ምን ተይዞ ጉዞ!?
በኢያሱ ታዴዎስ
ኢትዮጵያ እና ኦለምፒክ አይነጣጠሉም። ግዙፉ የዓለማችን የስፖርት መድረክ ኢትዮጵያ ከምንም በላይ እንድትታወስ የሚያደርጋት ነው። ኦለምፒክ መጣ ከተባለ ለኢትዮጵያ ሰርጓ ነው። ደምቃና አሸብርቃ የምትታይበት፣ ስሟ ደግሞ ደጋግሞ የሚወሳበት፣ የአፍሪካ ምልክት መሆኗ ዳግም የሚረጋገጥበት የተለየ ድግስም ነው።
አትሌቶቿም ቢሆኑ ለክብሯና ስሟ ተዋድቀው ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ የሚያደርጉላት አርበኞቿ ናቸው። ለዚህም ኦለምፒክ የኢትዮጵያን ንግስና በዓለም አደባባይ የሚያረጋግጥላት ልዩ መድረክ ነው። ንግስናዋን ግን ሙሉ የማያደርግላት አንድ ቅር የሚያሰኘው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ብርታት በሩጫው መስክ መሆኑ ብቻ ነው።
በእርግጥ ሩጫው በኦለምፒክ ውድድር ከሚካሄዱ ስፖርቶች ግንባር ቀደምና ብዙ ተመልካቾች ያሉት ነው። ይሁን እንጂ እንደነ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩስያ የኦለምፒክ የውጤታማነት ማማ ላይ ለመቆም ሩጫው ብቻ በቂ አይደለም።
የኦለምፒክ ቁንጮ ለመሆን መላው የአትሌቲክስ ውድድሮችን ጨምሮ በ32ቱም የስፖርት ዓይነቶች ተወዳዳሪ በመሆን አሸናፊ የሚያደርግ የሜዳሊያ ብዛት መሰብሰብን የግድ ይላል። የዓለምን የምጣኔ ሃብት በቀዳሚነት እየመሩ ያሉት አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩስያ በኦለምፒኩም ኃያላን የመሆናቸው ምስጢር በስፖርት ዓይነቶች ሳይወሰኑ በየውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸው ነው። (በእርግጥ ሩስያ ከዩክሬን ጋር በገጠመችው ጦርነት ምክንያት በፓሪሱ ኦለምፒክ ላትሳተፍ የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው።)
በመሆኑም ኢትዮጵያ ያልተሸራረፈና ከነሙሉ ክብሯ ስሟን የሚያስጠራ ገድል በመድረኩ መፈጸም ከፈለገች ከሩጫው ሻገር ብሎ ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች ያንኳኳ ተሳትፎ ማድረግ አለባት። ይህ ነው አሁን ካላት በላይ ዝናዋን ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ የሚያዳርስላት።
ለማንኛውም ኢትዮጵያን ይህንን ዕድሏን የምትጠቀምበት ሌላ መድረክ በቅርቡ እየጠበቃት ነው፤ የ2024ቱ የፓሪስ ኦለምፒክ። የዘንድሮ ኦለምፒክ እንደ 100 ሜትር ሩጫ ሳይታሰብ ከተፍ ያለ ይመስላል። ከዚህ ቀደም የኦለምፒክ ውድድሮች ከመካሄዳቸው ከአንድ ከሁለት ዓመት በፊት ብዙ ይወራላቸው ነበር።
ያንኑ ያህል ሀገራችን አስቀድማ ስለምታደርጋቸው ዝግጅቶች ለሕዝቡ በየመገናኛ ብዙሃኑ የአዋጅ ያህል ተደጋግሞ ይለፈፍ ነበር። አሁን ግን ሁሉ ነገር የቀረ ይመስላል። “መጽሃፉም ዝም፣ ቄሱም ዝም” እንደሚባለው።
የፓሪሱ ኦለምፒክ በሀገራችን የጊዜ አቆጣጠር መሰረት ከፊታችን ሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ድረስ እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለታል። ከአምስት ወራት ያልበለጠ ዕድሜ ይቀረዋል ማለት ነው። በአምስት ወራት ውስጥ ምን ዓይነት ዝግጅት ተደርጎ ምንስ ውጤት ሊመጣ ነው? ሆድ ይፍጀው።
እኔ በግሌ ይህንን ሃሳቤን የማነሳው ኦለምፒክ ኮሚቴውን፣ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑን ወይም ደግሞ ስፖርት ኮሚሽንን ለመተቸት ሳይሆን መቼም ከፊታችን የተደቀነው ውድድር ግዙፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትልቅ ዝግጅት የሚጠይቅ በመሆኑና እስካሁን ድረስ ይህን የሚመጥን የዝግጅት ስራዎችን ባለማስተዋሌ ነው።
በእርግጥ ከአንድ ወር በፊት (ጥር 16/2016 ዓ.ም) የኢትዮጵያ ኦለምፒክ ኮሚቴ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በተገኙበት ለፓሪሱ ኦለምፒክ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር መካሄዱ የማይካድ ነው።
በዚሁ መርሃ ግብር በቀጣይ በቀሩት ጊዜያት የኦለምፒክ ሞቢላይዜሽን ስራዎች፣ የችቦ ቅብብል መርሃ ግብር፣ የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት፣ የአቀባበልና የሽኝት ፕሮግራሞችን ለማካሄድ መታቀዱ ይታወሳል። ከዚሁም መነሻ ንቅናቄው በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል።
የእኔም ዋናው ነጥቤ ከዚህ ከዝግጅቱ ጋር በተገናኘ የፈጠረብኝ ብዥታ ነው። ከላይ እንዳነሳሁት ከዚህ ቀደም የነበረው አካሄድ ከአሁኑ ሻል ያለ ነበር። ኦለምፒክ መድረኮች ከመምጣታቸው አንድ እና ሁለት ዓመታት በፊት ሕዝቡን ለማንቃት መገናኛ ብዙሃን ተግተው ይሰሩ ነበር።
ኦለምፒክ ኮሚቴ፣ ፌደሬሽኑም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ዝግጅትም ሆነ ሌሎች ንቅናቄዎቹን የሚያካሂዱት ቀድመው ውድድሩ ከመካሄዱ ከዓመት በፊት ነበር። የውድድሩ አካል የሆኑትን አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች እና አትሌቶችን የመመልመሉም ስራ እንዲሁ የሚሰራው አስቀድሞ ነበር። ሁሉም ነገር ተገቢው ጊዜ ተሰጥቶበት በእርጋታ ነበር የሚከወነው።
የአሁኑ ግን ሱሪ በአንገት ሆኗል። በአምስት ወራት ውስጥ ምኑ ተሰርቶ ነው ስኬታማ ዝግጅት ሊደረግ የሚችለው? በጥቂቱ መገናኛ ብዙሃኑን እንኳን ብናነሳ፣ በሌላ ጉዳይ ተጠምደው የፓሪሱ ኦለምፒክ ከወራት በኋላ እንደሚካሄድ የዘነጉ ይመስላሉ።
ከሀገር ውስጥ ይልቅ የውጪው ስፖርት የሚጥማቸው ሚዲያዎቻችን ለውድድሩ መነቃቂያ የሚሆኑ ዝግጅቶችን በማቅረብ ስፖርተኞችንና ፌደሬሽኑን ለውጤት እንዲሰሩ ማነሳሳትን እርም ያሉ ይመስላል። ውድድሩ ሊጀመር ሲል ግን ኢትዮጵያዊነታቸው ድንገት ትዝ ይላቸውና የዘገባ መዓት ያዥጎደጉዳሉ። ይሄ አካሄድ አትሌቲክሱን የትም አያሻግረውምና ከወዲሁ ቢታሰብበት ጥሩ ነው።
አትሌቲክስ ፌደሬሽኑም ቢሆን መገናኛ ብዙሃኑ የኢትዮጵያን የኦለምፒክ ውድድሮች ስኬትንና ቀጣዩን ውድድር በተመለከተ ከውድድር አስቀድሞ ሰፊ ሽፋን እንዲሰጡና ስፖርቱን እንዲያበረታቱ ጥሪ ማድረግ ነበረበት። “ነገር በዓይን ይገባል” እንደሚባለው ሕዝቡ አትሌቲክሱን እንዲደግፍ ከተፈለገ በመገናኛ ብዙሃኑ የማስተዋወቅና እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ደረጃ በደረጃ ይፋ ማድረግ የአትሌቲክስ ፌደሬሽንና የኦለምፒክ ኮሚቴው ኃላፊነት ነው።
ከዚህ በዘለለ ለኦለምፒክ ውድድሮች የሚደረጉ ዝግጅቶችን ሰፊ ጊዜ ወስዶ ማከናወን ያስፈልጋል። አትሌቶችና ሌሎች ተሳታፊ አካላትን ለመምረጥ ወቅቱን መጠበቅ አስፈላጊ ቢሆንም አትሌቶች በግል እና በቡድን የሚያደርጓቸውን ዓለም አቀፍ ውድድሮች በቅርበት መከታተል፣ እንዲሁም እንደየሚኒማቸው ለውድድሩ ተለይተው ዝግጅት የሚያደርጉበትን ጊዜ ከወዲሁ ማመቻቸትም ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።
ከዚህ ባሻገር ብዙ ጊዜ ትኩረት እየተነፈገ ያለውና ከቃል ባለፈ በተግባር ሊደገፍ ያልቻለው አሁንም በፓሪሱ መደገሙ እንደማይቀር እየተስተዋለ ያለው ከአትሌቲክሱ በዘለለ በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች በስፋት መሳተፍ አለመቻሉ ነው።
ከዚህ ቀደም ሀገራችን በብስክሌት፣ በቦክስ፣ በቴኳንዶ እና በውሃ ዋና ስፖርቶች ተሳታፊ ለመሆን ጥረት ብታደርግም የውድድሩ አሟሟቂ ከመሆን የዘለለ ታሪክ የላትም። አሁንም ሩጫውን ብቻ ተመክታ ነው ለውድድር የምትቀርበው።
ካለፉት ውጤቶች መነሻ ይህንን መጥፎ ታሪክ ለመቀየር የስፖርት ቤተሰቡ በተደጋጋሚ በሌሎች ስፖርቶች ላይም በትኩረት እንዲሰራ ቢጠይቅም አሁንም ጠብ የሚል ነገር የለም። ተስፋ የምናደርግበት ሩጫውም ቢሆን በኦለምፒክ መድረኮች አየተዳከመ መጥቷል። ስለዚህ ከቃል ባለፈ ሀገሪቱ ሜዳሊያ ልታገኝባቸው የምትችልባቸውን የስፖርት ዓይነቶች ላይ ጠንክሮ በመስራት ለውድድር መቅረቡ ምንም ጥያቄ የለውም።
ብቻ እንደ እኔ ምልከታ የ2024ቱ የፓሪስ ኦለምፒክ ገና ብዙ ሳይሰራበትና በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ የሚገኝ ውድድር ነው። ምን ተይዞ ጉዞ እንዳይሆንም ቀጣይ መርሃ ግብሮችን ለውድድሩ በሚመጥን መልኩ ዝግጅት በማድረግ ከወዲሁ የተደቀነውን ስጋት መቅረፍ የግድ ይላል።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው