“ሁሉም ሰው በማግኘት እና በማጣት ውስጥ ያልፋል” – ወ/ሮ ወርቄ ኮሌ
በአስፋው አማረ
ህይወት በበርካታ ውጣ ውረዶች የተሞላች ናት፡፡ አንዳንዴ ማጣትና ማግኘት፣ ሀዘንና ደስታ፣ ከፍታና ዝቅታ፣ መውደቅና መነሳት እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎችን ሊያካትት ይችላል፡፡ በዚህ ሁሉ ትልቁና ዋናው ነገር ጠንክረን በመስራት የሚገጥሙንን ነገሮች በመጋፈጥ ወደ ፊት መቀጠል ነው፡፡
በንጋት ጋዜጣ የእቱ መለኛ አምዳችን እንስት ያሳለፉት የህይወት ውጣውረድ ለሌሎች ተሞክሮ ይሆናል ስንል ልናጋራችሁ ወደናል፡፡ ወ/ሮ ወርቄ ኮሌ ይባላሉ የተወለዱት በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳ በኡገባይኖ ቀበሌ ነው፡፡ በማህበረሰቡ ባህል መሰረት አንዲት ሴት የምታገባው ከብቶችን የዘለለ ወንድን ነው፡፡
ከብት የዘለለ ወንድ እስከ ሶስት ሚስቶችን ማግባት ይችላል፡፡ እሳቸውም በባህላቸው መሰረት ከብቶችን ለዘለለ ወንድ ታጩ፡፡ ነገር ግን ባለቤታቸው አለመታደል ሆኖ ከእሳቸው በፊት ሁለት ሚስቶች ነበሯቸው፡፡
በብሔረሰቡ ባህል መሰረት ለወንድ ልጅ ሚስት የሚመርጡለት የሙሽራው ቤተሰቦች ናቸው፡፡ በአንፃሩ አንድ ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ሴት የመጣላትን እጮኛ ያለምንም ማንገራገር መቀበል የውዴታ ግዴታዋ ነው። በቤተሰብ አማካይነት የመጣውን ትዳር ለማግባትም ትገደዳለች፡፡
በዚህ ሂደት መሰረት ወ/ሮ ወርቄ የመጣላቸውን ባል በመቀበል ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ኑሯቸውን በሐመር ወረዳ ዲመካ ከተማ አደረጉ፡፡ ከተማ ከገቡ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ንግድ ዓለም ተቀላቀሉ፡፡ ከንግድ በሚያገኙት ትርፍ በማጠራቀም በ1 ሺህ ብር ሶስት መቶ ካሬ ላይ ያረፈውን መኖሪያ ቤት ገዙ፡፡
ሶስተኛ ሚስት ሆኖ መቀጠል ስለከበዳቸው ከባለቤታቸው ጋር አለመግባባት መፈጠር ጀመረ፡፡ በዚህ ምክንያት ከትዳር አጋራቸው ጋር ለመለያየት ተገደዱ፡፡ ይነግዱ የነበረው በአካባቢው በጣም ተወዳጅ የሆነውን ሹፉሮ(የቡና ገለባ/ገለፈት) ነበር፡፡ ይህንን ሥራ በስፋት በመስራት ከሚያገኙትም ትርፍ በቀን 10 ብር እቁብ ይጥሉ ጀመሩ፡፡
ከመሰረቱት ትዳር አንድ ልጅ ያፈሩት ወ/ሮ ወርቄ ልጃቸውን በአግባቡ ከማሳደግ ጎን ለጎን ሥራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ ሹፉሮ በመነገድ በቀን አስር ብር በሳምንት ደግሞ ሃምሳ ብር እቁብ በመጣል ሌላ የህይወት መስመር ወጠኑ፡፡ ይህን ሥራ ሲሰሩ የሚደግፋቸው አልነበረምና የሚደግፋቸው አጋር ፍለጋ ሲሉ ሌላ ትዳር መሰረቱ፡፡ ከትዳር አጋራቸው ሁለት መንታ ልጆችን አፈሩ፡፡ ልጆቻቸውን ከዚሁ በሚያገኙት ገቢ እንደሚያስተዳድሩ የተናገሩት ወ/ሮ ወርቄ፤ የመጀመሪያ ልጃቸው እስከ አምስተኛ ክፍል ካስተማሩ በኋለላ አባቱ ጋር ሄዶ ትምህርቱን የቀጠለ ሲሆን ሁለቱን መንታ ልጆች እሳቸው እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡
ይሁንና የአዲሱ ትዳር መሰረትም ከጊዜ በኋላ በመጣ የባህሪ ለውጥ በመናጋቱ በፍቺ ተጠናቀቀ፡፡ ባል ሥራውን አቁሞ መጠጥ መጠጣት እኔንና ልጆቼን መረበሽ መጀመሩ የፊቺ ምክንያት ነው ሲሉ በምሬት ያወሳሉ፡፡
መንታ ልጆቻችሁ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? ስንል መጠየቃችን አልቀረም፦ “ልጆቼ ወንድና ሴት ናቸው። ሴቷ አርባ ምንጭ ከተማ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ስትሆን ወንዱ ደግሞ የግል ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ሁለቱንም የሚያስፈልጋቸውን በማገዝ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰው የማየት ህልም አለኝ፡፡ ለዚህም ደግሞ በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ከጎናቸው ነኝ ብለዋል፡፡
ወደ ንግድ ዓለም በስፋት የገቡበትን አጋጣሚ እንዲህ ሲሉ አጫውተውናል፦“ሥራ እየሰራሁ የራሴን ቤት ከገዛው በኋላ የተሰማኝ ስሜት ይበልጥ አነሳሳኝ፡፡ በደንብ ብሰራ ከዚህ የበለጠ ማድረግ እችላለሁ በማለት ንግዱን ለማሳደግ ቁጠባ መቆጠብ ጀመርኩ። በቆጠብኩትም ብር ላሜራ ሱቅ ከፍቼ ሥራውን አስፋፍቼ መስራት ጀመርኩ፡፡
“መኖሪያ ቤቴ ጎጆ ነበር፡፡ ይህን ቤት ቆርቆሮ ለማድረግ እንጨት፣ ሚስማር፣ ጭድ፣ ድንጋይ እና ሌሎች ቤት ለመስራት አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አሟላሁኝ፡፡ በመቀጠል ለአናጺ የሚከፈል ብር በማዘጋጀት ጎጆ ቤቴን በማፍረስ ዘመናዊ ቤት ገነባሁኝ፡፡ ከዚህ በኋላ የነበረው የሥራ ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ እየተስፋፋ መጣ፡፡ ሌላ ወደ አራት ተጨማሪ ሱቆችን ከፈትኩኝ፡፡ እነዚህ ሱቆችም የሹፉሮና ቦቆሎ መሸጫ ሱቆች ናቸው። ቦቆሎ ከተለያዩ አካባቢዎች በማስመጣት ማከፋፈል ጀመርኩ፡፡ ሹፉሮውን ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከወላይታ፣ ከይርጋ ጨፌ አስመጣለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ሥራዎች ከአቅሜ በላይ እየሆኑ መጡ፡፡
“በዚህ መሃል ትዳር መመስረት እንዳለብኝና ሥራውን የሚያግዘኝ አጋር ፈለኩኝ፡፡ በአንድ አጋጣሚ አንድ ሰው ተዋወኩኝ፡፡ ይህም ሰው በጣም ጥሩ ስለነበረ ትውውቃችን ውሎ እያደረ ወደ ትዳር አመራ። ሰማኒያ(ህጋዊ) በመፈራረም ትዳር መስርተን በአንድ ጣሪያ ስር መኖር ጀመርን። እሱም የምሰራውን ሥራ በቀላሉ ተላምዶት ያግዘኝ ጀመረ፡፡
“ሥራውን በጥሩ ሁኔታ እየሰራን አንድ ላይ እየተረዳዳን ማደግ ጀመርን፡፡ በጣም እንዋደዳለን፣ እንተጋገዛለን፣ እንተሳሰባለን። እሱም ያግዘኛል ይንከባከበኛል፡፡ ከተማ ወጥቶ ሲመጣ ስጦታ ገዝቶልኝ ይመጣል። ብዙ ነገሮቹ የሚወደዱና በጣም መልካም ሰው በመሆኑ አሁን ፈጣሪ ድካሜን አይቶ ካሰኝ ሥል አመሰገንኩ፡፡
“ከዚህም የተነሳ የሥራ ብር ሁሉ በእሱ አካውንት ነበር የምናስቀምጠው፡፡ ከሱቅ ሥራ በተጨማሪ የህዝብ መኪና ገዛን፡፡ የመኪናው ዶክመንት በሙሉ በእሱ ስም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ አንድ ላይ ለዘጠኝ ዓመት በትዳር ቆየን።
“‘ሁሉም ነገሮች በእሱ ቁጥጥር ስር መሆኑ መጥፎ ነው ይዞብሽ ይጠፋል’ ብለው ጓደኞቼ ይመክሩኝ ነበር፡፡ በእሱ ሙሉ እምነት ስለነበረኝ እሱ እንደዚህ አያደርግም፤ ከጠፋም ይጥፋ በማለት ምላሽ ሰጠኋቸው፡፡ ጉድና ጅራት ከበስተኋላ ነው እንደሚባለው ጓደኞቼ የፈሩትም አልቀረ ደረሰብኝ፡፡
“ምንም ነገር ሳያስቀር ጠፋ፡፡ በአካውንቱ ላይ ያለውን ገንዘብ፣ ንግድ ፍቃድ፣ የመኪና ዶክመንት፣ የመኖሪያ ቤታችንን ፋይልና ሌሎች ነገሮች በሙሉ ይዞ ተሰወረ፡፡ በተለይም ደግሞ ሁለተኛ ተሳቢ መኪና እንገዛለን በሚል ተማክረን ያጠራቀምነውን ብር ጨምሮ ሁሉን ነገር በድንገት ይዞብኝ ተሰወረ፡፡
“ወንጀሉን ለፖሊስ ባሳውቅም የመክሰስ ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ እግዚአብሔር ለሁላችንም እንደ ሥራችን ይከፍለናል ስል እራሴን አጽናንቼ ሥራየን ቀጠልኩ” ሲሉ የደረሰባቸውን ጉዳት ፈገግታ ባልተለየው የምጸት ፊት አጫወቱን፡፡
አሁን ላይ ወ/ሮ ወርቄ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በማሰብ ስነ ልቦናቸውን በማጠንከር ወገባቸውን አስረው የጠፋባቸውን ገንዘብ በስራ ለመመለስ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ ትኩረታቸውን ኪሳራ ላይ ሳይሆን ሥራቸው ላይ አድርገዋል።
እንደ አጋጣሚ ባላቸው ከመጥፋቱ በፊት በሳምንት ስምንት ሺህ ብር የሚጥሉት እቁብ ዕጣ ስላልወጣ አልወሰደም ነበር፡፡ እቁቡን ከግማሽ በላይ ጥለው ስለነበር ባለቤታቸው ገንዘባቸውን ይዞ በጠፋ በሁለተኛው ወር አንድ ሚሊየን ብር ደረሳቸው፡፡ ይህን ገንዘብ ንግዳቸውን ማጠናከሪያ በማድረግ ሥራቸውን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
መኖሪያ ቤታቸው ለመናኸሪያ ቅርብ በመሆኑ ለመኝታ አገልግሎት የሚሆኑ ክፍሎችን በመስራት ገቢያቸውን ለማሳደግ እየተጉ ነው፡፡ ወደ ፊት እነዚህ ክፍሎችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ እቅድ እንዳላቸው አውግተውናል፡፡ ማንኛውም ሰው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ጠንክሮ ከሰራ የሚፈልግበት ደረጃ ይደርሳል የሚል ጠንካራ አቋም ያላቸው ወ/ሮ ወርቄ ዛሬ ላይ ከራሳቸው አልፈው ለበርካቶች ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
“አንድ ሰው አገኝሁ ብሎ ሥራውን ማቆም የለበትም፤ ከሰርኩ ብሎም ተስፋ መቁረጥም የለበትም” የሚል መርህ አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው በማጣት ወይም በማግኘት ህይወት ውስጥ ያልፋል፡፡ ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጠንክረን በመስራት ካሰብነው መድረስ እንችላለን ሲሉ ባስተላለፉት መልዕክት የዛሬውን አበቃሁ፡፡ ቸር ይግጠመን…
More Stories
“ጤናችን በአመጋገባችን ይወሰናል”-ዶክተር ዘላለም ታፈሰ
አዲስ ህይወትን በአሜሪካ
ጥቂት ስለ በርሊን ማራቶን