በትር (ቦኩ) ጥንተ ታሪክ

በትር (ቦኩ) ጥንተ ታሪክ

በጌቱ ሻንቆ

ክፍል አንድ

ነገስታት እጃቸው ላይ የሚይዙት በትር (ቦኩ) አለ፡፡ ብዙዎቻችን ግን ይህ የሚይዙት በትር ምን ትርጉም አለው የሚል ጥያቄ አናነሳም፡፡ ነገስታት ብቻ አይደሉም የሀይማኖት መሪዎችም በትር ይይዛሉ፡፡ የሀይማኖት መሪዎች የሚይዙት ይህ በትር ምን ትርጓሜ አለው፡፡ ብለንም የማንጠይቅ ብዙዎች ስለመሆናችን እገምታለሁ፡፡

በቅርቡ የጌዴኦ ዘመን መለወጫ በዓል (ደራሮ) ተከብሯል፡፡ በዚህ የደራሮ በዓል ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም የደራሮ በዓላት ላይ የብሄረሰቡ ባህላዊ መሪ ወይም ንጉስ ወይም አባገዳ በትር ይዘው በአደባባይ ታይተዋል፡፡

ለመሆኑ ይህ በነገስታትም በሀይማኖትም መሪዎች የሚያዘው በትር (ቦኩ) ምን ትርጉም፣ ምን እንድምታ አለው? እኔና እኔን መሰል ብዙዎች እነዚህን ጥያቄዎች አንስተን ምላሽ ፍለጋ የተጓዝን አይመስለኝም፡፡

ዛሬ ግን መልሶችን እንፈልጋለን፡፡

‘‘Faseter capital’’፣ የተባለ ድረ ገፅ ‘‘scepter: The Power with in: The symbolisim of the royal scepter’’፣ በሚል ርዕስ ለጥያቄያችን ምላሽ የሚሆኑ ከፍ ያሉ መረጃዎችን ያትታል፡፡ ዝርዝሮቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

በታሪክ ውስጥ በትር (ቦኩ) በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባህል ውስጥ በርካታ ተምሳሌቶች ያሉት ምልክት ነው፡፡ እነዚህ ተምሳሌቶች ደግሞ ጥልቅ ትርጓሜ ያላቸው ናቸው፡፡ ይሁንና በአብዛኛው በትር (ቦኩ) ከሀይለ ልእልና (Power)፣ ከስልጣን ከፍታ፣ ከመሪነት መገለጫነት ጋር ይያያዛል። በዓለማችን ላይ በየደረጃው፣ በታሪክ ዕጥፋቶች ውስጥ እንደተስተዋለው፣ የበትር (ቦኩ) ተምሳሌታዊ ትርጉም በአብዛኛው ከፍ ሲል ከተገለፁት ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ለመሆኑ በትርን (ቦኩን) ይዘው ነገስታት በአደባባይ ሲታዩ፣ በአንድ ብሄረሰባዊ በዓል ላይ ሲከሰቱ የመሪነት ቅባትና ሀይል ያላቸው መሆናቸውን ማሳየታቸው፣ ይህም ምልክታዊ ተምሳሌታቸው መሆኑን በበዓሉ ላይ ለተሰባሰቡት ህዝቦቻቸው መግለፃቸው ነው፡፡

ለመሆኑ በትርን (ቦኩን) ተምሳሌታዊ ምልክት መያዝ የተጀመረው መቼ ነው? ይኸው ‘‘Fastere capital’’ የተባለው ድረ ገፅ ጥንታውያን ግብፆች ስለመሆናቸው ያትታል።

በጥንታዊት ግብፅ ይኸው ምልክት የከፍታና የስልጣን መገለጫ አድርጎ የተጠቀመበት ንጉስ ሜነስ ስለመሆኑ ነው። ‘‘Egyptian Hours’’ ፣ የተሠኘ ድረ – ገፅ ከከርስቶስ ልደት በፊት በ3150 የመጀመሪያውን የግብጽ ስርወ መንግስት ያቆመው ሰው ስለመሆኑ ነው የሚጠቅሰው። የንጉስ ሜነስ ስርወ መንግስት 65 ዓመታት ስለመቆየቱም ይነገራል፡፡

ንጉስ ሜነስ ግብፃዊ ነው ሲባል ግን ወገኑ ከማን ነው ? አረብ ነው ወይስ ጥቁር አፍሪካዊ?

ቻንስለር ዊልያምስ የተባለ ሰው፣ ‘‘The destruction of black civilization’’፣ በሚል ርዕስ አንድ ዳጎስ ያለ መፅሐፍ ፅፏል። ይህ በተለያዩ መረጃዎች ላይ የተመሰረተው ጥልቅ ጥናታዊ መፅሀፍ ላይ እንደተመለከተው ‘‘ኢትዮጵያ’’፣ የሚለው ግዛትና፣ ‘‘የኢትዮጵያ ነገስታት’’፣ ይመሩት የነበረ ግዛት አለ እያለ፣ ከሜነስ አስቀድሞም እንደነበረ ይተርክልናል፡፡ ከሜነስ በፊት ይመሩ የነበሩት ነገስታት አፅመ ርስታቸው ሚድትራኒያን ባህር መለስ እንደነበርም ይኸው መፅሐፍ ይነግረናል፡፡

ፀሐፊው በዚህ መፅሐፉ ላይ እንደተረከው ንጉስ ሜነስ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ንጉስ ነው፡፡ አረቦች ወይም አውሮፓውያን በእርሱም የንግስና ዘመን ይሁን አስቀድሞ በነበሩት የኢትዮጵያ አፅመ ርስቶች ላይ በቋሚነት አልነበሩም፡፡

በኋላ ግን ጦርና ሰይፍ ይዘው በመምጣት ወረራዎች አካሂደዋል፡፡ ወረራው ጥቁሮችን ከታችኛው አፅመ ርስታቸው እየገፋ ወደ ላይኛው ግዛታቸው ወስዷቸዋል፡፡ በዚያ ላይ የተፈጥሮ አደጋዎችና ጥቃቶች ተደምረውበት ምድራቸውን እየለቀቁ ሄደዋል፡፡

ዞሮ ዞሮ ምን ለማለት ነው? ቦኩን ወይም በትርን ለመጀመሪያ ጊዜ ይዞ በአደባበይ የታየው ንጉስ ሜነስ ኢትዮጵያዊ ወይም ጥቁር አፍሪካዊ እንጂ አረብ አልነበረም፡፡

እንመለስ ወደ ተነሳንበት የጌዴኦ ባህላዊ ንጉስ ስለያዘው ቦኩ ወይም በትረ መንግስት ጉዳይ፡፡

የጌዴኦ ብሄረሰብ ነገደ ኩሽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የነገደ ኩሽ ጥንታዊ የትመጣነት ሲጠና መነሻውን እስራኤል፣ ካም ነገድን መነሻ ያደርጋል፡፡ ነገደ ኩሽ ቀደም ሲል በደረሰባቸው መገፋቶች ወይም ሌሎች ምክንያቶች አፅመ ርስታቸውን እየለቀቁ ወደ ላይኛው የአፍሪካ ክፍል ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ኑቢያን፣ ኢትዮጵያን፣ ሱማሊያን፣ ጅቡቲን፣ ወዘተ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የነገደ ኩሽ ወገኖች በሱማሌ ሎው ላንድ፣ በሀረር፣ በባሌ፣ ከፍተኛ ስፍራዎች አድርገው በተለያዩ የኢትጵያ አካባቢዎች ሰፍረዋል፡፡ እነዚህ የኩሽ ነገዶች በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ታሪክ ውስጥ ምድባቸው ከከፍተኛ ስፍራዎች የኩሽ ቋንቋዎች ምድብ ላይ ያርፋል፡፡ ሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ…. የዚህ አብነቶች ናቸው፡፡

እናም በሜነስ ዘመነ መንግስት መያዝ የጀመሩት ባህላዊ የሀይልና ስልጣነ የበላይነት ፣ የከፍታ መገለጫ በትረ መንግስቶች ትውልድ ቅብብሎሽ አሁን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሷል ማለት የምንችል ይመስለኛል፡፡

ይህ ከሆነ ጉዳዩ በታሪክ አልፈን የተመለከትነው በትረ መንግስት ከአፍሪካ ተነስቶ ወደ ሌሎች አለማትም ተስፋፍቷል ማለት እንችላለን፡፡

ወደ እዚህ ድምዳሜያችን የማረጋገጫ አስረጆች ከማለፋችን በፊት ግን አንድ መተንተን ያለበት ጭብጥ እንዳለ አምናለሁ። ይኸውም የከፍታ መገለጫ፣ የስልጣን ማሳያ ምልክት የሆነው ቦኩ ጥንተ ታሪክ ባላቸው ነገዶች ወይም ብሄረሰቦች ውስጥ ተምሳሌትነቱ እስከምን ድረስ ነው?