንደሚወክል እንጃ።