ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል
ግብ ጠባቂዎቹ በሚሰሩት ስህተት ግብ በማስተናገድ ተጋላጭ የሆነው ማንቸስተር ዩናይትድ ሊጠናቀቅ አንድ ቀን ብቻ በቀረው የክረምቱ የዝውውር መስኮት ሁነኛ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ቀያይ ሴይጣኖቹ ያለባቸውን የግብ ጠባቂ ክፍተት ለመድፈን ሁለት ግብ ጠባቂዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ተነግሯል።
የአሰልጣኝ ሩበን አሞሪሙ ቡድን ቤልጄማዊውን ግብ ጠባቂ ሴን ላመንስን በዋናነት ኢላማው ማድረጉን ዘ ቴሌግራፍ አስነብቧል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የ23 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ከሚጫወትበት ክለብ ሮያል አንትወርፕ ጋር ንግግር ማድረግ ከጀመረ የሰነበተ ቢሆን አሁን ላይ አዲስ የተሻሻለ የዝውውር ሒሳብ ማቅረቡ ተሰምቷል።
የዚህን የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ድሉን በትናንትናው ዕለት ያስመዘገበው ማንቸስተር ዩናይትድ ለግብ ጠባቂው ዝውውር ከ20 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ አቅርቧል ተብሏል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከሴነ ላመንስ ጋር በግል ጉዳይ ከስምምነት ላይ ሳይደርስ የቱርኩ ክለብ ጋላታሳራይ ሌላኛው ፈላጊ ክለብ ሆኖ ብቅ ማለቱ ቀያይ ሰይጣኖችን ያሳሰባቸው ይመስላል።
የዚህ ውድድር ዓመት አጀማመር ያላማረለት ማንቸስተር ዩናይትድ የሰነ ላመንስ ዝውውር ካልተሳካ ፊቱን በድጋሚ ወደ አስቶንቪላው ግብ ጨባቂ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ ለማዞር መወሰኑ ተዘግቧል።
አርጀንቲናዊው ግብ ጠባቂ አስቶንቪላን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ከጥር ወር አንስቶ ስሙ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር እየተነሳ ይገኛል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የ32 ዓመቱን ግብ ጠባቂ በውሰት ለማስፈረም በሀምሌ ወር ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ መደረጉ አይዘነጋም።
ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝን ለማስፈረም ወደ ኋላ ያላለው ማንቸስተር ዩናይትድ ጄደን ሳንቾን የዝውውሩ አካል አድርጎ በማቅረብ ግብ ጠባቂውን ለማስፈረም ጥረት ማድረግ መጀመሩን የዘ አትሌቲክ መረጃ አመላክቷል።
በዚህ ክረምት ሆላንዳዊውን ግብ ጠባቂ ማርኮ ቢዞት በአዲስ መልክ ወደ ስብስቡ የቀላቀለው አስቶንቪላ ከማንቸስተር ዩናይትድ የቀረበለትን ጥያቄ ይቀበላል ወይ የሚለውን ጥያቄ ቀሪ ሰዓታት ምላሽ የሚሰጡን ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ማንቸስተር ሲቲ በአዲሱ የውድድር ዓመት 2ኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናገደ
ጄሚ ቫርዲ ወደ ጣሊያን ሴሪኣ ሊያቀና ነው
ሊቨርፑል ከአርሰናል ከሰዓታት በኋላ ወሳኝ ግጥሚያ ያካሂዳሉ