በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በአፋጣኝ መመለስ እንደሚገባ ተገለፀ

በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በአፋጣኝ መመለስ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት አባላት ከክልሉ አስፈፃሚ አካላት ውይይት አድርገዋል።

የሁለቱ ምክር ቤት አባላት ከህብረተሰቡ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት የተነሱ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን ለአስፈፃሚው አካላት አቅርበዋል ።

የመሠረተ ልማት ችግር፣ የመብራት በተደጋጋሚ መቋረጥ፣ በቡና ምርት አርሶ አደሩ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ አለመሆኑ፣ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ፍትሃዊ አለመሆን፣ የትምህርት ጥራት እየተባባሰ መምጣትና መጠነ መቋረጥ ከፍ ማለት ፣ በጤና ተቋማት የመድሀኒት አቅርቦት በቂ አለመሆኑ ፣ የኑሮ ውድነት አለመሻሻሉ፣ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች በጥቃቅን ጉድለቶች ወደ ስራ አለመግባት፣ የወጣቶች ስራ አጥነት ችግር አለመቀረፍ፣ ወባና ኮሌራን የመሳሰሉ በሽታዎች በተደጋጋሚ መከሰት ፣ የደሞዝ መዘግየት ፣ በጌዴኦ ዞንና በኦሮሚያ አዋሳኝ አከባቢዎች የፀጥታ ስጋት መኖር፣ በአርብቶ አደር አከባቢዎች አልፎ አልፎ እንስሳትን የመዘረፍ ህገ ወጥ ተግባራት መኖራቸው በምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው።

ከህብረተሰቡ በተወካዮች በኩል ለቀረቡ ጥያቄዎች አስፈፃሚ አካላት መልስና ማብራሪያ ስጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮ ቴሌኮም ተወካዮች በኩልም መልስ ተሰጥቷል።

የመብራት እና የስልክ አገልግሎት መቆራረጥ እንዲሁም የአገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት ለመቅረፍ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እንሰራለን በማለት ቃል ገብተዋል ።

የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎች ትክክል መሆናቸውን አንስተው ችግሩን ለመቅረፍ ቢሮው በትጋት እየሰራ ነው ብለዋል።

በአሁን ወቅት በክልሉ በ14 ከተሞች ከፍተኛ በጀት የተያዘላቸው የውሃ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ በመሆኑ ግንባታዎች ሲጠናቀቅ የተጠቀሱ ችግሮች ይቀረፋሉ፤ ሀምሳ በመቶ የሆነውን የንፅህ መጠጥ ውሃ ሽፋንም ከፍ ይላል ብለዋል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውሃ ግንባታ ግብዓቶች ከፍተኛ ውጪ መጠየቃቸው የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተጠቅሷል::

ከክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘብዲዮስ ኤካ በተመሳሳይ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት አስተያየት ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን መሀል ላይ መቀዛቀዝ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በአራት ድስትሪክቶች ተግባራት እየተፈፀሙ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የመጀመር ፍላጎት የለውም ያሉት አቶ ዘብዲዮስ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶችም በቅርቡ ተጠናቀው ወደ ስራ ይገባሉ ነው ያሉት።

ባለስልጣኑ የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ለማርካት አዳዲስ 2 ዲስትሪክቶችን ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የክልሉ የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይለማርያም ተስፋዬ ባለፉት ጥቂት አመታት ተከስቶ የነበረውን የግብርና ግብዓት ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥረት መደረጉን ጠቅሰው በዚህም አመርቂ ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።

አሁንም በርካታ ሺህ ቶን ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ከባህር ማዶ ወደ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ስለመሆኑም አመላክተዋል ።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከጎረቤት ሀገራት፣ ከኦሮሚያ ክልልና በዞኖች አዋሳኝ አከባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች የፀጥታ ስጋት እየሆኑ በመሆኑ በጥንቃቄ መያዝ ይገባል ብለዋል።

የሻኔ ታጣቂ ቡድንን አደብ ለማስያዝ የኢፊድሪ መከላከያ ሰራዊት የራሱን ስራ እየሰራ ነው ያሉት የቢሮው ሀላፊ ህብረተሰቡም ተገቢውን ድጋፍ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ