እጅ አልባው ሰዓሊ

እጅ አልባው ሰዓሊ

በይበልጣል ጫኔ

ሰዓሊ እና መምህር ናቸው። በተጨማሪም ግጥም ይፅፋሉ። በልጅነታቸው እጆቻቸውን ባሳጣቸው አደጋ ምክንያት ለሀገር እና ለትውልድ መትረፋቸው ቀርቶ “ሰው” ይሆናሉ ያላቸው አልነበረም። ኧረ እንደውም “ቢሞት ይሻለዋል” ያሏቸውም ነበሩ። እኚህ ሰው ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ናቸው።

ሰዓሊ ወርቁ ማሞ የተወለዱት በምዕራብ ሸዋ ነው። ዘመኑም 1927 ዓ.ም። ሰው አይሆኑም የተባሉት ሰው÷ በስነ ጥበብ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል። ከዚህ ስኬታቸው አስቀድሞም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሽመልስ ሃብቴ እና በየነ መርዕድ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት።

በዚህ አልፈው ነው እንግዲህ አዲስ አበባ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤት የገቡት። እስከ አራተኛ ዓመት ከተማሩ በኋላም÷ በ1955 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ሶቪየት ህብረት ተልከው ለአንድ ዓመት ቋንቋ እና ዲዛይን፣ ለሶስት ዓመታት የመድረክ አቀማመጥ እና ዲዛይን ተምረዋል።

ስዕልን እና ተጓዳኝ ጥበባዊ ዕውቀትንም በሚገባ ተገንዝበው÷ ከሌኒንግራንድ አርት አካዳሚ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀው÷ በ1964 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ወትሮም ጅማሮዋቸው በነበረበት የአዲስ አበባ ስነ ጥበባት ትምህርት ቤትም በመምህርነት ተመደቡ።

በወቅቱ የክረምት ስልጠና በመስጠት የማስተማር ስራቸውን የጀመሩት ሰዓሊ ወርቁ ማሞ÷ በቀጣይ ዓመት መደበኛ ተማሪዎችን በመቀበል ስራቸውን ገፉበት። ተማሪዎች እሳቸውን ፈልገው ለመማር መምጣታቸው ብቻ ሳይሆን÷ እሳቸውም ክፍት ክፍለ ጊዜ ባገኙ ቁጥር ወደ ተማሪዎቻቸው ስለሚሄዱ ከተማሪዎቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው። በዚህም ሂደት በርካታ ተማሪዎችን አስመርቀዋል።

ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ዛሬ ላይ ሆነው ልጅነታቸውን ሲያስቡት ይገረማሉ። ይኼ መገረማቸው የሚመነጨው በልጅነታቸው ከገጠማቸው አደጋ እና በዚያ ምክንያት ባለፉበት የህይወት መንገድ ነው። ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፦

ሰዓሊው ገና የ9 ዓመት ልጅ ሳሉ÷ በጥበቃ ስራ የሚተዳደሩት አባታቸው ወደ ሚሰሩበት ጋራጅ እየሄዱ ይጫወቱ ነበር። ከቀናት መካከል በአንዱ እንደ ወትሮው ከጓደኛቸው ጋር ጨዋታ ይዘዋል። በዚህ መካከል ዝናብ ማካፋት ጀመረ። ሰዓሊ ወርቁ እና ጓደኛቸው ከዝናብ ለመጠለል በማሰብ ጋራጅ ውስጥ ከቆሙት መኪናዎች መካከል ወደ አንዱ ገቡ።

ጓደኛቸው መኪና ውስጥ እንደገባ አንዳች ብረት ነገር አነሳ። እሳቸው ያነሳው ነገር ቦምብ ሳይሆን እንዳልቀረ ጠርጥረዋል። ጥርጣሬያቸውን ለጓደኛቸው በመንገር መነካካቱን እንዲተው ቢያሳስቡትም የልጅ ነገር ሆነና ሳይሰማቸው ቀረ። እንደፈሩት ነገርየው ቦምብ ነበርና ፈንድቶ ጎዳቸው። በዚያ ፍንዳታ ምክንያት ሁለት እጃቸውን ያጡ ሲሆን አንድ አይናቸው ላይም መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የዚያ ዘመኑ ታዳጊ ወርቁ ማሞ ለህክምና ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ተወሰዱ። በጊዜው የደረሰባቸው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ከቁስላቸው ማገገም ቢችሉም÷ ለመብላት፣ ለመልበስ እና መሰል ግላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሰው እገዛ የግድ አላቸው።

እሳቸው ግን እንዲህ መቀጠልን አልፈቀዱም። ብርቱ ልምምድ በማድረግ በሂደት ብዙውን ነገር በራሳቸው ማከናወን ቻሉ። ይኼ ሁሉ ሲሆን የእናታቸው እገዛ እና ማበረታታት ትልቅ ቦታ እንደነበረው መቼም የሚዘነጉት አይሆንም።

የእናታቸው ድርጊት ሰዓሊው በዕለት ተዕለት ህይወታቸው ከሚያስፈልጋቸው ተግባር ከፍ ያለ ነበር። በእርግጥም ሁለት እጅ ለሌለው ልጅ ወረቀት እና እርሳስ አዘጋጅቶ መሞነጫጨር እንዲችል እና እንዲለማመድ ማበረታታት እንዲህ በዋዛ የሚታሰብ ሃሳብ አልነበረም። የሰዓሊው እናት ግን አሰቡት÷ አደረጉትም።

ሰዓሊ ወርቁ በዚህ ሂደት ሁለት እጆቻቸውን አስተባብረው ብዕር ይዘው መፃፍ ቻሉ። የሚፈልጓቸውን ምስሎች ለመሳልም በእጅጉ ተበረታቱ። ማንም ባላሰበው መልኩ ትልቅ ለውጥ ማሳየት የቻሉት ሰዓሊ ወርቁ ማሞ፣ መስራት እንደሚችሉ አሳምነው ትምህርት ቤት ገቡ።

በዚህ ሁሉ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው የሚፈልጉትን መሆን የቻሉት ሰዓሊው÷ “የእጆቼ መቆረጥ ለበጎ ነው” ይላሉ። ለዚህም በምክንያነት የሚጠቅሱት “ብዙዎች ተስፋ በቆረጡ ጊዜ÷ እኔን አይተው ተበረታተዋል። እሱ የማይቻለውን ከቻለ እኛም እንችላለን÷ ብለው ለትላልቅ ስኬቶች በቅተዋል” ይላሉ።

ሰዓሊ እና መምህር ወርቁ ማሞ ከሰሯቸው ታላላቅ ስዕሎች መካከል “አድዋ” በዋናነት ይጠቀሳል። አድዋ ሶስት ሜትር በስድስት ሜትር ሆኖ የተሰራ እጅግ ግዙፍ ስዕል ነው። አልገዛም ባይነት እና ጥቃትን መጥላት አንገብግቧቸው ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ጦረኞች በጥቁር ህዝብ ታሪክ ውስጥ የፃፉትን ታላቅ የድል ታሪክ ነው÷ በዚህ የስዕል ስራቸው የከተቡት።

ከአድዋ በሻገርም እናቶች፣ ሞዴል፣ ንጋት፣ ወደ ዘመቻ እና የመጨረሻ ዙር የተሰኙ ሌሎች ታላላቅ ስራዎች አሏቸው። ሰዓሊው በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት በግላቸውም፣ ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በመቀናጀትም በርካታ ኤግዚቢሽኖች ላይ ስራቸውን ለህዝብ አቅርበዋል።

ሰዓሊው ያውም ሁለቱንም እጆቻቸውን አጥተው የደረሱበት የስኬት ደረጃ እጅጉን ይገርማል። የሳቸው ደስታ ግን በስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ውስጥ ያስተማሯቸው ልጆች የተሻለ ደረጃ ላይ ሲደርሱላቸው ነው። በእርግጥም አብዛኞቹ ተማሪዎቻቸው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰውላቸዋል።

በአቢሲኒያ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ውስጥም እንዲሁ ስዕልን በማስተማር በርካታ ወጣት ሰዓሊያንን አፍርተዋል። ከወጣቶቹ ባሻገርም የእሳቸው ተማሪዎች የነበሩት እነ በቀለ መኮንን፣ ዮሐንስ ገዳሙ እና እሸቱ ጥሩነህ የመምህራቸውን የሰዓሊ ወርቁ ማሞን ታላቅነት ይመሰክራሉ።

የአርዓያ ሰው የሽልማት ድርጅት ሰዓሊ እና መምህር ወርቁ ማሞ በህይወት ዘመናቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በማሰብ÷ አምና ያከናወነው የሽልማት ስነ ስርዓት መታሰቢያ ለእርሳቸው እንዲሆን አድርጎ ነበር። በመድረኩ ላይም ካባ አልብሰው፣ የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ሽልማት አበርክተው አክብረዋቸዋል። በዕለቱ ሰዓሊና መምህርት ወርቁ ማሞ ይህን ብለው ነበር፦

“አንደበቴ የምስጋናውን መጠን ለመለካት በጣም እየተጨነቀ ነው። የማመሰግንበት አንዱ ምክንያት በልጅነቴ በቦምብ ከተጎዳሁ በኋላ ከሆስፒታል ወጥቼ ከእናቴ ጋራ ስራመድ÷ “ቢሞት ይሻለው ነበር” የሚሉ ሰዎች ነበሩ። እናቴ ግን “ለእኔስ ይኑርልኝ÷ መማር የሚችላቸው ብዙ ሙያዎች አሉ” በማለት ከጎኔ በመቆሟ ለዚህ ስኬት በቅቻለሁ። አሁንም እናቶች ልጆቻቸው ምንም እክል ቢኖርባቸው ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል። ይኼ ደስታ ምንም ጉዳት ቢኖርባቸውም ታግለው ልጆቻቸውን ማቆም ለቻሉ እናቶች ይሁንልኝ” ብለዋል።

አስቀድመው በአዲስ አበባ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት÷ ኋላም በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በአቢሲኒያ የስነ ስዕል ትምህርት ቤት ዘመናቸውን ሁሉ ሲያስተምሩ የኖሩት መምህርት እና ሰዓሊ ወርቁ ማሞ÷ ዛሬም ለማስተማር ወደ ኋላ አይሉም። መማር ለወደደ ሁሉ በትግል የቀሰሙትን እና በዕድሜ ያካበቱትን ጥበብ ያፈሳሉ።