ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የመንገድ ግንባታ ዘርፍን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የመንገድ ግንባታ ዘርፍን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የመንገድ ግንባታ ዘርፍን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ገለፀ።

ይህ የተገለፀው በዞኑ አበሽጌ ወረዳ ያያቶና ኩዳድ 4 ቀበሌ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነባው መንገድ በተመረቀበት ወቅት ነው ።

የጉራጌ ዞን ትራንስፓርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ከድር በምረቃ ስነስርአቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር መንገድ የሁሉም መሠረተ ልማት አውታሮች ቁልፍ ነው ብለው የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በቀላሉ መቅረፍ እነዲቻል የመንገድ ግንባታ ስራዎችን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

አክለውም መንገድ ሁለገብ አገልግሎት ያለው ቢሆንም በተለይም በጤናው ዘርፍ ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለማግኘት መንገድ ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የትምህርት ዘርፍን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆንና የአርሶአደሩ የግብርና ምርት ውጤቶችን በቀላሉ ለገበያ ተደራሽ ለማድረግ የመንገድ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ገንዘቡ፣ ጉልበቱንና ጊዜውን መስዕዋትነት የከፈለበትን የተመረቀው መንገድ ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ በአግባቡ ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ አህመድ በወረዳው ከፍተኛ የሆነ የግብርና ምርቶች አምራች የሆኑ ቀበሌዎች መኖራቸውና ከነኚህም ያያአቶና ኩዳድ 4 ቀበሌ አንዱነው ብለዋል ።

ህብረተሰቡ ባደረገው ተሳትፎ መንገዱ ተሠርቶ ለምረቃ በመብቃቱ እጅግ አመስግነዋል ።

አሁንም ምላሽ የሚፈልጉ ህብረተሠቡ የሚያነሳቸው ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በቀጣይ መንግስትና ህብረተሰቡን በማሳተፍ መፍትሄ እንዲያገኙ አቅደን እንሰራለን ሲሉ ገልፀዋል።

የወረዳው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሪት ንጋቷ አበበ በ2016 የበጀት አመት በርካታ አዳዲስና ነባር የጥገና መንገዶችን ለመስራት አቅደን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን ብለዋል።

ያያቶና ኩዳድ 4 ለምረቃ በመብቃቱ የተሠማቸውን ደስታ ገልፀው የመንገድ ግንባታውም በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀና 4ሚሊየን 1መቶሺ 2 መቶ58 ብር የፈጀ ስራ እንደሆነም አስረድተዋል ።

በቀጣይም በወረዳው መሰራት ያለባቸው የመንገድ ግንባታ ስራዎች በመኖራቸው የዞኑ ድጋፍ እንሻለን ሲሉ ተናግረዋል ።

አስተያየታቸውን ከሰጡን ያያአቶና ኩዴድ 4 ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጌታሁን በደዊ፣ ተስፋሁን ታደሰና ወ/ሮ ምሳዬ ሲሳይ የመንገድ ስራው በአጭር ጊዜ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልፀዋል ።

ከዚህ ቀደም ምርቶቻቸው ወደ ገበያ ለመውሰድና የጤና እክል ሲገጥማቸው ፈጥነው ወደ ሚፈልጉት የጤና ተቋም ለመድረስ ችግር ይገጥማቸው እንደነበረና አውስተው አሁን ላይ ግን የመንገዱ መሰራት ለችግራችን መፍትሄ ለማበጀት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል ነው ያሉት።

በቀጣይ መንገዱ ብልሽት እንዳይገጥመው አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርጉለት ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን