ጥራትን መሠረት ያደረገ ትምህርት

በደረጀ ጥላሁን

ትምህርት ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ይህንኑ ለማሳካት ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራትን ለማጎልበት ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ በተለይ የተማሪዎችን  ውጤት ከማሻሻል አኳያ ችግሮች ይስተዋላሉ። ይህን ለመቅረፍ በሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

በሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ገ/ማሪያም በሀገር አቀፍና ክልል ደረጃ የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በክልሉ በ2014 እና በ2015 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት አነስተኛ መሆኑ ያለንበትን የትምህርት ጥራት ችግር አሳይቷል ብለዋል። ይህን ታሪክ ለመቀየር እንዲቻል ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ማምጣት አለባቸው በማለት በክልል ደረጃ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እንዲረዳ ችግሮችን የመለየት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህ መሰረት ለተማሪ መውደቅ መነሻው አንዱ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች የሆኑ እና የትምህርት ቤት ቅርጽ ያልያዙ በመሆናቸው ለህፃናቱ ምቹ አይደሉም፡፡ እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለፃ ራሳቸውን የቻሉ ትምህርት ቤቶች በጣም ውስን ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ቀደም ሲል በነበረው ስርዓተ ትምህርት ዜሮ ክፍል ተብለው ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጋር ነበር የቆዩት፡፡ ይህን ለማስተካከል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለብቻ መውጣት አለባቸው ይላሉ፡፡

ልጆች በተሻለ ትምህርት ቤት መማር ስላለባቸው በህብረተሰብ ተሳትፎ የሲዳማ ክልል የትምህርት ተሀድሶ ፈንድ ተቋቁሞ ህዝቡ፣ ባለሀብቶች እና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሳተፉ ተደርጎ ሥራ ከተጀመረ ሁለት አመት ሆኖታል፡፡ ስለዚህ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡

ሌላው ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ደርሰው መውደቃቸው እንጂ ለመውደቃቸው ምክንያት የሚሆነው በታችኛው የክፍል ደረጃዎች የሚሰራው ሥራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኤርሊይ ግሬድ ሪዲንግ አሲስመንት /አግሪ/ የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው ልጆች እስከ 3ኛ እና 4ኛ ክፍል ደርሰው ማንበብና መፃፍ አይችሉም፡፡ ይህን ለማስተካከል በማንበብ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ታፈሰ የተናገሩት፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደሚሉት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ማንበብና መፃፍ እንዲችሉ ፕሮጀክት ተቀርጾ መደበኛ ስራ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የማያነብ የ4ኛ ክፍል ተማሪ እንደ ክልል መኖር የለበትም በሚል እየተሰራ ነው፡፡ ሥራው በ2014 ዓ/ም የተጀመረ ሲሆን በ 185 ትምህርት ቤቶች ላይ የተለየ ክትትል ተደርጓል፡፡ በ2015 ዓ/ም ደግሞ ወደ 50 በመቶ በማሳደግ 531 ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት ተሰርቷል፡፡

እነዚህን ትምህርት ቤቶች ለየብቻ ባይመዘኑም በ2021 በተሰራው ጥናት በክልሉ 70 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች አንድም ቃል ማንበብ የማይችሉ መኖራቸውን የታየ ሲሆን በ2023 በተደረገው ጥናት ወደ 57 በመቶ ወርዷል፡፡ ከ3ኛ ክፍል ምንም ቃል የማያነቡ 49 በመቶ ሲሆኑ አሁን ወደ 32 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ መልካም ውጤት ነው፡፡ ኤርሊይ ግሬድ ሪዲንግ አሲስመንት /አግሪ/ ሲያጠና ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ያካተተ ነው፡፡ ይህን ጥናት የሚያስጠናው ደግሞ ሀገር አቀፍ የፈተናዎች አገልግሎት ነው፡፡

የክፍል ውስጥ መማር ማስተማር በሚገባ እንዲተገበር በተቻለ አቅም በጥሩ ዝግጅት፣ መምህራን በጥራት እንዲያስተምሩ እንዲሁም የትምህርት ብክነት ሳይኖር እንዲማሩ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የማጠናከሪያ ትምህርት በተለይ ለ12ኛ፣ 8ኛ እና 6ኛ ክፍሎች ይሠጣል፡፡ በየክፍሉ እስከ አምስትና አስር የወጡ ተማሪዎችን በመለየት የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጥ ተደርጓል። ከዚህ አኳያ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከአንደኛ መንፈቅ አመት የጀመሩ ሲሆን አሁን ግን ሁሉም ጀምረዋል፡፡ የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ በክልሉ እንደሚሰጥም ነው አቶ ታፈሰ የተናገሩት፡፡

የትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻል በተማሪ ውጤት ላይ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በክልሉ የሚገኙ በርካታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው፡፡ ደረጃ አንድና ሁለት ያሉትን ወደ ደረጃ ሶስት እንዲገቡ እየተሰራ ሲሆን ለዚህም ‹‹የተማሪ ውጤትና የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል ዘመቻ›› በሚል ለሶስት ወር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ወር ጀምሮ ክትትል እየተካሄደ እንደሚገኝም ነው አቶ ታፈሰ ያብራሩት፡፡

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተጀመረው ባለፈው አመት ሲሆን መማሪያ መጽሐፍት እና ለመምህራን ማስተማሪያ መጽሐፍት ተዘጋጅቷል፡፡ ይሁን እንጂ የአቅርቦት እምርታ ስላለ አብዛኞቹ  መጽሐፎች ፎቶ ኮፒ እየተደረጉ እንዲሁም በሶፍት ኮፒ በማሰራጨት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህ አመት ደግሞ ክልሉ ከ346 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የመጽሐፍት ህትመት በማከናወን የተሰራጨ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጽሐፍት ዝግጅትና ህትመት በፌደራል ደረጃ የሚከናወን በመሆኑ ለክልሉ የደረሰውን ለየትምህርት ቤቶቹ ተሰራጭቷል ብለዋል፡፡

የመምህራን ብቃት በተማሪ ውጤት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በክልሉ ያሉ መምህራን ተመዝነው ማምጣት የሚገባቸውን ውጤት ያላመጡ ነበሩ ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ብቃት ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት አጫጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ብቃታቸውን እንዲያሻሽሉ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም በርካታ መምህራንን በአጫጭር ሥልጠና ለማዳረስ ተሞክሯል፡፡ የረጅም ጊዜ ሥልጠናም እያገኙ ነው፡፡

ሌላው ስትራቴጂ በትምህርት ቤቶች ሲፒዲ /ተከታታይ የሞያ ማሻሻያ/ እንዲሰጥ ማድረግ ሲሆን በዚህም መምህራን ያሉባቸውን ችግር በመለየት ራሳቸውን የሚያሻሽሉበት እና የሚያበቁበት መሆኑን ነው አቶ ታፈሰ የተናገሩት፡፡

የትምህርት ቤት ማሻሻል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ሀንቃሞ  የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን፣ አመራሩንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተማሪዎች ውጤት እንዲያመጡ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱን ጠብቆ የመማር ማስተማሩ እንዲከናወን ክትትል እንደሚደረግ ገልጸው ተማሪዎች በችሎታቸው ብቻ የሚያልፉበት ሥርዓት እንዲኖር በመሰራት ላይ ነው ብለዋል፡፡

ምዘና እውቀትን ብቻ ሳይሆን ክህሎትን፣ አመለካከትንና እምቅ አቅምን እንዲመዘን ማድረግ በመሆኑ የመቅዳት ችግሮችን ለመፍታት የግንዛቤ ሥራዎችን ጨምሮ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡ በዋናነት ግን ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ተቆጥበው ትኩረታቸውን ለትምህርት በመስጠት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።

ተማሪዎች አስፈላጊውን ውጤት አምጥተው ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን ማወቅ፣ ምዘና እውቅትን ብቻ ሳይሆን ክህሎትን፣ አመለካከትን፣ እምቅ አቅምን እንዲመዘን ማድረግ፣ ለዚህ ስኬት ከወረቀት ፈተናዎች በተጨማሪ የምልከታ ክህሎትን፣ ነገሮችን ተንትኖ የማቅረብ ብቃትን፣ በፕሮጀክትና በጽሑፍ ስራዎች አማካይነት መመዘን፣ የትምህርት ምዘና ተከታታይ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ነሐሴ 2013 ይፋ ባደረገው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ ተመላክቷል፡፡

የትምህርት ጥራት ለሀገር ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝበን ከተማሪዎች መማር፣ ማጥናትና መፈተን፣ ከመምህራን በጥራት ማስተማር፣ እንዲሁም ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት ሁኔታ መከታተል አስፈላጊ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።