በመንግስትና ህብረተሰብ ትብብር በሚሰሩ ሥራዎች መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች እየተፈቱ መሆኑን በጉራጌ ዞን የአገና ከተማ አስተዳደር ገለጸ
በከተማ አስተዳደሩ በመንግስትና ህብረተሰብ ትብብር ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፤ በከተማው በመንግስትና ህብረተሰብ ትብብር የተሰሩ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የመብራት ዝርጋታና የዲች ከፈታ ስራዎች የህብረተሰቡ የእለት ተዕለት እንቅሰቃሴውና ማህበራዊ መስተጋብሩ እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።
እንደ መንግስት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ የህብረተሰቡን አቅም ይበልጥ በማስተባበር መስራት ይገባል ብለዋል።
በመንግስት የተጀመሩ የገጠርና የከተማ ኮሪደር ልማቶች የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ የሚቀይሩና የከተሞች እድገት የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጀፎረን የመጠበቅ፣ የማልማትና የመንከባከብ ስራውን ማጠናከር ይኖርበታል ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
የአገና ከተማ ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ በበኩላቸው፤ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ ሳቢና ውብ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህን ከተሞች የማዘመን፣ የማስዋብና የማሳደግ ተግባር እውን ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ከንቲባው ገለጻ ከፌደራል እስከ ከተማ አስተዳደሩ የመንግስት መዋቅር እና በህብረተሰብ ተሳትፎ እስካሁን ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የዲች ከፈታ፣ የመብራት ዝርጋታና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች መገንባት ተችሏል።
ወ/ሮ ሰፍወት ሸሪፍና አቶ ይታገሱ ሳህሌ የአገና ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ በከተማው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ስራዎች ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በከተማው ለሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተደራሽነት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረው ባለሀብቶችም በከተማው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የከተማውን እድገት በማፋጠኑ ሂደት የድርሻቸውን እንዲወጡ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በቀቤና ልዩ ወረዳ በግብርና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ
የሣውላ ከተማ ምክር ቤት የከተማውን የ2018 ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀት ከ594 ሚሊዮን በላይ ብር በሙሉ ድምጽ አጸደቀ
በጌዴኦ ዞን የ2017 በጀት ዓመት በሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕይዝ ዘርፍ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ዓመት መሆኑን የዞኑ ሥራና ክህሎት መምሪያ ገለጸ