“የጎደለኝ ነገር የለም” – ወጣት ከይረዲን ካሱ

በአንዱዓለም ሰለሞን

በዚህች ምድር ላይ በህይወት ስንኖር የተለያዩ አጋጣሚዎች ይቀርቡናል፡፡ አጋጣሚዎቹ እንደ ሁኔታው በህይወታችን ላይ በጎም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረው ያልፋሉ፡፡ አሉታዊውን  ተጽእኖ ተቋቁሞ ለማለፍ ታላቅ ትዕግስት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ እውነታውን ተቀብሎ፣ ችግሩን ከማሰብ ይልቅ መፍትሔው ላይ ማተኮር ያሻል፡፡

በባስኬቶ ዞን፣ ዛባ ኤላ በተባለ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ወጣት ከይረዲን ካሱ የህይወት ተሞክሮ የሚነግረንም ይህንኑ እውነታ ነው፡-

ወጣት ከይረዲን በልጅነቱ እግሩ ላይ የወጣበትን እባጭ በባህላዊ ህክምና ለማከም የተደረገው ጥረት ሌላ መዘዝ አመጣበት። ግራ እግሩ ለመንቀሳቀስ የማይችል ሆነና ለአካል ጉዳት ተዳረገ፡፡

ያላሰቡት ክፉ አጋጣሚ የገጠማቸው ወላጆቹ በሆነው ነገር ቢያዝኑም የሚቀየር ነገር አልነበረም፡፡ የተሞከረለት የባህል ህክምናም ውጤት ማምጣት አልቻለም፡፡ ወጣቱ ነፍስ ሲያውቅና ያጋጠመውን ጉዳት ሲረዳ ሀዘን ቢሰማውም ራሱን አሳምኖ የሆነውን ነገር ለመቀበል አልተቸገረም፡፡ ራሱን አረጋግቶ ስለሆነው ነገር በማሰብ ከመቆጨት ይልቅ መፍትሄውን ማሰብ ላይ ትኩረት ማድረጉን ይገልጻል፡-

“በልጅነቴ ከሰፈር ልጆች ጋር እንደልብ እየተሯሯጥኩ ባለመጫወቴ ይሰማኝ ነበር፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ጓደኞቼ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ሳይ ይከፋኝ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ለመሄድ ታላቅ ጉጉት ነበረኝ፡፡ ይህም ከእነሱ ጋር ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እንደምችል ራሴን እንዳሳምን አደረገኝ” በማለት በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ያስታውሳል፡፡

ትምህርት ቤት ሲገባ ሌላ ፈተና ገጠመው፡፡ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር በመሆን ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ የግድ አንድ ወንዝ ማቋረጥ ነበረባቸው፡፡ ይህ በየእለቱ የሚከውነው አስቸጋሪ ሁኔታ ቢሆንም ተስፋ ሊያስቆርጠው ግን አልቻለም፡፡ መጀመሪያ ላይ ጓደኞቹ እየተሸከሙ እያሻገሩት፣ ኋላ ላይ ደግሞ ራሱ እንዲሻገር አለማምደውት ችግሩን ተወጣው፡፡ 

ከእጁ የማይለያትን በትሩን በመመርኮዝና በጓደኞቹ ድጋፍ ታግዞ በየእለቱ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት እየተመላለሰ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማረ፡፡ መምህራኖቹም ጥረቱን በማየት ያበረታቱት ነበር፡፡ ውጤቱም በዚያው ልክ፡-

“ትምህርት ቤት በመግባቴ ደስተኛ ነበርኩ። ሰርቼ መኖር እንደምችል እንዳስብና በራስ መተማመን እንዲኖረኝ አድርጎኛል። ፈጣንና ቀልጣፋ ስለነበርኩ መምህራን ይወዱኛል፤ ያበረታቱኛል፡፡ ውጤቴም ጥሩ ነበር፡፡ እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ ከአራተኛ ደረጃ አልፌ አላውቅም፡፡ ከትምህርቱ ባሻገር በሚኒ ሚዲያ እና በአንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ድራማ በመስራት ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡”

እርሱን ጨምሮ አምስት ልጆችን ያፈሩት ወላጆቹ ገቢያቸው ለኑሯቸው በቂ አልነበረም። ይህ ደግሞ የመጀመሪያ ልጅ ለሆነው ከይረዲን በዝምታ የሚታለፍ ነገር አልሆነም። የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ከትምህርቱ ጎን ለጎን እዛው ትምህርት ቤት ውስጥ ቆሎ መሸጥ ጀመረ፡፡ ቆሎ እየሸጠ የሚያገኘው ገቢ ቤተሰቦቹን መደገፍ ቢያስችለውም በትምህርቱ ላይ ተጽዕኖ ማምጣቱ አልቀረም። ያም ሆኖ በተቻለው መጠን የትምህርቱን ጊዜ በማይነካ መልኩ የቆሎ ንግዱን ከትምህርት ቤት ወደ ገበያ አዘዋወረው፡፡

የዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ትምህርቱን የተማረው በላስካ ከተማ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ሌላ ሥራ እንዲጀምር ምክንያት ሆነው፡፡ የቆሎውን ንግድ ትቶ ሎተሪ ማዞር ጀመረ፡፡ በዚህ ወቅትም ከትምህርቱ ይልቅ ትኩረቱን ሥራው ላይ ያደረገበት ነበር፡፡ ከሥራው ባሻገር የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ትዳር መመስረቱ የበለጠ ሀላፊነት እንዲሰማውና ሥራው ላይ የበለጠ እንዲያተኩር አደረገው፡፡ የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሙሉ ትኩረቱ ሥራው ላይ ሆነ፡፡

ሎተሪ ማዞሩን በመተው ወደ ትውልድ አካባቢው በመመለስ ሻይ ቤት ከፍቶ ይሰራ ጀመር፡፡ የሻይ ቤቱ ገበያ ሲቀዘቅዝ ደግሞ ዳግም ወደ ላስካ ተመልሶ ሎተሪውን ማዞር ጀመረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወደ ዶሮ ንግድ ገባ። ይህ አላዋጣ ሲለው ደግሞ ገበያ ከብት ተራ ውስጥ ተገኘ፡፡ በዚህ የንግድ ሥራ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ከፈተ። በመጨረሻም አሁን የሚሰራውን የእህል ንግድ ጀመረ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እያንዳንዱን ሥራ በሚሰራበት ወቅትና በሚያልፈው ውጣ ውረድ ብዙ ልምድ ማግኘቱንና ውጤታማ መሆኑን ይናገራል፡-

“ኑሮን ለማሸነፍ የተለያዩ ሥራዎችን ሰርቻለሁ፡፡ አንደኛው ካልተሳካልኝ ሌላ እጀምራለሁ እንጂ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ሥራዬ ከብዙ ሰዎች ጋር አስተዋውቆኛል፡፡ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመስራቴ ጠቃሚ የህይወት ልምድ አግኝቻለሁ፡፡ ሰዎችም በስራዬ ያከብሩኛል። ብዙዎችም እኔን በማየት ስራ ጀምረዋል። እኔ ስራ ያስጀመርኳቸውና አብረውኝ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችም አሉ፡፡ አሁን የተሻለ ገቢ አገኛለሁ፡፡ ከራሴ አልፌ ወላጆቼንም እረዳለሁ፡፡ እነሱም እኔን በዚህ መልኩ ለማየት በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው”

ወጣት ከይረዲን አሁን በሚመራው ህይወት ደስተኛ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይህ የሆነው ግን እንዲሁ በዋዛ እንዳልሆነና ተስፋ ሳይቆርጥ ጥረት ማድረጉ እንደጠቀመው ይገልጻል፡፡ ጥረቱን አይተው ያበረታቱት የነበሩትንም አልዘነጋም፡-

“አሁን ባለው ሁኔታ ደስተኛ ነኝ፡፡ ቤት ንብረት አፍርቼ አራት ልጆችን ወልጃለሁ፡፡ በሥራዬ የማገኘው ገቢ ጥሩ ኑሮ እንድመራ አድርጐኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ ነገ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝልኝ ሥራ ለመስራት እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ስራውን እየለመድኩት ነው። እዚህ ደረጃ ለመድረስ ያጋጠሙኝን ችግሮች በትዕግስት ማለፌ ብርታት ሆኖኛል። ከምንም በላይ ደግሞ ራሴን እንደ አካል ጉዳተኛ አለመቁጠሬ ጠቅሞኛል፡፡ የጎደለኝ ነገር የለም። ከሰው ከመጠበቅ ይልቅ በተቻለኝ መጠን ራሴን ችዬ ለመማርና ለመስራት ያደረኩት ጥረት ለዚህ አብቅቶኛል፦

“አንዳንዴ ሙሉ አካል ይዘው የሚለምኑና የሰው ንብረት የሚሰርቁ ሰዎችን ስመለከት እገረማለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች የጎደላቸው ነገር ሰርተው ለመለወጥ እንደሚችሉ አለማመናቸው ነው፡፡ ሰው ራሱን ካሰነፈ ምንም ነገር መስራት አይችልም፡፡ ሁል ጊዜም የሰው እጅ ጠባቂ ነው የሚሆነው፡፡ እኔን የጠቀመኝ መስራት እንደምችል ማመኔ ነው። እዚህ ከተማ ውስጥ ሁሉም ያውቀኛል፡፡ ሥራዬም አስከብሮኛል”

አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ በሰጠው አስተያየት፡-

“አሁን ላይ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት እየተቀየረ ቢሆንም በመንግስት ረገድ ግን አሁንም ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለምሳሌ እኔ ምንም የተደረገልኝ ድጋፍ የለም፡፡ እዚህ የደረስኩት በጥረቴ ችግሮችን ተቋቁሜ ነው፡፡ ያም ሆኖ በየአካባቢው ተደብቀው ያሉና ድጋፍ የሚያሻቸው አካል ጉዳተኞች መኖራቸው ሊታሰብ ይገባል” ብሏል፡፡