በኮንትራት እና በአርሶ አደሩ የሚመረቱ ምርቶች ተበረታተዉ ለዉጭ ገበያ እንዲቀርቡ ማስቻል እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 05/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮንትራት የሚመረቱና በአርሶ አደሩ የሚመረቱ ምርቶች ተበረታተዉ ለዉጭ ገበያ ደረጃቸውን ጠብቀዉ እንዲቀርቡ ለማስቻል ማብቃት እንደሚገባ ተገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከኤክስፖርተሮች፣ አምራቾች፣ ኮንትራት ፋርመሮች እና ከዘርፉ ነጋዴዎች ጋር በምርት ጥራትና ቁጥጥር ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠዉ የሰሊጥ፣ ነጭ ቦለቄ፣ ዥንጉርጉር ቦለቄ እና ሌሎችም ለኤክስፖርት ከሚቀርቡ ምርቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተው በክልሉ የኢ-ሴክስ አማራጭ አለመኖሩ ለኮንትሮባንድ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጓታል ብለዋል።
ከኮንትሮባንድ ንግድ አኳያ በፍጆታ ምርት ዙሪያ በሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ቢሮዉ ቁርጠኛ አቋም እንደሚወስድ አስገንዝበዋል።
የዶላርን ዋጋ በቀላሉ ለማግኘትና የዉጭ ምንዛሬ ገቢን ከማስገኘት በተጨማሪ እንደ ሀገርም ሆነ ክልል በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ያለው ፋይዳ ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮንትራት የሚመረቱና በአርሶ አደሩ የሚመረቱ ምርቶች ተበረታተዉ ለዉጭ ገበያ ደረጃቸውን ጠብቀዉ እንዲቀርቡ ለማስቻል ማብቃት እንደሚገባ ነዉ አቶ ዳንኤል የጠቆሙት።
አዲስ የተቋቋሙት የክልሉ የንግድና ዘርፍ ም/ቤት እንዲሁም የነጋዴ ሴቶች ማህበር ም/ቤትም በመንግስትና በንግዱ ማህበረሰብ የሚያገለግሉ እንደመሆናቸዉ በንግድ ስርዐቱ ዙሪያ ነጋዴውን በማገዝ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።
በመድረኩ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ዉይይት የተደረገበት ሲሆን ከዘርፉ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከሚመለከተው አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግና ሁሉም አካላት ለዘርፉ ልማት ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊና የገበያ ግብይት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቀመሪያ ረሺድ በበኩላቸው ኤክስፖርተሮች መመሪያውን በመጠበቅ በህጋዊ መንገድ ምርት በማቅረብ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ ተቀናጅቶ በመስራት መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊና የንግድ ስርዓትና ሸማች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይስሀቅ ማሶሬ እንደገለፁት፤ የገበያ ስርዓቱን የሚያዛቡና የኮንትሮባንድ ምርት የሚያዘዋውሩ ህገወጦችን በጋራ መከላከል ይገባል።
ቢሮው፤ ኤክስፖርተሮች ትስስር በመፍጠር ምርታቸውን በተቀላጠፈ መልኩ መላክ እንዲችሉ የድርሻውን እንደሚወጣ አስረድተዋል።
የመድረኩ ተሳፊዎችም እንደገለጹት፤ በኤክስፖርት ዘርፉ የምርት ጥራት ቁጥጥር፣ የገበያ ስርዓት ሁኔታ፣ ህገወጥ ደላሎች ጣልቃ መግባትና ሌሎችም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መንግስት ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በንግዱ የሚበረታቱ ህጋዊነት ያላቸውን ስራዎች በማስቀጠል ችግሮቹን ለመቅረፍ በሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከመንግስት አካላት ጋር በጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ብዙነሽ ዘዉዱ
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ