የየማ “ፖስተኛው”
በጌቱ ሻንቆ
ፖስተኛው መጣ ለናፍቆታችን ጥም የሚያረካ
አልኩልህ ውዴ ትንፋሽ እስኪያጥረኝ ባንተ ብመካ፡፡
ቢያስደስተኝም ማሸጊያው ፖስታ ጌጡ ማማሩ
እጅግ ጓጉቼ ሳየው የለም ጦማሩ፡፡
የተቀበልኩት ያንተን እንግዳ
ደግሼ ነበር ጥቂት ፍሪዳ፡፡
ደስታዬ ቢታይ ለአምባው በሙሉ
አወይ እድሏ ፃፈላት አሉ፡፡
በሽቶህ ልርካ ደብዳቤም ባላይ
ጠረንህ አለ እማሸጊየው ላይ፡፡
እስኪ ንገረኝ ማን እንደከፋ
ምን ብትፅፍልኝ መልዕክትህ ጠፋ፡፡
አያ ሸንኮራ ልቤ ጠብቆ
ያጨዳው ለታ ቢታይ ሸንበቆ፡፡
በቆሎ አድርሼ ተክዬ አገዳ
እንዴት ለፋለሁ ለቆረቆንዳ፡፡
ታጥፎ በፖስታ እንዴት ይላካል
እንባ አበባ አይደል በምን ይደርቃል?
ላኩት ባዶውን መሰናበቻ
አይነግርህም ወይ ሀዘኔን ብቻ፡፡
ጉድለቴ ገሀድ ይውጣ አደባባይ
ቃላት አልፅፍም እጦማሬ ላይ፡፡
የጠቆረ ፊት መንገር ካልካደ
ሀዘኔን አይቶ በቃኝ ከሄደ፡፡
እኔ በፖስታ ወርቃማ የመገኛኛ ዘመን ከነበሩት፣ በፖስታ መልእክት ከፃፉት አንዱ ነኝ፡፡ የ የማ አዲሱ ‘‘ፖስተኛው’’ ዜማ ወደ እዚያ ወርቃማ ዘመን መልሶኛል፡፡ ፖስታ መጣልህ፣ ፖስታ መጣልሽ ሲባል እጅግ በጣም ደስ ይል ነበር፡፡ መልእከቱን(ጦማሩን) ከፍቶ የማየት ጉጉቱ የሚፈጥረው ስሜት በራሱ ደስ የሚል ዓይነት ነበር፡፡ በተለይ የፍቅረኛ ከሆነማ፡፡ ልብ ውርድ ነው የሚያረገው። የናፍቆት፣ የፍቅር ረሀብና ጥም መቁረጫ አንዱ መንገድም ነውና፡፡ የቸገረ እለት ማለት ነው፡፡
የፖስታ ማሸጊያዎች እንደ ላኪው አቅም ነው የሚወሰኑት፡፡ ፖስታ ቤቶች ቀለል ባለ ገንዘብ የሚሸጧቸው የፖስታ ማሸጊያዎች አሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ በየሱቁ የሚሸጡ እጅግ ያማሩ ማሸጊያዎችም አሉ፡፡ ሀረጎቻቸው በጣም የሚያምሩ፡፡ እራስህም ባበጀኸው ማሸጊያ መላክ ይቻላል፡፡ በአደራም፣ ባስቸኳይም በተራ መልዕክትም፡፡ ቴምብር መግዛት ግን ግድ ነው፡፡ እንደ መልዕክቱ ዓይነት፡፡
እንዲሁም ደግሞ ትንሽ ዋጋ የሚጠይቀው የፖስታ አይነት አለ፡፡ ለዚህ ፖስታ መፃፊያ ወረቀት አያስፈልግም፡፡ እላዩ ላይ ይፃፍበታል። ቴምብርም አያስገዛም፣ አይለጠፍበትምም፡፡ ኤሮግራም ይሰኝ ነበር፡፡ በ የማ አዲሱ የ ‘‘ደጋ ሰው’’ አልበም ውስጥ ካሉት ዘፈኖች መካካል አንዱ ነው እንግዲህ ‘‘ፖስተኛው’’፡፡
በነገራችን ላይ የ የማ አዲሱ የደጋ ሰው አልበም ላይ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ድምጾችን ሰማንበት ይላሉ፡፡ ጂጂን ሰማንባት ይላሉ፡፡ ቤቲ ጂን ሰማንባት ይላሉ። እኔ ደግሞ አንዳንድ ዘፈኖቿ ላይ ማሊን ሰምቼባታለሁ፡፡ የማሊን የክር መሳሪያ ማጀቢያ ሙዚቃዎችን የማ የምታደምጥ ይመስለኛል፡፡ ከማሊ ዘፋኞችም መካካል የአሊ ፋርካ ቱሬን። በዚህ ጉዞዋ ከአፍሪካ የሙዚቃ ቅኝቶች ጋር ተራርቋል የሚባለውን የኛን ሙዚቃ ለማቀራረብ ድልድይ መሆን ያሰበችም ይመስለኛል፡፡ ደግሞም ነው፡፡ የደጋ ሰውን በሙዚቃ መሳሪያዎች ታጅባ ስትከውን ተመልክቼያለሁ፡፡ እዚህ የሙዚቃ ክዋኔ ላይ ያሉትን የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችን አለባበሶች አተኩራችሁ ከተመለከታችሁ እውነት ነው ትላላችሁ፡፡
ማሊ፣ የአፍሪካ የሙዚቃ ልብ የምትባለው ሀገር በአለም አቀፍ ትላልቅ መድረኮች ላይ ኮንሰርቶቻቸውን የሚያቀርቡ አርቲስቶች ያሉባት ሀገር ናት፡፡ ሰይድ ኬታ፣ አሊ ፋርካ ቱሬ፣ ኦማ ሳንጋሪ፣ ፋጡማታ ዲያዋራን አብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
የማም እነዚህ መድረኮች ላይ በአማርኛ የሙዚቃ ስልተ መንገድ መቆም የፈለገች ይመስላል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ መድረኮች ይበቃሉ ብዬ ከማስባቸው ሙዚቃዎቿ መካካል አንዱ ደግሞ ‘‘ፖስተኛው’’ ነው፡፡
እንመለስ ወደ ፖስተኛው ፡-
የ የማ ፖስታ ደረጃው ከፍ ያለ ነው፡፡ ማሸጊያው ያምራል፡፡ ሀረጎቹ ማለቷ መሰለኝ። ወይም ደግሞ የማሸጊየው ላይ አበቦች። ወይም ደግሞ ባለቀለም ቢራቢሮዎች፡፡ ወይም ደግሞ ባለቀለም ወፎች፡፡ ደስ ይላል የ የማ የትውስታ ገመድ፡፡ ስቦ ወሰደኝ፡፡
ግን ደግሞ እዚህ ላይ የአዝማቹን ስንኞች ይበልጥ ምስል ከሳች ማድረግ ይቻል ነበር። ገጣሚው ያልተጠቀመባቸው የቃላት ምርጫ ዕድሎች ስለመኖራቸው ይታየኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‘‘ማማር፣ መደሰት’’፣ የሚሉት ቃላት ረቂቅ መጠሪያዎች ናቸው፡፡ ረቂቅ መጠሪያዎች ለስነፅሑፍ የሚመረጡ ቃላቶች አይደሉም፡፡ ምስል የመከሰት ሀይላቸው ዝቅ ያለ በመሆኑ። ስለዚህ ማማሩንም ምስል በሚከስት ቋንቋ፣ ምልሰቱንም ምስል በሚከስት ቋንቋ መግለፅ አስፈላጊ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ተችሎ ቢሆን ኖሮ የግጥም ውበቱ አሁን ከሚታየው በላይ ከፍታ ይኖረው ነበር፡፡
ፖስታ ከላኩለት የፖስታ መልእክት ከተፃፈላቸው ሰዎች መካካል አንዱ ነኝ ብያችኋለሁ፡፡ ከፃፍኳቸው ፖስታዎች መካካል ለአንዲት የኮሌጅ ተማሪ ጓደኛዬ እፅፍ የነበረውን ላንሳ፡፡ እሷም ያለችኝን ላስታውስ፡፡
በተለይም የሷን ላስቀድም፡፡ የኔ ደብዳቤዎች ሲደርሷት ዶርሟ ውስጥ ያሉ ጓደኞቿ ጭምር ፃፈላት ፃፈላት ብለው ያወሩ ነበር፡፡፡ ደብዳቤ መፃፍ ለካ እድል ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የፍቅር ደብዳቤ ሲሆን፡፡ እንደ ዜና ይወራ እንደነበር በኋላ ነግራኛለች፡፡ እየተፃፃፍን ሳለ ግን አንድ ነገር ተከሰተ፡፡
እንደምወዳት መልክዕት(ጦማር) ይዞላት ለሄደው ደብዳቤዬ የሰጠችኝ ምላሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡ እንደማትፈለገኝ – እሷ(በኋላ ሚስቴ ብትሆንም)፡፡ ለዚህ መልዕክቷ ምላሽ ልኬያለሁ፡፡ የሚያምር ሀረግ ያለው ማሸጊያ ውስጥ፣ የሚያምሩ የልብ ቅርፅና አበቦች በታተሙበት ባለቀለም ወረቀት ላይ፡፡ ወረቀቱ ግን ምንም ዓይነት ጦማር (የፅሑፍ መልዕክት) አልነበረውም፡፡
ይህ መልእክት የደረሳት ዕለት የተሰማትን ስሜት ነግራኛለች- ጓደኛዬ(ሚስቴ) ፡፡ ፖስታ መጣልሽ ተብላና ተቀብላ ከተመለሰች በኋላ ጦማር የሌለው ሆኖ ስታገኘው በጣም ነበር የተናደደቸው፡፡ የማ ውስጥ ግን ንዴቱ ሳይሆን ሀዘኑ ነው ያለው፡፡
የምትወደው ደብዳቤ ሲመጣ ፍሪዳ ጥላ ለምትደግስ የወዳጇን መልእክት ናፋቂ ለሆነች አፍቃሪ ጦማር የሌለው መልዕክት ሲደርሳት የሚፈጠረው ስሜት ንዴት ነው ወይስ ሀዘን? ተደግሶ ሙሽራዋ የቀረባት ሴት ሊሰማት የሚችለው ስሜት ምንድነው?
ንዴት ወይስ ሀዘን?
በርግጥ ወረድ ባሉት ስንኞች ውስጥ የ የማ ስሜቶች በትክክለኛው መንገድ የተገለፁ ይመስለኛል፡፡ ደጋግሜ የማ፣ የማ የምለው የዘፈኑ ገፀ -ባህሪ እሷ ስለሆነች ነው፡፡ የንዴት ወይም የብስጭት ስሜቶቹ የተገለፁት በነዚህ ስንኞች ውስጥ ነው፡-
አያ ሸንኮራ ልቤ ጠብቆ
ያጨዳው ለታ ቢታይ ሸንበቆ፡፡
በቆሎ አድርሼ ተክዬ አገዳ
እንዴት ለፋለሁ ለቆረቆንዳ፡፡
እነዚህ ሀረጎች የብስጭት፣ የንዴት ስሜቶችን ነው ያዘሉት፡፡ ‘‘ቆረቆንዳ!’’ እስከማለት ድረስ ነው ብስጭቱ፡፡
ከዚያ በኋላ ያሉት ስንኞች ግልጽ ናቸው። እሷም ብድር መላሽ ሆናለች፡፡ ባዶ ጦማር ልካለች፡፡ ብስጭት ነው፡፡ ግን አሁንም ንዴት ይቀድማል ወይስ ሀዘን የሚለው ነገር በተከታዮቹም ስንኞች ውስጥ ይታያል፡፡
ከዚህ ውጪ ሸጋ የሙዚቃ ቅንብር፣ ሸጋ ሀሳብ፡፡ ሸጋ ድምፅ፡፡ ሸጋ ኢትዮጵያ- በአፍሪካ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው