የምኞት፥ “እጅ አዙር”

በአንዱዓለም ሰለሞን

እነሆ አዲሱን የየማ ሙዚቃ እየሰማሁ ነበር፤ ፖስተኛው መጣ የሚለውን፡፡ ሙዚቃውን እሰማ የነበረው ደግሞ አጋጣሚ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ የተወሰኑ የክፍል ጓደኞቼ  ሀሳቦቻቸውን ያሰፈሩበትንና ለማስታወሻ ይሆነኝ ዘንድ ፎቶ ግራፋቸውን የለጠፉበትን ደብተር (አውቶግራፍ) እያየሁ ነበር፡፡ ግጥምጥሞሹ ለትዝታዬ የተለየ ስሜት ሰጥቶታል፡፡ ሙዚቃውም፣ ማስታወሻ ደብተሩም ትዝታን የሚጠሩ ናቸው፡፡

ከደብተሩ አንደኛው ገጽ ላይ ስለ ጓደኛና ጓደኝነት የተነገሩ የተወሰኑ ጥቅሶችና አባባሎች ተከትበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው፡-

“መልካም ጓደኛ የህይወት መስታወት ነው”  ይላል፡፡ እርግጥ ነው፤ ጥሩ ጓደኛ ጥሩ ጎናችንን የሚነግረን ብቻ ሳይሆን ድክመታችንንና ጉድለታችንንም የሚያሳየን ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ጓደኛችን “ከማይረባ ጓደኛ ሰባራ መስታወት ይሻላል” የሚለውን አባባል የሚያስታውሰን ነው የሚሆነው፡፡

መተሳሰብ ያለበት ጓደኝነት ለመመስረት ጊዜ ያስፈልጋል፤ “እውነተኛ ጓደኝነት ቀስ በቀስ የሚመሰረት ሲሆን ጓደኝነት ከመባሉም በፊት ብዙ ፈተናዎችን ያልፋል” እንዲል ጆርጅ ዋሽንግተን፡፡

በህይወት ጥሩ ጓደኛ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጓደኛ ልክ እንደ ወተት ማለት ነው፤ በትኩሱ የሚጠጣ፣ ሲረጋ የሚጠጣ፣ ሲናጥ ቅቤ የሚወጣው፡፡ (ይህን ያልኩት እኔ አለመሆኔንና ደብተሩ ላይ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ሆኖ የተከተበ መሆኑን ልብ በሉልኝማ)

በዚህ መንደርደሪያ ጓደኞቼ ለአውቶግራፉ ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሾች በተመስጦ ሆኜ አነብ ጀመር፡፡ ከሀያ ሁለቱ ጥያቄዎችና ምላሾቻቸው ትኩረቴን በተለየ መልኩ የሳቡ ቢኖሩም ከርዕሰ ጉዳዬ አንጻር አስረኛውን ጥያቄ ልጥቀስ፡-

ጓደኝነትን እንዴት ይገልጹታል? ይላል ጥያቄው፡፡ ከምላሾቹ መካከል የተለየ ስሜት የሰጡኝን እነሆ፡-

“ጓደኝነት ማለት ለእኔ አንዱ ለአንዱ እንደቆመ እንደ ትልቅ ህንጻ ወለል ነው፡፡” ሌላኛው ጓደኛዬ ደግሞ እንዲህ አለ፡-

“ጓደኛ ማለት ለእኔ እንደ አንድ ኩላሊት ማለት ነው፡፡”

ይህንን የጓደኛዬን ምላሽ ሳነብ ጓደኛዬ ይህን ያለው ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት፣ ኩላሊት እንዲህ እንደዛሬው ሳይወደድ በፊት መሆኑን አስቤ መገረሜ አልቀረም፡፡ ሌላኛው ደግሞ እንደዚህ በማለት መለሰ፡-

“ጓደኝነት በህይወታችን የምናገኘው አንድ የማይረሳ ስጦታ ነው፡፡”

ሌላኛዋ ደግሞ ተመሳሳይ ትርጓሜ በመስጠት በተለየ አገላለጽ እንዲህ በማለት ምላሿን ከተበች፡-

“ጓደኛህ በአንድ ወቅት የነበረህ ወይም እስከ መጨረሻው ሊኖርህ የሚችል ጌጥህ ማለት ነው፡፡”

ሌላኛዋ ጓደኛዬ ደግሞ የሚሰማትን እንዲህ በማለት ገለጸች፡-

“ጓደኝነት ማለት ለእኔ፤ በመዋደድ፣ በመከባበር፣ በመቀራረብና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ዝምድና ነው፡፡”

ይህን በእዚህ ልግታና ወደ ሌላ አንድ ጥያቄ ልለፍ፡፡ ጓደኞቼ በወቅቱ ለአንድ ጥያቄዬ የሰጡኝን ምላሽና አሁን ላይ የሆነውን ነገር ሳስበው መገረሜ አልቀረም፡፡ ጥያቄው “ለወደፊት ምን መሆን ይፈልጋሉ?” የሚል ነው፡፡ አሁን ላይ ሳስበው ብዙዎቹ የተመኙትና ሆነው የተገኙት ለየቅል ነው፡፡

ጋዜጠኛ ለመሆን እንደሚፈልጉ የገለጹ ሁለት ልጆች ኢኮኖሚክስ አጥንተው በሌላ የሙያ መስክ ተሰማርተዋል፡፡ ሳይኮሎጂስት ያለችው ልጅ ፖለቲካል ሳይንስ አጥንታ ውጪ ሀገር እየሰራች ሲሆን፣ ውጪ ሀገር የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ መስራት እፈልጋለሁ ያለኝ ልጅ በአካውንቲንግ ተመርቆ ካሰበው በተራኒው፣ በሌላ የሙያ መስክ ተሰማርቷል። …

“ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ፤ እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በቅርቡ አብሮኝ ከተማረ አንድ ጓደኛዬ ጋ ድንገት መንገድ ላይ ተገናኘንና በቆምንበት ጥቂት አወራን፡፡

“የት ነው የምትሰራው?” ሲል ጠየቀኝ ጓደኛዬ፡፡ የምሰራበትን ነገርኩት፡፡ እርሱም ጥያቄውን ቀጠለ፡-

“ቤተሰብ መሰረትክ?”

ትዳር መያዜንና የአንድ ልጅ አባት መሆኔን ነገርኩት፡፡

“ቤት ሰራህ?”

“አልሰራሁም፡፡”

ቀጥሎ ተረኛ እኔ ሆንኩና እሱ የጠየቀኝን ጥያቄዎች መልሼ ጠየኩት፡፡ እሱም ትዳር መያዙንና የሁለት ልጆች አባት መሆኑን ብሎም ቤት መስራቱን ነገረኝ፡፡ ሌላ ጊዜ እንደምንገናኝና በሰፊው እንደምንጨዋወት ተነጋግረን፣ ስልክ ተለዋውጠን ልንለያይ ስንል፡-

“እኔ ምልህ…” ሲል ለሌላ ጨዋታ መንደርደር ጀመረ፡፡ ትኩረቴንና ጆሮዬን ሰጠሁት፡-

“ማትሪክ ስንፈተን አብረን እንደተቀመጥን ታስታውሳለህ አይደል?”

“አዎ፡፡” አልኩ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ሳይመጣለት መቅረቱ ትዝ እያለኝ፡፡

“አቤት፤ ውጤት የተነገረ ቀን ምነው ካንተ በኮረጅኩ ኖሮ ብዬ መቆጨቴንና የዚያን ዕለት ያለቀስኩትን ልቅሶ መቼም አልረሳውም” አለ እየሳቀ፡፡

“እንኳንም ሳትኮርጅ ቀረህ” አልኩ እኔም አብሬው እየሳቅሁ፡፡ ቀጠልኩና፡-

“በራስህ መንገድ ተጉዘህ ይኸው ዛሬ የራስህን ህይወት እየመራህ ነው፡፡ ነገሮች የሚሆኑት ለበጎ ነው፤ በአንድ ነገር ብቻ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡ አንደኛው አልከፈት ሲል ሌላኛውን በር ማንኳኳት ነው፡፡”

እንግዲህ የምናስበውን ሆነን የምንገኝበት ሁኔታ መፈጠሩ አንድ የህይወት አጋጣሚ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፤ የአንዲት የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ነገር፡፡ ልጅቱ በትምህርቷ ደካማ ነበረች፡፡ አንድ ቀን ከሌሎች ጓደኞቻችን ጋር ሆነን ከዩኒቨርሲቲ ስንመረቅ ምን መሆን እንደምንፈልግ ስናወራ፦

“የህክምና ባለሙያ ብሆን ደስ ይለኝ ነበር” አለች፡፡

“እና?”

“ምን እናስ አለው፤ በዚህ ውጤቴ እንዴት ነው ዶክተር የምሆነው!?”

እርግጥ ነው፤ ዶክተር ልትሆን ይቅርና ዩኒቨርሲቲ ሊያስገባት የሚያስችላትን ውጤትም አላመጣችም፡፡ ግን ደግሞ ዶክተር ባል አግብታለች፡፡ ምኞትህን “በእጅ አዙር” ማሳካት ይሉሀል ይህ ነው፡፡ የሚያስገርመው ነገር ግን የልጅነት ምኞቷ ድንገት ትዝ ሲላት የምታደርገው ነገር ነው፡፡ ይህን ጊዜ ባሏ ሳይሆን እሷ ዶክተር የሆነች ይመስላታል መሰል ስለ ህመሙ ላጫወታት የሰፈር ሰውና ጓደኛዋ መድሀኒት ታዝለታለች፡፡ በደፈናው ሆዴን ይቆርጠኛል ላላት “ሲፕሮ”፣ ጨጓራዬን ያመኛል ለሚላት “ኦሜፕራዞል” እንዲወስድበት ትመክረዋለች፡፡ …

ጎበዝ፤ የመረመራችሁ ዶክተር ያዘዘላችሁን መድሀኒት ትቶ ያልተባለውን ሌላ መድሀኒት የሚሰጣችሁ የመድሀኒት ቤት ባለሙያ ባለበት ሀገር የአንድ ዶክተር ሚስትን ምክር ሰምቶ መድሀኒት መውሰድ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት አስባችሁታል?…

ለማንኛውም ያሰብነውን መሆን ባንችል እንኳ ራሳችንን መሆን የግድ ነው፡፡ ራሳችንን ከሆንን ቢዘገይም ያሰብነውን ነገር ልናሳካ እንችላለን፡፡ አልያም በሆነው ነገር ደስተኞች እንሆናለን፡፡ ከዚያ በዘለለ ግን ለአንድ ነገር የሚያበቃ ምንም ነገር ሳይኖረን ያንን ነገር ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ ማለቱ የሥጋ ቤት ጋዋን ስለለበስን ብቻ ልጄ ዶክተር ነውና እኔም መርፌ ካልወጋሁ ወደ ማለት እንዳያመራ መጠንቀቅ ያሻል፡፡