ችግርን ወደ ዕድል የቀየረች

በደረሰ አስፋው

ትጉህ ናት፡፡ ለዚህ ምስክሯ ያለፈችባቸው የለውጥ ጉዞዋ ነው፡፡ ትጋት መታወቂያዋ፣ ብርታትና ከበሬታ ልብሷ ናቸው። የወንድሞቿ አብሮነትና ድጋፍ የሞራል ስንቅ ቢሆናትም የራሷ የአስተሳሰብ ልዕልና ደግሞ ለስኬቷ ላቅ ያለውን ስፍራ ይዟል፡፡ ከጓዳዋ የጀመረው ስራዋ በአደባባይ የመታየት ዕድልን ፈጠረላት።

ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከትምህርት እስከ ንግድ ባለው ቆይታዋ በጊዜ፣ በሁኔታ፣ በማግኘት እና በማጣት ሞራሏ ወድቆ እንደማያውቅ ነው የገለጸችልን። ይህቺ ሴት ዘመኑን የዋጀች ናት። የንግድ አሰራር ታውቃለች። በንግዱ የውስጡንም የውጪውንም ታሳልጣለች። ያለውን የማስተዳደር ብቃት፣ የሌለውን ፈጥሮ የማቅረብና ከቤቷ አልፎ ለውጪ ስራም እጅ አልሰጠችም።

ወ/ሪት ተስፋነሽ ለማ ትባላለች፡፡ የሙዱላ ከተማ ነዋሪ ነች፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ተስፋነሽን “ተስፉ” እያሉ ይጠሯታል፡፡ የተወለደችው በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዘንባራ ቀበሌ ነው፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቷን ያጠናቀቀቸው በሙዱላ ከተማ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ወደ ሆሳዕና ከተማ በመሄድ በግል የትምህርት ተቋም በቢዝነስ ማናጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች፡፡

ተማሪ እያለች ከትምህርቷ ጎን ለጎን ከንግድ ስራ ጋር ተለማምዳለች፡፡ ንግዱን የጀመረችው በቡና ነው፡፡ ወደ አርሶ አደሩ መንደር ጎራ እያለች በቅናሽ ዋጋ ትሸምታለች። ይህንኑ ወደ ከተማ በማምጣት በችርቻሮና በጅምላ በመሸጥ ታተርፋለች፡፡ እህልም በተመሳሳይ በጋ ላይ በርካሽ ገዝታ አትርፋ ትሸጣለች፡፡ ይህ በመንደር ገበያ የጀመረችው ንግድ ዛሬ የህይወቷ መተዳደሪያ ሆኗል። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከገበያው ንግድ ወደ ሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ንግድ ተሰማርታለች፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የቀድሞ ስራዋን ሙሉ ለሙሉ አልተወችውም፡፡

“በአካባቢው ያሉ ገበያዎችን ሁሉ አስሳለሁ፡፡ የገዛሁትን እህልም ሲገኝ በመኪና ሳይገኝ በአህያ አስጭኜ ወደ መንደር እወስዳለሁ፡፡ ከዚህ ስራ ጎን ለጎን ፍየል፣ በግና ዶሮም ገዝቼ በማሞከት እሸጣለሁ፡፡ ይህ ስራዬ እና ጥረቴ አድጎ እና ተመንድጎ ዛሬ ላይ በሙዱላ ከተማ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ለመክፈት የሚያስችለኝን ጥሪት ማፍራት አስቻለኝ” ስትል ነው የገለጸችው፡፡ ታዲያ በግል በቢዝነስ ማናጅመንት የቀሰመችው ዕውቀትም የንግድ ክህሎቷን ለማሳለጥ እንደጠቀማት ነው የምትገልጸው፡፡ ንግድ በእድል ሳይሆን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሲሆን ውጤቱ የተሻለ እንደሚሆን በመጠቆም፡፡

ወደ ንግዱ ስትገባ በአንድ ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ነው፡፡ ከ12ኛ ክፍል ውጤት በኋላ ወደ ሆሳዕና ሄዳ በግል የትምህርት ተቋም ነው የተማረችው፡፡ ለዚህም በግብርና ስራ ከሚተዳደሩ ቤተሰቦች ድጋፍ ወይም እርዳታ አላሻትም፡፡ ይልቁንስ ነግዳ ባጠራቀመቻት ጥሪት ከፍላ ነው የተማረችው፡፡

ወ/ሪት ተስፋነሽ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የቀጣይ የህይወት ጉዞዋ ያሳስባት ነበር።  ለዚህም የመፍትሄው አካል ያደረገችው እራሷን ነው፡፡ በመንደር አካባቢ ቡና ገዝታ ችርቻሮ መሸጥ፡፡ ወደ ንግዱ መሰማራቷ ብዙ ሀሳቦቿን እንዳቃለለላት ነው የተናገረችው፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ አድርጓታል። ከራሷም አልፋ ቤተሰብን መደገፍ የምትችልበትን አቅም ፈጥሮላታል፡፡

አሁን ላይ የተሰማራችበት የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ቀደም ብላ ከምትሰራው የተሻለ እንደሆነ ታነሳለች፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ ይገጥማት የነበረውን ድካም አቅልሎላታል። በሱቋ ውስጥ አስፈላጊ የተባሉ ነገሮች ሁሉ ይገኛሉ፡፡ አለ እንጂ የለም የማይባልበት ሱቅ ነው፡፡ ይህንንም የላቀ ደረጃ ለማድረስ ትተጋለች፡፡ እህል ገዝቶ አትርፎ መሸጡንም ዛሬም አልዘነጋችውም፡፡ የአርሶ አደር መንደሮችን አልረሳችውም፡፡

ከዛሬ 3 ዓመት በፊት ሱቅ ስትከፍት 30 ሺህ ብር ዕቁብ ደርሷት ነበር፡፡ የነገውን ራዕይዋን ለማየት የሚጓጉት የወንድሞቿ ድጋፍም አልተለያትም፡፡ አሁንም ቢሆን እቁብ መጣሉን አልዘነጋችውም፡፡ በሳምንት 500 ብር እንደምትጥል በማስታወስ፡፡ እቁብ ለነጋዴ አስፈላጊ እንደሆነም ታነሳለች፡፡ ለነጋዴ ገንዘብ በስራ ላይ ማዋሉ ጠቃሚ በመሆኑ አብዛኛውን ገንዘቧን በሸቀጥ ላይ ነው የምታውለው፡፡

“የሰው ልጅ እቅድ ማብቂያ የለውም። ቡና እና እህል ገዝቼ ቸርችሮ በመሸጥ የተጀመረው ስራዬ ዛሬ እዚህ ደርሷል። ነገም ይህንኑ ስራዬን የላቀ ደረጃ ለማድረስ ነው የዘወትር ሀሳቤ፡፡ የግል የምለው መኖሪያ ቤት መስራትም የዕቅዴ አካል ነው፡፡ ሱቁንም ቢሆን በከተማው የተሻለ ሱቅ እንዲሆንና የደንበኞቼን ፍላጎት ለማሟላት ነው የምጥረው” ብላለች፡፡

በጀርባዋ ላይ ያለው የአካል ጉዳት እንደልብ ለመንቀሳቀስ ቢፈትናትም ለዚህ ግን እጅ አልሰጠችም፡፡ “ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንደተባለው ድካም አለ ብዬ ሳልሰራ መኖር አልችልም፡፡ ሰርቶ የሚገኝ ጥቅም ያስደስታል፡፡ እንዲያውም ትጋትን ይጨምራል” ነው ያለችው፡፡

አሁን ላይ በአንድ ሺህ ብር የጀመርሽው የንግዱ ስራ ምን ያህል ካፒታል ደርሰሻል ስል ላነሳሁላት ጥያቄ ስትመልስ፡-

“በእርግጥ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደደረስኩ ይሰማኛል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ባልልህም ወደዚያው እየተንደረደርኩ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በዚህም ደስተኛ ሆኜ ነው የምሰራው፡፡ የተሻለ ገንዘብ ቢገኝ በርካታ የስራ አማራጮች አሉ። በአጭር ጊዜም የተሻለ ደረጃ ይደረሳል። ከሱቁ ጎን ለጎን ብዙ ስራ መስራት ይቻላል። ዛሬ ለንግድ ምቹ ሁኔታ አለ፡፡ ለመንቀሳቀስ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክሎች አሉ፡፡ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎችን በመዳሰስ ብዙ መስራት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ተጨማሪ ገንዘብ ባለመኖሩ ይህን እውን ማድረግ አልቻልኩም፡፡

“አካል ጉዳተኛ ሰርቶ የመለወጥ ብሎም ስራ የመፍጠር ዕድሉን የነፈጋቸው የለም። የዚህ ዕድል ነፋጊዎች እራሳቸው እንጂ። የራሳቸው የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ቀዳሚው ሊሆን ይገባል” ስትል አካል ጉዳተኛ በመሆኗ የገደባት ነገር እንደሌለ ነው የምትገልጸው፡፡

ወ/ሪት ተስፋነሽ በአሁን ወቅት የምትሰራበትን ሱቅ ተከራይታ ነው የምትሰራው፡፡ በወር 2 ሺህ 500 ብር ትከፍላለች፡፡ ዓመታዊ ግብሯንም በታማኝንት እንደምትከፍል ታነሳለች፡፡ ይህ በመስራቷ የመጣ እንደሆነ ገልጻ አካል ጉዳተኞች ከሰሩ ከራሳቸው አልፈው ለሀገርም አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ነው የተናገረችው፡፡ በዚህ ላይ ድጋፍ የሚያደርግላት አካል የለም።