ከቡስካ ወደ ዲመካ

ከቡስካ ወደ ዲመካ

በአስፋው አማረ

የተወለዱት በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳ ቡስካ መንደር ነው፡፡ በልጅነታቸው ትምህርት የመማር ዕድልንም አግኝተዋል፡፡ ትምህርታቸውን ለመከታተል ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም።

መምህር ግርግር ደጀኔ ይባላሉ። ትምህርታቸውን ከ1ኛ እስከ 4ኛ በቡስካ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ 5ኛ እና 6ኛ ክፍል ደግሞ በዲመካ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡

በመቀጠል ወደ ጂንካ በማቅናት በደጃ አዝማች ለማ አቦየ ትምህርት ቤት 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በጂንካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡፡ በመቀጠል ወደ ሐዋሳ መምህራን ኮሌጅ በማቅናት በሁለገብ ትምህርት ክፍል ለአንድ ዓመት ሠልጥነው ተመርቀዋል፡፡

በመምህርነት ላይ እያሉ የትምህርት ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ በማቅናት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ከዚያም ወደ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ በማቅናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስፖርት ሳይንስ አግኝተዋል፡፡

የስራውን ዓለም የተቀላቀሉበትን አጋጣሚ ሲያጫውቱን፦

“በመምህርነት በሙርሲ ወረዳ ውብ ሐመር ትምህርት ቤት ሥራ ጀመርኩ፡፡ በመቀጠል ማሌ ኮይቤ ትምህርት ቤት፣ በና ፀማይ እና ሌሎች የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ በመምህርነት አገልግያለሁ፡፡

“በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች አገልግያለሁ፡፡ በመምህርነት፣ ሱፐርቫይዘርና እንዲሁም ርዕስ መምህር በመሆን ሰርቻለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በዲመካ መሰናዶ ትምህርት ቤት የባዮሎጂና ስፖርት ትምህርቶችን በማስተማር ላይ እገኛለሁ፡፡

“በሥራ ዓለም ላይ በርካታ ትውልዶችን መቅረጽ ችያለሁ፡፡ አካባቢው የአርብቶ አደር አካባቢ እንደመሆኑ ተማሪዎችን ማበረታታትና በቅርበት መከትተል ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ በወረዳም ሆነ በዞን በአመራርነት ላይ የሚገኙትን ብዙዎችን አስተምሬያቸዋለሁ፤ በርካቶች ቢሮ ላይ ባለሙያ በመሆን እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡

“በመምህርነት 38 ዓመት አገልግያለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ትውልድ በመልካም ስነ-ምግባር ታንጾ እንዲያድግ የበኩሌን ማበርከት ችያለሁ፡፡ ባሳለፍኳቸው የሥራ ዓመታት ሙያውን ወድጄና አክብሬ ሰርቻለሁ፡፡”

የአርብቶ አደር አካባቢ እንደመሆኑ መጠን ስለትምህርት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መስራት ችለዋል፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ቢልኩ ነገ እራሳቸው ተጠቃሚዎቹ እንደሚሆኑ በማስረዳትና በመወያየት ችግሩን ለመፍታት ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡ ይህንን ተግባር ከሌሎች መምህራን ጋር በመሆንም ሰፊ ሥራ ሰርተዋል፡፡

“የአካባቢው ተወላጅ እንደመሆኔ የአርብቶ አደር ልጆች ከብቶችን እየጠበቁ ትምህርታቸውንም ጎን ለጎን መማር እንደሚችሉ በማግባባት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እናደርግ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት አይላኩም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአርብቶ አደር አካባቢ ሴት ልጅ ስታገባ በርካታ ጥሎሽ ስለምታስገኝ እንደ ሀብት ትቆጠራለች፡፡ ከተማረች ደግሞ ባል አታገባም የሚል እምነት አላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርት ቤት አትላክም፡፡

“አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ባይባልም ችግሩ በተወሰነ ደረጃ እየተቀረፈ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ደክመናል፡፡ አጥጋቢ ባይባልም የተወሰኑ ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የማድረግ ሥራን ሰርቻለሁ” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ለትምህርት ሥራ ደከመኝ የማያውቁት መምህር ግርግር፣ ዲመካ ከተማ የደቡብ ኦሞ ዋና ከተማ ስትሆንም በትምህርት ተቋማት ላይ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና መቀመጫ ዲመካ ከተማ አመሰራረትን አስመልክቶ ሲናገሩ፦ “ዲመካ ከተማ ከመመስረቷ በፊት የአውራጃው መቀመጫ የነበረው ሐመር ኮኬ ልዩ ስሙ ቡስካ ነበር፡፡ ዲመካ ከተማ ከተመሰረተች 56 ዓመት ሆኗታል። ከቡስካ ወደ ዲመካ ደግሞ ከተማው የወረደው በ1960 ዓ.ም ነው፡፡

“ከሐመር ኮኬ ወደ ዲመካ ሊመጣ የቻለበት ምክንያት ደግሞ ለትራንስፖርት አመቺ ነው፣ ሜዳማ እና ሰዎች ከስፍራ ወደ ስፍራ ለመንቀሳቀስ ይቸገሩ ነበር፤ በከተማዋ ቀደም ብለው የሰፈሩት ሚሽነሪዎች(ሱዳን ኢንቲሬር ሚሽን) ነበሩ፡፡ የነሱን በአካባቢው ላይ መስፈር ተከትሎ ከተማው ተቆርቁሯል፡፡

“በወቅቱም የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ፈጠነ ይባላሉ፡፡ የዲመካ አካባቢን ተዟዙረው ከተመለከቱ በኋላ ከቡስካ ወደ ዲመካ መቀመጫው እንዲዞር የሚል ሀሳብ አቀረቡ። የአካባቢውን የሀገር ሽማግሌዎችን በማማከር በተደረገ ስምምነት እንዲወርድ ተደርጓል፡፡

“ከተማው ሲቆረቆር ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ነው በዲመካ የነበረው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ ሌሎች የመንግስት ተቋማት ሥራ ጀመሩ። ከተማዋ ቀስ በቀስ እየተስፋፋች መጣች፡፡

“ሚሽነሪዎቹ ቆይታቸውን ጨርሰው ዲመካ ከተማን ለቀው ወጡ፡፡ እነሱ በሄዱበት ጊዜ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ቤቶችን የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተረክበው አገልግሎት እንዲሰጡ ነው የተደረገው፡፡

“ከተማዋ ስትመሰረት 20 የሚሆኑ ነዋሪዎች መስርተዋታል፡፡ መንግስታዊ ተቋማት ደግሞ ፖሊስ፣ መምህራንና አስተዳዳሪ ብቻ ነበሩ፡፡ ከ1980 ዓ.ም በኋላ ግን ግብርና፣ ጤና፣ ፋይናንስና ሌሎች የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እየተሟሉ መጡ፡፡

በከተማዋ ትምህር ቤት እንዲከፈት መምህር ግርግር ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ በወቅቱ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት በማስታወስ እንዲህ ይላሉ፦

“ትምህርት ቤቱ ሲከፈት የአርብቶ አደር ልጆች አይማሩም ነበር፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ልጆች ነበሩ የሚማሩት፡፡ በ10 ተማሪዎችም ነበር የመማር ማስተማር ሂደት የጀመረው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት የሚገቡ የዐርብቶ አደር ልጆችም ቀስ በቀስ ቁጥራቸው እየጨመረ መጣ፡፡

“በዚህ ጊዜ ሆስቴል(የማደሪያና የምግብ አገልግሎት የሚገኝበት) አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ለአርብቶ አደር ተማሪዎች የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ይደረግላቸው ነበር፡፡

“በጊዜ ሂደት የመንግስት ተቋማት እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎ የነዋሪው ቁጥር ጨመረ፡፡ የአርብቶ አደሩ አኗኗር ዘይቤም እየተቀየረ ሲመጣ ከተማው እየተስፋፋ ሄደ፡፡ ይህን ተከትሎ ከሌላ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ ሰዎች መምጣት ጀመሩ፡፡

“መሰረተ ልማቶች እንዳሁኑ ከመስፋፋታቸው በፊት ከዲመካ ወደ ጂንካ ትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረም፡፡ ስለሆነም አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የሚሆነውን መንገድ በእግር በመጓዝ ነበር ትምህርታችንን የተማርነው፡፡

“ትምህርት ቤት መስከረም ላይ ሲከፈት እንሄዳለን፤ ስንማር ቆይተን ትምህርት ሲዘጋ ሰኔ 30 ወደ ቤተሰብ ጋር እንመለሳለን፡፡ ወደ አካባቢው አልፎ አልፎ የሚመጣው የፖሊስ መኪና ነው፡፡ የጥርጊያ መንገድ የተሰራው በ1980 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡

“ከ1980 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በሳምንት አንድ የህዝብ መኪና ትራንስፖርት ተመድቦ ሥራ ጀመረ፡፡ የህዝብ ትራንስፖርት በቋሚነት ተመድቦ መስራት የጀመረው ግን ከሁለት ሺህ በኋላ ነው” በማለት የችግሩን ስፋት አውግተውናል፡፡

እንደዚህ ያሉና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮች ባሉበት የአርብቶ አደር ልጅን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን መንግስት በሚያደርገው የምገባ ፕሮግራም፣ ደብተር፣ ብዕርና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የአርብቶ አደር ልጆች እንዲማሩ ተደርጓል፡፡

አሁን ላይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የትምህርት ተደራሽነትን በተመለከተ ትልቅ ሥራ መሰራቱን ይናገራሉ፡፡ ጥራቱን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት የሚናገሩት መምህር ግርግር፤ ልጆችን በማስተማር ማህበረሰቡን በቀላሉ መቀየር ይቻላል የሚል እምነትም አላቸው፡፡

እሳቸው ለበርካታ ተማሪዎች በግላቸውና ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር በመሆን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች እገዛ ያደርጉ ነበር፡፡ ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ በማድረግ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡ ከ15 በላይ የሚሆኑ የኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የጀመሩትን ትምህርታቸውን እንዲጨርሱም ረድተዋቸዋል፡፡