ወጣቶች ከጠባቂነት አመለካከት ተላቀው ችግር ፈቺ የስራ መስክ በመፍጠር ከራሳቸው አልፎ አገርን ለማሻገር መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ

ወጣቶች ከጠባቂነት አመለካከት ተላቀው ችግር ፈቺ የስራ መስክ በመፍጠር ከራሳቸው አልፎ አገርን ለማሻገር መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጣቶች ከጠባቂነት አመለካከት ተላቀው ችግር ፈቺ የስራ መስክ በመፍጠር ከራሳቸው አልፎ አገርን ለማሻገር መስራት እንዳለባቸው አሳሰበ።

ቢሮው “በተሳትፎ ድህነት ቅነሳ” ከተሰኘው መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር “የስራ ፈጣሪነት እና ተነሳሽነት” በሚል መሪ ቃል ለወጣቶች በሆሳዕና ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ ወጣቶች ዘመኑ የሰጠውን ቴክኖሎጂ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወጣትነታቸውን ለልማትና ለመልካም ተግባር ማዋል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአካባቢያቸውን ጸጋዎች ለይቶ በማወቅ ውጤታማ ስራዎችን ፈጥሮ ለመስራት ማቀድ እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ ጌታቸው ወጣቶች ከጠባቂነት አመለካከት ተላቀው ችግር ፈቺ የስራ መስክ በመፍጠር ከራሳቸው አልፎ አገርን ለማሻገር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

በተሳትፎ ድህነት ቅነሳ ድርጅት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ደምሴ ሎብዱኖ በበኩላቸው በረቂቅ ክህሎት ወጣቶችን ማብቃት የድርጅቱ ዋና ተግባር እንደሆነ ጠቁመው ውጥኑ ግብ እንዲመታ በስልጠና የማብቃት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዕለቱም ከ800 በላይ ወጣቶች ከሆሳዕና ከተማ አስተዳደር እና ሌሞ ወረዳ በማሳተፍ የተሰጠው ስልጠና የዚሁ አካል እንደሆነ ያብራሩት አቶ ደምሴ÷ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚመጣው የሚያስቡ አዕምሮዎች፣ የሚያልሙ ልቦችና የሚሰሩ እጆች ሲደመሩ እንደሆነ በመረዳት መተግበር እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ወጣቱ የሚገጥመውን ኢኮኖሚያዊ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በይቻላል መንፈስ መጋፈጥ እንዳለበት ያስገነዘቡት የድርጅቱ አስተባባሪ÷ በችግር ውስጥ አልፎ ስመ ጥር መሆን እንደሚቻል ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ተዋቂ ግለሰቦችን ሕይወት ታሪክ በማቅረብ አስረድተዋል።

በዕለቱ ”በረቂቅ ክህሎት ወጣቶችን ማብቃት” በሚል ርዕስ በተሰጠው ስልጠና ተሳታፊ የነበሩ አንዳንድ ወጣቶች ስልጠናውም ራሳቸውንም በደንብ እንዲያዩ እንደረዳቸው ገልጸው በየአከባቢያቸው ያለውን ጸጋ በመጠቀም ስራ ፈጥሮ ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን