የ2017/18 በመኸር እርሻ ከተዘሩ ዋና ዋና ሰብሎች የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ አልመው እየሠሩ መሆናቸዉን በዳዉሮ ዞን የከጪ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

የ2017/18 በመኸር እርሻ ከተዘሩ ዋና ዋና ሰብሎች የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ አልመው እየሠሩ መሆናቸዉን በዳዉሮ ዞን የከጪ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2017/2018 በመኸር እርሻ ከተዘሩ ዋና ዋና ሰብሎች የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ አልመው እየሠሩ መሆናቸዉን በዳዉሮ ዞን የከጪ ወረዳ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ገለጹ፡፡

‎የወረዳዉ ግብርና፣ አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ጽ/ቤት በበኩሉ በመኸር እርሻ በወረዳው በዘር ከተሸፈነዉ ማሳ ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቋል፡፡

‎በወረዳው ከሚገኙ አርሶአደሮች መካከል ሸባራ ሰጠና ፣ ተፈራ ሽፈራዉና አለማየሁ አያኑ በመኸር እርሻ ወቅት ከአከባቢው አየር ሁኔታ ጋር የሚሠማሙ የስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተር እና መሰል ሰብሎች በመዝራት አመርቂ ምርት ለመሰብሰብ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‎አርሶ አደሮች ማሳቸዉን ደጋግመዉ ማረሳቸዉ፣ ግብዓቶችን በአግባቡ መጠቀማቸዉንና የአረም ቁጥጥር ወቅቱን ጠብቀዉ ማድረጋችዉን ተናግረዋል።

የግብርና ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ እና በምርጥ ዘር እንዲሁም በሙያዊ ክትትልና ድጋፍ ለምርትና ምርታማነቱ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

‎በወረዳዉ ከሚገኘኙ የግብርና ባለሙያዎች መካከል አቶ አማሩ ኡሸቾም በወረዳዉ በመኸሩ እርሻ የሚለሙ ሰብሎችን አርሶ አደሮች ከየአከባቢዉ የአየር ፀባይና ኢኮሎጂ ጋር በማገናዘብ እንዲያለሙ ስለመደረጉ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዘር ከመዝራታቸዉ በፊት ደጋግመዉ እንዲያርሱ፣ ከዘሩም በኋላ የአረም ቁጥጥር እንዲያደርጉ በመከታተልና በመቆጣጠር ብሎም በዋግና መሰል በሽታዎች ሰብሎች እንዳይጠቁ የመድኃኒት ርጭትን በወቅቱ በማድረግ አሁን በማሳ ላይ ያለዉም ምርት በወረዳዉ ለአጨዳ እየደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የወረዳዉ ግብርና፣ አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ንጋቱ ዮሐንስም በበኩላቸዉ በወረዳዉ በሚገኙ ስምንት ቀበሌያት በ2017/2018 የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደዉ 7 ሺህ አንድ መቶ ሃምሳ ሄ/ር መሬት ወደ 200 ሺህ ኩንታል ምርት በላይ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

‎ይሄዉም ካለፈዉ ተመሳሳይ የምርት ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ35% በላይ ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል።

‎ለስኬቱም በወረዳዉ አርሶ አደሩ መሬቱን ደጋግሞ እንዲያርስ ከመደረጉም በተጨማሪ ሙሉ ፓኬጅ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም ሁኔታዎች ተመቻችተዉ እንደነበርም ገልጸዋል።

አሁን በማሳ ላይ የሚገኘው ምርትም እንደወረዳዉ በጥሩ ሁኔታ እየደረሰ እንዳለ ጨምረው በዚሁ የተናገሩት የጽህፈት ቤቱ ተወካይ፣ በአጨዳ ወቅት የምርት ብክነት እንዳይኖርም የግብርና ሙያተኞችን ጨምሮ ሌሎችም ትኩረት ሰጥተዉ ይደግፋሉ ሲሉ ተናግረዋል ።

ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን