ከተማዋን ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኝ የድልድይ መሠረተ ልማት ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

ከተማዋን ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኝ የድልድይ መሠረተ ልማት ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

የድልድይ ግንባታ መከናወኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ የጎላ ፋይዳ እንዳለው የአከባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።

ይርጋጨፌ ከተማዋን አቋርጠው የሚያልፉ ሦስት ወንዞች እንዳሉዋት ገልጸው እነዚህ ወንዞች አቋርጠው በሚያልፉበት ሁሉ የድልድይ መሠረተ ልማት የሚፈልጉ ናቸው።
ምንም እንኳን የእንጨት ድልድዮች ቢኖሯቸውም ዘመኑን የማይመጥንና ወንዞቹ በሞሉ ቁጥር በውሃ የሚወሰዱ ነበሩ።
መስፍን በዙ፣ ሰናይት ጽጌና ሌሎችም በከተማዋ የወናታ፣ ሰዴና መልካሎሊ ነዋሪዎች ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ወደ ከተማ ወጥተው ለመመለስም ሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቻቸውን ለመከወን ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ተገንብተው መጠናቀቃቸው እንዳስደሰታቸው የሚናገሩት ነዋሪዎቹ አዲስ የተጀመረው ድልድይ በፍጥነት ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል።

ለዚህም ከህብረተሰቡ የሚጠበቀውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በከተማው የሚገኙ ወንዞች ከስጋት ይልቅ ወደ ጸጋነት ለመቀየር እየተሠራ ነው ያሉት የይርጋጨፌ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ታምራት ወንዞችን ከማልማትና ዳርቻዎችን ከማስጠበቅ ባሻገር የህብረተሰቡ ጥያቄ የሆኑ የድልድዮች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከተማዋን ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች በህብረተሰብ ተሳትፎና በመንግሥት በጀት እየተገነቡ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ዳዊት ተገንብተው ከተጠናቀቁት አራት ድልድዮች በተጨማሪ አምስተኛውን ጋርደን ብሪጅ በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታ ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።

ወንዞቻችን የቆሻሻ መጣያ ሳይሆኑ አልምተን ንጹህ በማድረግ ሌላኛው የከተማ ውበት ለማድረግ እየሠራን ነው ያሉት የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን የተጀመረውን የወንዝ ዳርቻ ልማት በአጭር ጊዜ ለማሳካት ቆርጠው እንደተነሱ አስረድተዋል።

የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግም ወንዞችን ትናንሽ የመዝናኛ ሀይቆችና ለኃይል አገልግሎት የሚውል ግድብ በረጅም ጊዜ እቅድ የማሳካት ራዕይ ሰንቀው እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: ውብሸት ካሣሁን-ከይርጋጨፌ ጣቢያችን