አዳኝና ታዳኝ
‘‘የወለደ አንጀት ስለማይጨክን ነው’’
በጌቱ ሻንቆ
(ክፍል ሶስትና የመጨረሻ)
(ክፍል ሶስትና የመጨረሻ)
ሳምንት በይደር ያቆየሁት የጉዞ ማስታወሻዬ ላይ ‘‘ስለ ሶሬሳ በር’’፣ አንስቼላችሁ ነበር፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ስም የማውጣት ችግር አልነበረም፡፡
የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለን ነበር፡፡ አዳዲስ በሸክላ የተገነቡ ዶርሚተሪዎች ዝግጁ ሆኑ። ዶርሚተሪዎቹ አዳዲስ በመሆናቸው መተኛ ፍራሾቹም አዳዲስ፣ ትራሶቹም አዳዲስ፣ ወለሉም አዳዲስ (መጀመሪያ ሰሞን ደክሞን ስንገባ ጋደም እንልበትም ነበር)፡፡ ወደነዚህ ብሎኮች ከኛ ቀድሞ ማን ሊገባ ይችላል? የግቢው የመጀመሪያ ልጆች ነንኮ፡፡ እናም አሮጌዎቹን መርጠን ወደነዚህ ኣዳዲስ ዶርሚተሪዎች ገብተን ነበር፡፡
ዶርሚተሪዎቹ የተገነቡበት ስፍራ በአንፃራዊነት ከቦዝኒያ መንደር ጋር ሲተያይ ቆላና ደጋ ነው፡፡ ደጋው ቦስኒያ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አዳዲሶቹ ዶርሚተሪዎች የሚገኙበት ይህ መንደር አዲስ ስም ወጣለት፡፡ ‘‘ገደል ግቡ’’፣ ተባለ፡፡
ገደል ግቡ መንደር ውስጥ ብዙ ትዝታዎች አሉን፡፡ አሁንም ስም ከማውጣት ጋር የተያያዙ። እኛ ዶርሚተሪ አጠገብ ያለው ክፍል ውስጥ እንዲሁ ሌሎች ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ከነዚህ ሲኒየር ተማሪዎች መካካል አንደኛው መላኩ ይሰኛል፡፡ መላኩ ለየት ያለ ባህሪ ነበረው፡፡ ‘‘ካፌ’’ ቢሰለፍም የካፌ ምግቡን ካፌ አይበላም ነበር፡፡ ወጡን በሳህን በአንድ እጁ፣ እንጀራዋን ደግሞ ራቁቷን በሌላ እጁ ይዞ ወደ ዶርሚተሪው ይመጣል፡፡
ዶርሚተሪው ውስጥ ከካፌ ያመጣውን ምግብ አጣፍጦ ይሰራዋል፡፡ ደብቆ ያስገባው የኤሌክትሪክ ምድጃ ነበረው፡፡ ደግሞ የማጣፈጥ ሙያውን ተግባር ላይ ማዋል የሚጀምረው ካፌ ተቀምጦ በሊታዎች፣ የበላነው ምግብ ተንሸራሽሮ ሆዳችን ለባዶነት ሲቀርብ ነው፡፡ አመሻሽቶ – ከአራት ሰዓት በኋላ፡፡ ሽታው እንደ እርጉዝ ሴት ይረብሸን ነበር። ብቻ በዚህ ከፍ ያለ የወጥ አጣፋጭነት ሙያው የግቢው ተማሪዎች የተለየ ስም አውጥተውለታል። ‘‘እምዬ መላኩ’’፣ ብለውታል፡፡
እንደነገርኳችሁ ነው፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስም የማውጣት ችግር አልነበረም፡፡ ጊዜው ‘‘ታይታኒክ’’፣ ስለተባለው አዲስ የሆሊውድ የፍቅር ፊልም የሚወራበት ነበር፡፡ ይህ ፊልም ገና ወደ እኛ ሀገር አልደረሰም፡፡ ባይደርስም በሌብነት መንገድ ተቀርፆ ግቢያችን መጣና አየነው፡፡ አደነቅነው፡፡ (በአማርኛ፣ syncronaized) በኋላ ስመለከተው ቢየስጠላኝም፡፡ ከፍለን ነበር ግን ያየነው፡፡ በተመራቂ ተማሪዎች ኮሚቴ በኩል እንደ ገቢ ማስገኛ ተወስዶ፡፡ በወቅቱ ሌላም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሚተላላፍ ሳምንታዊ ተከታታይ ፊልም ነበር፡፡ ‘‘ኣካፕልኮ ቤይ’’ የሚባል፡፡
ያኔ ገደል ግቡ መንደር ፊት ለፊት በመገንባት ላይ የነበረች ባለ ፎቆች ህንፃ ነበረች፡፡ በወቅቱ ለሴት ተማሪዎች ማደሪያ ነው የምትገነባው እየተባለ ይነገር ነበር፡፡ ቀንተናል፡፡ ሴቶቹን አናታችን ላይ ሊሰቅሉብን ነው እያልን፡፡
እንድ ዕለት እንደዚህ ሆነ፡-
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጌዴኦ መልክዓ ምድር የሰማይ ደመናን ጎትቶ መሬት ላይ የሚያንደባልል ነው፡፡ ዶፍ ዝናብ ነው የሚወርደው – አንዳንዴ፡፡ ሀይለኛ ዶፍ ዝናብ ዘነበ -ሌሊቱን፡፡
በማግስቱ ከእንቅልፋችን ነቅተን ወደ ደጅ ስንመለከት ነጭ ቀለም ተቀብታ መጠናቀቋን የምትጠብቀው፣ እጩ የሴቶች ዶርም ህንፃ በርበሬ በመሰለ ጎርፍ ዙሪያዋን ተከባለች፡፡ የከበባት ጎርፍ የሽሮ ብጥብጥ ይመስላል፡፡ ባህር ላይ የቆመች ደሴት መስላላች፡፡ በዚህ ምክንይት TITANIC የሚል ስም ወጣላት፡፡ ስሙን ያወጣላት ወዳጄና ጓደኛዬ ተማሪ ገላጋይ ጌታሁን ነበር፡፡ እነሆ ዛሬም ድረስ ህንፃዋ TITANIC የሚለውን ስም እንደያዘች ዘልቃለች፡፡
ዲላ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ስም ያላቸው ሰዎች የፈለቁበት ሆኗል፡፡ ከነዚህ መካካል ወግ አውጊዎች፣ የአጭር ልቦለድ ደራሲያን፣ ተርጓሚዎች ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ መካካል ገጣሚና ጋዜጠኛ የኋላሸት ግርማ (ፋና)፣ ጋዜጠኛ ፍቃዱ ዳምጤ (ኢቲቪ) አንተነህ ይግዛው (ደራሲና ጋዜጠኛ) ይጠቀሳሉ፡፡
ዛሬም ያለ ይመስለኛል፡፡ ‘‘መቅረዝ’’ የስነ-ፅሑፍ ክበብ፡፡ አልፎ አልፎ ክበቡ ከሌክቸር ቲያትሮች በአንደኛው ምሽት ያዘጋጅ ነበር፡፡ ከነዚህ ምሽቶች መካላል እንግዳ ወርቅ የሚባለው ተማሪ ወግ ከዓእምሮዬ የማይጠፋ ነው፡፡
እንዲህ ነው ነገሩ፡-
ተማሪዎች መፀዳጃ ቤቶች ውስጥ ወገብ ለመፈተሸ ሲገቡ የተለያዩ ስሜቶቻቸውን ግድግዳ ላይ ይፅፋሉ፡፡ እነዚህ የመፀዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ፅሑፎች መገኛዎች ዘንድ ገብቶ ቀበቶውን የፈታ ሰው መልሶ መታጠቁን ረስቶ እዚያው እንደተቀመጠ ሊቀር ይችላል፡፡ ግድግዳ ላይ የተፃፉት ፅሑፎች መነሳትን የሚያስረሱ ናቸው፡፡
አንድ ጊዜ እኔ ያነበብኩትን ልንገራችሁ፡-
አንድ ተማሪ ጥያቄ የሚመስል ነገር ግድግዳ ላይ ፅፏል፡፡ ጥያቄው እንዲህ ይላል፡-
‘‘እዚህ ምን እያደረግክ ነው?’’
መላሹ ‘‘አንተስ ምን እያደረግክ ነው?’’ ብሎ ጥያቄውን በጥያቄ መልሶለታል፡፡
‘‘አንተስ?’’
‘‘አንተስ?’’
‘‘አንተስ?’’… እየተባባሉ ግድግዳውን ግጥግጥ አድርገውታል፡፡
የእንግዳ ወርቅ ወግም ከእነዚሁ የመፀዳጃ ቤት ፅሑፎችን በማሰባሰብ የተቀመረ ነበር፡፡ እጅግ ፈገግ ካስደረግን ከዚያ የወግ ፅሑፍ አንዷን PUNCH ልምዘዝላችሁ፡-
መፀዳጃ ቤቱ ውስጥ ቀበቶውን ፈትቶ የተቀመጠ አንድ ተማሪ ተከታዩን ጥያቄ ግድግዳ ላይ ፅፎ ነበር፡-
‘‘ሰው ከተፀዳዳ በኋላ ዞር ብሎ የሚያየው ለምንድነው?’’
መላሹ፡-
‘‘የወለደ አንጀት ስልማይጨክን ነው’’
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው