የኮሌጁንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

የኮሌጁንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኮሌጁንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑን የሆሣዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ።

በኮሌጁ የአይሲቲ መሠረተ ልማት ማስመረቅ የተቻለ ሲሆን በኮሌጁ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ማቲዎስ አኒዮ እና በሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል ።

የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አወል ሸንጎ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኮሌጁ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን አሰልጥኖ በማውጣት በሀገር እድገት ላይ የድርሻቸውን እንዲያዋጡ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በኮሌጁ ሰልጥነዉ በኢንተርፕራይዝ በመደራጀት የእንጨት ውጤቶችን በማምረት እና በዶሮ እርባታ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትም ከራሳቸው አልፈው ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከኮሌጁ በተለያዩ የስልጠና መስኮች በየጊዜው የሚሰለጥኑ ወጣቶችና ሴቶች ስራ ፈጥረው በመስራት ሀብት ማፍራት መቻላቸውን አቶ አወል ጠቁመዋል።

በዕለቱ የተመረቀው የአይሲቲ ማዕከል የስራና ክህሎት ሚንስቴር ባደረገው የ60 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የተሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በማዕከሉ የሰልጣኞችን ከምዝገባ እስከ ምርቃት ድረስ ያሉ መረጃዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ሲሆን ከኮሌጁ በ500 ሜትር ሬዲየስ ዉስጥ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚያደርግ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ማዕከሉ ሀገራዊ ስልጠናዎችን ጭምር መስጠት በሚያስችል መልኩ የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በማዕከሉ በonline ፈተና መውሰዳቸውንም ገልጸዋል ።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ እና የሀዲያ ዞን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ በበኩላቸው በኮሌጁ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በኮሌጁ ሰልጥነዉ በኢንተርፕራይዝ በመደራጀት ወደስራ የገቡ አባላትም ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ገልፀዋል ።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን