የታዳጊዎች የአዕምሮ ስነ-ጤና

የታዳጊዎች የአዕምሮ ስነ-ጤና

በገነት ደጉ

በዓለማችንም ይሁን በሀገራችን የታዳጊዎች ስነ- አዕምሮ ችግር እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየከፋ በመምጣቱ በታዳጊዎች ጤና ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

የታዳጊዎች ወላጆችም በልጆቻቸው ላይ የሚታየውን ችግር በቀላሉ መረዳት ባለመቻላቸው ችግሩ እየከፋ ሄዷል፡፡ ልጄ አፉን አልፈታም በማለት ከዛሬ ነገ ይፈታል ብለው በመዘናጋት ችግሩ ይባባሳል፡፡

በተለይም ለችግሩ አጋላጭ ከሚባሉት ጉዳዮች መካከል ከታዳጊዎች ጋር ተያይዞ ከእጅ ስልኮች እና ቲቪ እስክሪኖች እይታ እንዴት እንገድባቸው? እነዚህ ነገሮች የሚያስከትሏቸው የጎንዮሽ ጉዳቶችስ ምንድናቸው?

ፓነሲያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህፃናት ህክምና እስፔሻሊስት ዶክተር ብሩክታዊት አረጋዊ እንዳሉት ህፃናት እና ታዳጊዎች ረጅም ጊዜያቸውን በስልክ፣ በቴሌቪዥን፣ በታብሌቶች እና በኮምፒዩተር መስኮቶች ላይ ማሳለፋቸውን አንስተው እነዚህ መስኮቶች አዝናኝ፣ አስተማሪ እንዲሁም ጊዜ የሚያሳልፉባቸው ጭምር ስለመሆናቸው ነው የሚናገሩት፡፡

ግን ከልክ ያለፈ ሲሆኑ ደግሞ ተያያዥ እና የጎንዮሽ ችግሮችን እንደሚያመጡ የጠቀሱት ዶክተር ብሩክታዊት ቤተሰብ ልጆች ምን እያዩ ነው? ለምን ያህል ጊዜ እያዩ ነው? ለምን እየተጋለጡ ነው? የሚለውን መከታተል እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

ቤተሰብ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በድካምም ይሁን በሌሎች የቤተሰብ ኃላፊነትን ከመወጣት ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ልጆች የሚከታተሉትን ነገሮች በግልጽ ባለማወቅ እና የሚከታተሉትን መመጠን ባለመቻል ችግሩ እንደሚከሰት ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም ሂደት ህፃናት ከሁከት ጋር የተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮችና አደገኛ የሆኑ ልምምዶች ላይ የሚያደርሱ ነገሮችንም ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡

በዚህ አኳኋን ልጆች በቤት ውስጥ መሞከር የሌለባቸው ነገሮች እንደሚያዩ ያነሱት ዶክተር ብሩክታዊት ህፃናቱ በተለያዩ ሙከራ ውስጥ በመግባት ህይወታቸውን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ህይወታቸውን ሊነጠቁ እንደሚችሉ የተለያዩ ከባህር ማዶ እና ከሀገር ውስጥ ያሉ መረጃዎች እንደሚዘግቡ በማስረዳት፡፡

ሌላው ወሲባዊ ልምምድ ያላቸውን ቪዲዮዎችን ያለዕድሜያቸው ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ ይህም ቀጣይ ህይወታቸውን ሊጎዳ የሚችል ስለመሆኑ የገለፁት ዶክተር ብሩክታዊት አደንዛዥ ዕፆችን በመጠቀም ደስተኛ ጊዜን ማሳለፍ ይቻላል የሚል አደገኛ መልዕክት የሚያሳዩ ቪዲዮች በመመልከት እና ፊልሞችን በማየት ወደ ተግባሩ ሊሸጋገሩ ይችላሉ፡፡

ህፃናት ሁሉንም ነገሮች መሞከር የሚፈልጉበት እድሜዎች ያላቸው መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ብሩክታዊት ቤተሰብ በቅርበት የማይከታተላቸው ከሆነ ህይወታቸውን ለአደጋ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

የመጀመሪያው 36 ወራት እስከ ሶስት ዓመታት ባለው ጊዜ ህፃናት ላይ የአዕምሮ ግንባታዎች የሚካሄዱባቸው ወቅቶች መሆኑን ጠቅሰው ይህም በሰውነት፣ በአስተሳሰብ፣ ለትምህርት በመዘጋጀትና አካባቢያቸውን በመላመድ ዝግጅት የሚያደርጉበት ወቅት በመሆኑ ቤተሰብ ልጆቹን በትኩረት መከታተል ያለበት ወቅት መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

ልጆች ልምምዶቹን በሚሞክሩበት ወቅት ለብዙ ችግሮች እንደሚያጋልጧቸው የሚያነሱት ዶክተር ብሩክታዊት ለዓብነት ጥሩ እንቅልፍ አለማግኘት እና ማደግ በሚችሉበት ፍጥነት አለማደግ፣ የትምህርት ውጤታቸው መቀነስ፣ ረጅም ጊዜ ስለማይንቀሳቀሱ አላስፈላጊ የሰውነት ክብደት መጨመር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ቤተሰብም ልጆችን ከመከታተል ይልቅ እራሱ በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚጠመድ ነው የጠቀሱት፡፡

በተጨማሪም ልጆች ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍን መጥላት አንዱ ምልክት ሲሆን ትምህርት ቤት ውስጥም ጓደኛ አለማፍራት ከሚታዩ ምልክቶች መካከል ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በንግግር መዘግየት እራሳቸውን መግለጽ አለመቻል እና መናገር የቻሉ ልጆች ተመልሰው ለመናገር መቸገር ጭምር በምልክቶች የሚካተቱ ናቸው፡፡

ሌላው ምልክት ሊሆን የሚችለው ከሰዎች ጋር አለመግባባት፣ መነጫነጭ መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ብሩክታዊት እነዚህ ችግሮች ላይ የወደቁት ህፃናት በመጨረሻም የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው የእስክሪን እይታን ያለመገደብ ስለመሆኑ ያነሳሉ። ያለ ዕድሜያቸው እስክሪን እንዲመለከቱ መፍቀድ ለህፃናት አዕምሮ ጤና ችግር መንስኤ ስለመሆኑ ነው የተብራራው፡፡

ከታዳጊ ህፃናት ስነ- አዕምሮ ጤና ጋር ተያይዞ ኦቲዝም የሚጠቀስ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ብሩክታዊት ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ግን “ቨርቹዋል ኦቲዝም” የሚባለው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ይህም ለረጅም ሰዓት እስክሪን ላይ በመቆታቸው ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ በዚህም ህፃናቱ ልክ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ላይ እንደሚስተዋለው ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡

ችግሩ ባለባቸው ህፃናት ላይ በተለይም የቋንቋ መዘግየት በስፋት የሚታይባቸው ሲሆን ቤተሰብ ክትትል ማድረግ እንደሚገባው ዶክተር ብሩክታዊት አሳስበዋል፡፡

ህፃናቱ እስክሪን ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ከእውነታው ዓለም ስለሚወጡ ይህም የአዕምሮአቸው ሴሎች ማደግ ባለባቸው ፍጥነትና መጠን እንዳያድጉ ያደርጋል፡፡ ይህም ዞሮ የስሜት ህዋሳቸው ጥቂቱ ብቻ በመሆኑ እራሳቸውን መግለጽ እንደሚቀንሱና እንደሚያቆሙ ነው የሚያስረዱት፡፡

ማንኛውንም ነገር መግለጽ የሚጀምሩት በምልክት እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ብሩክታዊት ይህንን ስጡኝ ከማለት ይልቅ መጎተት እንደሚያዘወትሩ ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህም ሰዎች ሳይረዱአቸው ሲቀሩ ስሜታዊ እንደሚሆኑ ነው ያመላከቱት፡፡

በዚህም የተነሳ ከአካባቢያቸው ጋር ማለትም አባት፣ እናት፣ ሞግዚት፣ እህትና ወንድም ጋር መግባባት ባለመቻላቸው ምክንያት ቁጡዎች ይሆናሉ፡፡

በአዳሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና እስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ግዛቸው ለገሰ የአዕምሮ ጤና የሀሳብ፣ የስሜትና የባህሪ ሲሆኑ የእነዚህ ደህንነት የአዕምሮ ጤና ሊባል እንደሚቻል ነው የገለፁት፡፡

የአዕምሮ ህመም የምንለው ደግሞ የእነዚህ የሶስቱ ማለትም የሀሳብ፣የስሜት እና የባህሪ መዛባት ነው ያሉት ዶክተር ግዛቸው የሰው ልጅ ጤናማ ህይወት ለመኖር እና እለት ተዕለት በሚያከናውናቸው ጉዳዮች ስኬታማ ለመሆን የእነዚህ አንድ ላይ ተጋግዞ እና ተደጋግፎ መስራት አስፈላጊ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የአዕምሮ ህመም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ዶክተር ግዛቸው ችግሩ ጠለቅ ወይም ሰፋ ያለ መሆኑን አንስተው በተለይም ህፃናቶችን በተለየ መንገድ እንደሚያጠቃቸው ነው የተናገሩት፡፡

ህፃናት ልክ ሌሎች አካላዊ ህመሞች እንደሚያጠቃቸው ሁሉ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው የአእምሮ ህመም እንደሚገጥማቸው የሚያነሱት እስፔሻሊስቱ አብዛኛውን በማህበረሰቡ የተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት ህፃናት የአዕምሮ ህመም የሚያገኛቸው ሰዎች አሉ፡፡

በዚህ ዙሪያ የህብረተሰባችን ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ነው ያሉት ዶክተር ግዛቸው የህፃናት የአዕምሮ ህመም እራሱን የቻሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት ሲሆን ህብረተሰባችን ወደ ህክምናው ተቋም ከማምጣት ይልቅ ወደ ቤተ-እምነትና እቤት ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚቀናቸው ነው የጠቀሱት፡፡

በተለይም በእስክሪን ላይ የሚያዘወትሩ ታዳጊ ህፃናትን የአዕምሮ እድገት ውስንነት ህመም እንደሚያጠቃቸው የጠቀሱት ዶክተር ግዛቸው ሌሎችም አዋቂዎችን የሚያጠቋቸው ተጨማሪ ህመሞች በሙሉ ህፃናቱ ላይም ሊከሰቱ እንደሚችሉ ነው ያስረዱት፡፡

ህፃናቶችን እና ወጣቶችን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ የአዕምሮ ህመም እንዳለ ያጫወቱን ዶክተር ግዛቸው ይህም ከአዕምሮ እድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሲሆን ለአብነትም ኦቲዝም፣ የአዕምሮ ውስንነት፣ ከሰዎች ጋር አለመግባባት፣ ትኩረት አለመስጠት፣መፍጠን፤ ትኩረት መሳብ አለመቻል እና መናገር አለመቻል የመሳሰሉ ናቸው ብለዋል፡፡

መንስኤዎቹ የተለያዩ ናቸው የሚሉት ዶክተር ግዛቸው መንስኤዎቹ ለአብነትም ከዘረመል፣ ከስነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ ምክንያቶች ጋር የተቆራኙ ስለመሆናቸው ነው የጠቀሱት፡፡

ወደ ህፃናቱ ሲመጣ ከአካባቢ ሁኔታዎች፣ ከጀኔቲክስ እና እንዲሁም ህፃኑ ሲረገዝ ጀምሮ በሚገጥም እክል ሊነሳ እንደሚችል ያነሱት ዶክተር ግዛቸው እናትየው በእርግዝና ወቅት በተለያየ ቫይረሶች ስትጠቃ እና በምትወስዳቸው አልኮልና አደንዣዥ እፆች ሳቢያ ሽሉ ሊጠቃ ይችላል፡፡

በተለይም የመናገር ችግር ያለባቸው እና በጊዜ አፋቸውን መፍታት ያልቻሉ ህፃናት ከሞባይል እና ከቴሌቪዥን ጋር ተያይዞ ረጅም ጊዜ መቆየት አንዱ ችግር በመሆኑ ቤተሰብ ህፃናት ከቴክኖሎጂ ጋር የሚቆዩበትን ጊዜያት በመገደብ ሊገጥማቸው ከሚችለው ችግር ሊታደጋቸው ይገባል፡፡