“ሠራተኞቹ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ህዝቡ ቤተሰብ ሆኖ እየደገፋቸው ነው” – አቶ ጌታሁን ካሳሁን
በመለሰች ዘለቀ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ጌታሁን ካሳሁን ይባላሉ፡፡ የሳጃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ናቸው፡፡ ስለከተማዋ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፦
ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ጌታሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- በቅድሚያ ስለትውልድና እድገትዎ በማንሳት እንጀምር?
አቶ ጌታሁን፡- የተወልዱኩት በየም ዞን ሾሾ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በተወለድኩበት አካባቢ ነው የተማርኩት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በጅማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ፡፡ የመጀመሪያ ድግሪዬን በጅማ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት፣ የሁለተኛ ድግሪዬን ደግሞ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በቋሚ ንብረት ግመታ /property evaluation/ ትምህርት ዘርፍ ተከታትያለሁ፡፡
በገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዘርፍ ላለፉት 15 አመታት ስሰራ ቆይቻለሁ። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የሳጃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡ በአጠቃላይ በመንግስት ስራ ወደ 19 አመታት ቆይቻለሁ፡፡
ንጋት፡- የሳጃ ከተማ አጠቃላይ ገጽታ ምን ይመስላል?
አቶ ጌታሁን፡- ሳጃ ከተማ ከሀዋሳ በ355 ኪሎ ሜትር፣ ከአዲስ አበባ ደግሞ በ243 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት፡፡ ከተማዋ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ከክልሉ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የምትገኝ ሲሆን በመሬት ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ ከ1 ሺህ 870 እስከ 1 ሺህ 920 ሜትር ከፍታ መካከል ትገኛለች፡፡
ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት ሲሆን ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 288 ሚሊ ሜትር ዓመታዊ ዝናብ ታገኛለች፡፡ የሙቀት መጠኗ ከ15 – 27/ በአማካይ 21/ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲኖራት በ1ሺህ 590 ሄክታር በላይ የቆዳ ስፋት የተካለለች ናት፡፡
በከተማዋ አሁን ላይ በአብዛኛው የየም ብሔረሰብ የሚኖሩ ሲሆን በተጨማሪም ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የተወጣጡ ማህበረሰቦች በፍቅር እና በመቻቻል የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡ ከተማዋ ከአዲስ አበባ ጅማ በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ከጅማ ከተማ በስተደቡብ ምስራቅ 112 ኪሎ ሜትር እና ከወልቂጤ ከተማ በ88 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
ቀደም ሲል ሳጃ ላፍቴን በሚባል የገጠር ቀበሌ የነበረች ማዘጋጃ ናት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ራሷን እያሻሻለች በ2000 ዓ.ም በማዘጋጃ ቤትነት ደረጃ በፈርጅ 4 ተደራጅታለች፡፡
ሳጃ በ2003 ዓ/ም በህዝብ ውሳኔ የቀድሞ የየም ልዩ ወረዳ ዋና ከተማ በመሆን በማዘጋጃ ስትተዳደር ቆይታ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከተደራጁ አዳዲስ ፈርጀ ሶስት ከተማ አስተዳደሮች ጋር አድጋ በአሁኑ ሰዓት የተሻለ መነቃቃት እያሳየች ትገኛለች፡፡
አራት የመውጫና የመግቢያ የንግድ በሮች ያሏት ሳጃ ጠንካራ የህዝቦች አብሮ የመኖር፣ የመረዳዳትና የመቻቻል እሴት የሚታይባት ናት፡፡ እንዲሁም የተረጋጋ ሰላምና ጸጥታ፣ የተለያዩ እምነቶች በነፃነት የሚኖሩባት ሲሆን ነፋሻማ የአየር ንብረቷና የህዝቦቿ እንግዳ ተቀባይነት ባህልም መገለጫዎቿ ናቸው፡፡ የህዝብ ብዛቷ ደግሞ ከ10 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡
በ3 ቀጠናዎች፣ በ11 ሰፈሮች እና በአንድ ቀበሌ የተዋቀረች ናት፡፡ ከተማዋ ባንኮችና የገንዘብ ተቋማት በብዛት ይገኙባታል፡፡
ከአዲስ አበባ እስከ ጅማ አማካይ በሆነ ቦታ ላይ ያለችው ሳጆ በብዙ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች የተወደደችና ሰላማዊ የሆነች ከተማ ናት፡፡ ላለፉት አመታት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ተፈጥረው በነበሩ የተለያዩ የጸጥታ ችግሮች ሳጃ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ሳይፈጠር የቆየችም ናት፡፡
ንጋት፡- የከተማዋ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ጌታሁን፡- ከመሰረተ ልማት አንጻር ማዘጋጃ በነበረበት ጊዜ የተወሰኑ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ነበሩ። አሁን ግን ከ2014/15 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ከተማ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ የመንገድ ከፈታ እና ጠጠር የማልበስ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከውሃ ተደራሽነት ረገድም ያለው የንጹህ የመጠጥ ውሃ በቂ ባይሆንም በፈረቃ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
ከመብራት ተደራሽነት አንጻርም ቀደም ሲል የመንገድ ዳር መብራት ያልነበረባት ከተማዋ፣ ዘንድሮ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የመንገድ ዳር መብራት አስገብተናል፡፡
ንጋት፡- ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ጽዱና ውብ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትን ቢጠቅሱልን?
አቶ ጌታሁን፡- ጽዱና ውብ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማን ለመመስረት ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን። በተለይም የጽዳትና ውበት ስራን እንደ ክልል በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ማህበራትን አደራጅተን አሰማርተናል። ነዋሪው በሚያመነጨው ቆሻሻ ልክ ገቢ ማስገባት ስላለበት ከውሃ ቆጣሪ ጋር አገናኝተን በየወሩ የውሃ ፍጆታ ሲከፍሉ ለቆሻሻውም እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው። ከተሰበሰበው ገቢ ለማህበራት ወርሃዊ ክፍያ እየከፈልን የጽዳትና ውበት ስራም በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ከዚያም ባሻገር ከተማዋን ውብ ለማድረግ የመንገድ ዳር አበባዎችንና የውበት ዛፎችን ጭምር ለማስተከል እንቅስቃሴ እያደረግን እንገኛለን፡፡ አጠቃላይ የከተማዋን ህዝብ በማሳተፍ በየሳምንቱ ቅዳሜ የጽዳት ዘመቻ ይካሄዳል፡፡ በወር አንድ ጊዜ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች የጽዳት ዘመቻ ያካሂዳሉ፡፡ የጽዳት ተግባርን ባህል ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይት ይካሄዳል፡፡ ሎጆችና መዝናኛዎችም ያሉን ሲሆን በአካባቢዎቹ የመንገድና የመብራት መሰረተ ልማቶች የማሟላት ስራ እየሰራን እንገኛለን፡፡
ንጋት፡- ከተማዋን ለኢንቨስትመንትና ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ ምን ስራዎች ተከናውነዋል?
አቶ ጌታሁን፡- የሳጃ ከተማ ለንግድና ኢንቨስትመንት አቅም ያላት ናት፡፡ ለኑሮ ምቹና አየሯ ተስማሚ ነው፡፡ ህዝቡ የሚታወቀው በጠንካራ ሰራተኝነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጥሩ የሆነ አምራች የሰው ሀይል ያለበት ነው፡፡ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ደህንነት የሚጠብቅባት ከተማ ናት፡፡ ይህም በመሆኑ ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ እየሆነች ነው፡፡
እስካሁን 39 ባለሀብቶች በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተዋል፡፡ አሁን ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችም እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ባለሀብቶቹ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ከመጡ ከተማ አስተዳደሩ ፈጣን እና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነው።
ንጋት፡- ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ጌታሁን፡- ልዩ ትኩረት ሰጥተን ከምንሰራባቸው ስራዎች መካከል የገቢ አሰባሰብ፣ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአመቱ ለ1 ሺህ 440 ወጣቶች ልየታ ተደርጎ ለ1 ሺህ 85 ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዟል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ወደ 228 ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች በቋሚነት የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ እንዲሁም በበጀት አመቱ ወደ 1ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት በመመደብ ሼድ በመገንባት የስራ ዕድል እየፈጠርን እንገኛለን፡፡
በከተማ ግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎችም ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል፡፡ እንደ አስተባባሪም እንደ ካቢኔ የስራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይን በልዩ ሁኔታ እየመራን እንገኛለን፡፡ በቀጣይም የያዝናቸው ሰፋፊ ዕቅዶች አሉ። እነዚያን ካሳካን የስራ አጥነትን ችግር በተወሰነ ደረጃ መቅረፍ እንችላለን፡፡
ንጋት፡- የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተደራሽነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ጌታሁን፡- በከተማችን የተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ፡፡ በመንግስትም የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ሆነዋል፡፡ ተማሪዎችም በቅርበት የመማር ዕድሉን አግኝተዋል፡፡
ከጤና ተቋማት አንጻር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና የህዝብ መድሃኒት ቤቶችም በልዩ ሁኔታ በጀት ተይዞላቸው በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
ንጋት፡- በሳጃ ከተማ ላይ መቀመጫ ላደረጉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቢሮዎች ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር ረገድ ምን ስራዎች ተሰርተዋል?
አቶ ጌታሁን፡- የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሲመሰረት በልዩ ሁኔታ የቅድመ ዝግጅት ስራ ሰርተን ነው የጠበቅነው፡፡ ከዚህ አንጻር የዞኑ መንግስት እና የከተማ አስተዳደር ቢሯቸውን በመልቀቅ ለክልሉ ተቋማት በነጻ እንዲጠቀሙ አድርጓል፡፡ ሰራተኞችም በተመጣጣኝ ዋጋ ኪራይ ቤት ተመቻችቶላቸዋል፡፡ የበላይ ኃላፊዎችም የተሻለ መኖሪያ ቤት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥረናል፡፡
መቀመጫቸውን በከተማው ላደረጉ ቢሮዎች ለግንባታ የሚሆን ቦታ እያዘጋጀን እንገኛለን፡፡ ለዚህም የክልሉ መንግስት በጀት መድቦ እየሰራ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ሰራተኞች በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት የሚገነቡበት ቦታ እያዘጋጀን ሲሆን በቅርብ ጊዜ ርክክብ እንፈጽማለን። ከዞኑ መንግስትና ከከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ጋር ተነጋግረን ውሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡
ሰራተኞችን ቢሯቸው ድረስ በመሄድ የሚቸግራቸውን በመጠየቅ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሞክረናል። ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ህዝቡም አብሮ ቤተሰብ ሆኖ እያስተናገዳቸው ይገኛል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሰባት ከተሞች ላይ መቀመጫውን አድርጓል። ከነዚህም ውስጥ ሳጃ አንዷ ነች፡፡ በዞኑ የተመደቡ የብሔረሰቦች ምክር ቤት፣ ባህልና ቱሪዝም እና የአመራር አካዳሚ ቢሮዎች ህዝቡ ቅድሚያ ሰጥቶ ነው የተቀበላቸው፡፡
ንጋት፡- የክልሉ ወይም የዞኑ መዋቅር ምላሽ ካገኘ ወዲህ ከተማዋ ያሳየችው መነቃቃት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጌታሁን፡- ሳጃ ከተማ የየም ዞንና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሶስት ቢሮዎች መቀመጫ ሆናለች፡፡ ከዚህም የተነሳ በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ የዚህም ማሳያ ብዙ ባለሀብቶች ከአዲስ አበባ እና ከጅማ ከተለያዩ ቦታዎች የኢንቨስትመንት ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ ሳጃ ሰላማዊ ቀጠና በመሆኗ መኖሪያ ቤት ገንብቶ ለመኖር ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
ከሰላም አንጻር ሳጃ ተመራጭ በመሆኗ ትልልቅ የጭነት መኪናዎች ማደሪያቸውን ያደርጋሉ፡፡ በከተማ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡
ንጋት፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
አቶ ጌታሁን፡- የከተማዋ ነዋሪዎች የተፈጠረውን መነቃቃት አጠናክሮ ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን መቆም አለባቸው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ትልቁ ችግር ከውሃ ጋር የተያያዘ ነው። ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናቶች ሲደረጉ የሚጠይቀው በጀት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ከዞን እና ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ ስለሆነ የክልሉ መንግስት እና የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ድጋፋቸውን ማድረግ መቻል አለባቸው የሚል መልዕክት አለኝ፡፡
ንጋት፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ጌታሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“ጤናችን በአመጋገባችን ይወሰናል”-ዶክተር ዘላለም ታፈሰ
አዲስ ህይወትን በአሜሪካ
ጥቂት ስለ በርሊን ማራቶን