ኬሮድ የስፖርትና ልማት ማህበር ተተኪ አትሌቶች የሚፈሩበትና ለሀገራችን የአትሌቲክስ ዘርፍ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ የስፖርት ማህበር መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ

ኬሮድ የስፖርትና ልማት ማህበር ተተኪ አትሌቶች የሚፈሩበትና ለሀገራችን የአትሌቲክስ ዘርፍ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ የስፖርት ማህበር መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ

5ኛው ዙር ኬሮድ ታላቁ የጎዳና ላይ ሩጫ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን እንዳሉት፤ ኬሮድ የስፖርትና ልማት ማህበር ተተኪ አትሌቶች የሚፈሩበት ለሀገራችን የአትሌቲክስ ዘርፍ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ የስፖርት ማህበር ነው።

የኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ በሀገራችን የሚገኙ አትሌቶች አቅማቸውን የሚፈትሹበት ራሳቸውን ለቀጣይ ውድድር የሚያዘጋጁበት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ ስፖርት ወጣቶች አልባሌ ስፍራዎች ላይ እንዳይውሉ የሚረዳ በመሆኑ በዞኑ የሚገኙ ተተኪ ስፖርተኞችን የሚያፈሩ ክለቦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

አቶ ላጫ አክለውም፤ ውድድሩ አብሮነትን ለማጠናከር አካላዊ ብቃት ለመፈተሽ የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር፤ ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ የከተማውን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝብ ለህዝብ ከማስተሳሰርና አንድነታችንን ከምናጠናክርበት በላይ ተተኪ አትሌቶች የሚወጡበት በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ኬሮድ ሰላምና አንድነት የሚሰብክና የዞኑ ስፖርት እንዲያድግ እና ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው እየሰራ የሚገኝ ማህበር መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኬሮድ ስፖርትና ልማት ማህበር ፕሬዝዳንት አትሌት ተሰማ አብሽሮ ናቸው።

በ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ከ750 በላይ ኤሊት አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸውን በማንሳት ከ15 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ውድድሩ አትሌቶች ያደረጉትን ዝግጅት ለመሞከር የሚያግዝ መሆኑን ያነሱት ተወዳዳሪ አትሌቶች፤ ውድድሩ እጅግ ፈታኝ መሆኑን አስረድተዋል።

መሰል የጎዳና ላይ ውድድሮች አትሌቶች አቅማቸውን ለማሳየት የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

በመጨረሻም በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ለወጡ አትሌቶች ከአንድ መቶ ሀያ አምስት ሺህ ብር እስከ አምስት ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን