በዞኑ የቡና ምርትን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተዉ እንዲሰሩ ተጠየቀ

በዞኑ የቡና ምርትን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተዉ እንዲሰሩ ተጠየቀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሸካ ዞን ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ከቡና ጥራት ቁጥጥር አስተዳደር ግብረ ኃይል አባላት ጋር በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በዞኑ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ገቢ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ባሻገር የተሰበሰበዉ የቡና ምርት ሙሉ በሙሉ  በጥራት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ከባለድርሻ አካላት ብዙ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

የሸካ ዞን ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ምክትል ኃላፊና የቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዳምሰገድ ሀይለየሱስ ቡና በተመረተው ልክ ለገበያ ከማቅረብ አንፃር በቂ ባለመሆኑ ሰፊ ስራ መሰራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከዞኑ 19 ሺህ ቶን በላይ የታጠበና ያልታጠበ ቡና መካከል 7ሺህ 871 ቶን በላይ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል ።

ጥራት ያለውን ቡና ከማምረት አንፃር የተሻለ አፈፃፀም ቢሆንም የአቅርቦት መጠኑን ለማሻሻል የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ  የሸካ ዞን ደን አከባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሳልኝ ናቸው፡፡

ህገወጥ የቡና ግብይትን ከመከላከል አንፃር በሁሉም አካባቢዎች ተከታታይነት ያለውን ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ጌትነት ገረመዉ – ከማሻ ቅርንጫፍ