ሸካቾዎች ንጉሳቸውን ሰይመዋል!

ሸካቾዎች ንጉሳቸውን ሰይመዋል!

ትውፊት፣ በአኗኗር ወጥነት የተዋቀረ ሀገረ-ሰባዊ ትውን ጥበብ እንዲሁም አፋዊ ሥነ-ቃሎች የአንድን ማህበረሰብ ማንነት የሚያደምቁ ከመሆናቸው በላይ ህልውናው እንዳይከስም የሚረዱ ሰዋዊ ሀብቶች ናቸው።

በአንድ የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል ዘንድ ዘላቂነት ያለው ቅጥልጥል የሆነ አብሮ የመኖሪያ ገመዱ ይጠነክር ዘንድ እንዲሁም እነዚህ ሰብዓዊ የማንነት መገለጫ ሀብቶች ይጎለብቱ ዘንድ የህዝቡን የጋራ ፍላጎት ባከበረ መልኩ የአስተዳደር ሥርዓት ይበጃል።

ይህም የአስተዳደር ሥርዓት የሚቃኘው እንዲሁ በተለምዶ በህዝብነትና በመሪነት መካከል ባለው ከፍታና ዝቅታ ሳይሆን በመሀላቸው በሚኖር ጽኑ ፍቅርና የእርስ በርስ መከባበር ውል ሰነድ አማካኝነት ይሆናል።

ወጥ የሆኑ ሕዝባዊ የማንነት መገለጫዎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ምድራዊ ጫናዎች ገጽታቸው ፍጹም የማይወይብ ስለመሆኑ ከዛሬው የሸካቾ ንጉስ ስያሜ ሥነ-ሥርዓት በላይ ምስክር ሊኖር አይችልም።

ለአንድ ክፍለ ዘመን በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ የነበረው የሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር ምንም እንኳን ለእነዚህ እጅግ የበዙ ዓመታት የደበዘዘ ቢመስልም ህዝቡ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሲገለገልበት ስለመቆየቱ በዘውድ ሥርዓቱ ጊዜም ሆነ በወታደራዊ መንግሥቱ ተጽዕኖ ሳይበገር እስካሁን የዘለቀው የህዝቡ ጠንካራ አንድነት ማሳያ ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ የሸካቾ የንግሥና ሥርዓት መዋቅሩን በተሟላ መልኩ ለማስኬድ ታቅዶ በተሠራው ሥራ ከብዙ አስርት ዓመታት በኋላ “ታቶ ተቺ ቄጆቺ” በማለት የንግሥና ማእረግ በመስጠት ሸካቾዎች 16ኛ ንጉሳቸውን ሰይመዋል።

በቁጥር እጅግ የላቁ የአካባቢው ተወላጆች፥ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ዳያስፖራዎች ሩቅ ተጉዘው በመናገሻዋ አንድራቻ(ጌጫ) በመገኘት የንግሥና ሥርዓቱን ታድመዋል።

ከአጎራባች ካፋ ዞን የካፌቾ ንጉስና የባህል ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ከቤንች ሸኮ ዞን፣ ከጋምቤላ ክልል ከማጃንግ ዞንና ከኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦራ ዞኖች የተውጣጡ የብሔረሰቡ ወንድምና እህት ህዝቦች በቦታው ተገኝተው የመርሃ-ግብሩ ድምቀት ሆነዋል።

አዘጋጅ፡ አስታወሰኝ በቃሉ – ከማሻ ጣቢያችን