ባለፉት 11 ወራት ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የካፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
መምሪያው የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ደረጃ “ሐ”፣ “ለ” እና “ሀ” ግብር ከፋዮች የግብር አሰባሰብ ንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፥ ዞኑ ከሚያመነጨው ኢኮኖሚ ግብርን በተገቢው በመሰብሰብ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
ለተግባራዊነቱም በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠርና ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብሩን በታማኝነት እንዲከፍል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
በዞኑ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ለገቢ አሰባሰብ በተሰጠው ትኩረት የራስ ወጪ በራስ አቅም መሸፈን ከመቻል አልፎ ከዚህ ቀደም በዞኑ የነበሩ ከግብዓትና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያያዥ እዳዎችን መሸፈን ተችሏል ብለዋል።
የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ፥ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 81 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ባለፉት 11 ወራት 2 ነጥብ 74 ቢሊዮን በላይ ብር ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
አፈጻጸሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ የታየበት ነዉ ብለዋል።
በዞኑ ከሚገኙ አጠቃላይ መዋቅሮች 6ቱ ከመቶ ፐርሰንት በላይ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻላቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ቢጣ፣ ሺሾ-እንዴ ወረዳና ቦንጋ ከተማ አስተዳደር በቅደም ተከተል ከፍተኛ አፈጻጸም ያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የደረሰኝ አጠቃቀም ባህል አነስተኛ መሆን፣ አዳዲስ መመሪያዎችን ተግባራዊ አለማድረግ፣ የገቢ ምንጭ አለማስፋት፣ የቅንጅት ማነስ፣ የደረጃ ሽግግር ዉስን መሆንና መሰል ጉዳዮች ክፍተት እንደነበሩ በመድረኩ አንስተዋል።
መምሪያው በ2018 ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱን አንስተው፤ ሐምሌ 01/2017 የሚጀምረው የደረጃ “ሐ” ግብር ሙሉበሙሉ በቴሌብር እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል።
ይህም የመንግስት ሀብት እንዳይባክን፣ የነጋዴው ማህበረሰብ ባለበት ግብር እንዲከፍል የሚጠቅም ነዉ ብለዋል።
በመድረኩ የመምሪያው ደንበኞች አገልግሎት፣ አወሳሰንና አሰባሰብ ቡድን መሪ በሆኑት አቶ አደመ ቆጵቶ አጠቃላይ አፈጻጸሙ እየቀረበ ነው።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የካፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ግርማ ደፋርን ጨምሮ የዞን፣ የሁሉም ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች ስራ አስፈጻሚዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነዉ።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የሰንበት ገበያ ማዕከል ሸማቹና አምራቹ ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የላቀ ሚና እንዳለው ተገለጸ
በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ከ36 ሚሊዬን ብር በላይ ወጪ የተሰራው የኡማ ባኬ መንገድ ተጠናቆ ተመረቀ
የ2017 የክረምት ወራት የገቢ አሰባሰብና የ2018 ዓ.ም የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳት ስራ በአግባቡ ለመስራት መዘጋጀታቸውን በጋሞ ዞን ባለድርሻ አካላት ገለጹ