ማንቸስተር ሲቲ በአዲሱ የውድድር ዓመት 2ኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናገደ
በ3ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከሜዳው ውጪ ብራይተንን የገጠመው ማንቸስተር ሲቲ ከመምራት ተነስቶ 2ለ1 በመረታቱ በአዲሱ የውድድር ዓመት 2ኛ ተከታታይ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
በአሜክስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኤርሊንግ ሀላንድ በ34ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ ማንቸስተር ሲቲ እየመራ ወደ ዕረፍት እንዲያቀና አስችሎ ነበር።
ሆኖም ግን በ2ኛው አጋማሽ ጄምስ ሚልነር በፍፁም ቅጣት ምት እና ግሩዳ ባስቆጠሯቸው ግቦች ብራይተን ከመመራት ተነስቶ ጨዋታውን በማሸነፍ ሙሉ 3 ነጥብ ይዞ ከሜዳ ወቷል።
ኤርሊንግ ሃላንድ በማንቸስተር ሲቲ መለያ 100ኛ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታውን አከናውኗል።
ኖርዊያዊው አጥቂ በመጀሪያዎቹ 100 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች 88 ጎሎችን በማስቆጠር በሊጉ ታሪክ ቀዳሚው ተጫዋች ሆኗል።
ስፔናዊው አማካይ ሮድሪ ባለፈው የውድድር ዓመት በፕሪሚዬር ሊጉ ከአርሰናል ጋር ሲጫወት ካጋጠመው እና ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ካራቀው ጉዳት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ጨዋታውን ጀምሯል።
በሌላ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ኖቲንግሃም ፎረስትን የገጠመው ዌስትሃም ዩናይትድ 3ለ0 በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።
ፕሪሚዬር ሊጉ መካሄዱን ሲቀጥል ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሊቨርፑል ከአርሰናል በአንፊልድሮድ ይጫወታሉ።
እንዲሁም ምሽት 3 ሰዓት ላይ ደግሞ በቪላ ፓርክ አስቶንቪላ ክርስቲያል ፓላስን የሚያስተናግድ ይሆነናል።
ዘጋቢ፦ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል
ጄሚ ቫርዲ ወደ ጣሊያን ሴሪኣ ሊያቀና ነው
ሊቨርፑል ከአርሰናል ከሰዓታት በኋላ ወሳኝ ግጥሚያ ያካሂዳሉ