ገቢን በተገቢው በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በተገቢው መመለስ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ገቢን በተገቢው በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በተገቢው መመለስ እንደሚገባ የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቴን ተናገሩ፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን ገቢዎች መምሪያ በ2016/2017 በጀት አመት ከተለያዩ ዘርፎች 2 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታውቋል፡፡

በቤንች ሸኮ ዞን የ2016/2017 በጀት አመት የገቢ አሰባሰብ ሂደት እና የደረጃ “ሐ” “ለ “መ” የግብር አሰባሰብ  ንቅናቄ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት  ተካሂዷል፡፡

የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ተረፈ ሲንቡል በመድረኩ እንደናገሩት፤ በዞኑ የሚመነጨውን የገቢ አቅም አሟጦ ለመሰብሰብ ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት በ2016/2017 በጀት አመት ከመደበኛ ገቢ እና ከማዘጋጃ ቤት ገቢ 2.2 ቢሊየን በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን  ከተለያዩ  ዘርፎች 2 ቢሊየን ብር  መሰብሰብ ተችሏል።

በበጀት አመቱ ግብር በዲጂታል እንዲሰበሰብ በተደረገው ጥረት በአምስት መዋቅሮች በቴሌ ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው በዚህ በጀት አመት በሁሉም መዋቅሮች ተግባራዊ እንደሚደረግም አመላክተዋል።

በ2016/2017 የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋትና ጉድለቶችን በማረም በ 2017/2018 በጀት አመት 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ግብ መጣሉንም ጠቁመዋል።

በዞኑ ያሉትን ትልቅ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር የገቢ አሰባሰቡን በማጠናከር የህዝቡን የልማት ጥያቄ መመለስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በንግድ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ወደህጋዊነት ያልመጡትን ወደህጋዊ ማምጣት ያስፈልጋልም ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ በ2016/2017 በጀት አመት ከተለያዩ ዘርፎች መሰብሰብ የሚገባቸውን ገቢ ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻላቸውን ጠቁመዋል።

በ2017/2018 በጀት አመት የነበሩ ችግሮችን ከወዲሁ በመቅረፍ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የንቅናቄ ተግባራትን በየደረጃ በሚገኙ መዋቅር በማካሄድ ወደተግባር እንደሚገቡም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን