ሂሳብና ሀሳብ
በጌቱ ሻንቆ
አህለን!! አህለንዎሳለን። የቆየ የሠላምታ አይነት ነው።
ሂሳብና ሀሳብ ላይ እንዴት ነህ። ሂሳብ አውቀህ ሀሳብን ካላወቅክ ነገር ቶሎ አይገለጥልህም።
ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ የሂሳብ አዋቂ ሠው ነበር። ይህ አዋቂ ሠው ወደጓደኛው ስልክ ደወለና እንዲህ አለው:-
“አንድ ሲደመር አንድ እኩል ይሆናል ሶስት”፣ አለው። እኩል ይሆናል ሶስት ብሎ ስልኩን ዘጋው። ስልክ የተደወለለት ሠው የሂሳብ እንጂ የሃሳብ እውቀት የለውም። እንዴት ሊሆን ቻለ ሣይል፣ ሳያሰላስል መልሶ ወደጓደኛው ስልክ ደወለ።
“አንድ ሲደመር አንድ እንዴት ሶስት ሊሆን ይችላል?”፣ አለው።
አንድ ሲደመር አንድ ስንት ነው?
እኛ ሀገር ውስጥ የሂሳብ ችግር የለም። ችግሩ የሀሳብ ዝግነት ነው።
ሠውየውም ” እኔና ሚስቴ ልጅ ወለድን” ብሎ መለሠለት። ሂሳቡ እንጂ ሀሳቡ ካልገባህ መልሶ ጠያቂ፣ ደንቆሮ ትሆናለህ። ነገር ቶሎ አይገባህም።
አንድ ጊዜ ነው። አስር ሰዎች አደን ወጥተው አስር ሚዳቆዎች አደኑ። ከአስሩ አዳኞች መካከል አንደኛው እነዚህን ያደንናቸውን የሚያካፍለን አዋቂ ሠው ያስፈልገናል አለ።
ከአዳኞቹ፣ ከአስሩ ሌላኛው ተነሳና፣ “ይህ ምን ዕውቀት ያስፈልገዋል? አስር ነን አስር ሚዳቆዎች አድነናል አንዳንድ ይደርሱናል”፣ ማለት።
የሚያካፍለን ሠው ያስፈልጋል ብሎ ጥያቄ የጠየቀው ሠው ከተቀመጠበት ተነስቶ ተንደረደረና አንዳንድ ይደርሰናል ያለውን ሠው አይን በቡጢ መታ። የሠውየው አይን እንደንቧይ ፈረጠ።
ሂሳቡን እንጂ ሀሳቡን ካላወቅክ ትርፉ የአይን መጥፋት ነው።
ይህንን ያስተዋለ፣ ከአስሩ አንደኛው ምን ቢል ጥሩ ነው?
“ማካፈሉ ትክክል አይደለም። እኛ ዘጠኛችን አንድ ሚዳቆ እንወስድና አስር እንሆናለን። አንተም ዘጠኝ ሚዳቆዎች ትወስዳለህ። አስር ትሆናላችሁ”፣ አለ።
ሀገራችን ውስጥ ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው። የፍትሀዊነት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ አገኘ የሚባለው ጉልበተኞች እና በጉልበታቸው የሠበሠቡትን ሀብት ባንድ ወገን እኛን ደግሞ በሌላ ወገን ቆጥሮ በማመጣጠን ነው። እኛ ሀገር ውስጥ የፍትሀዊነት ሂሳብ ዘጠኝ ለአንድ ነው። ሂሳቡን እንጂ ሀሳቡን ሳታውቅ ይገባኛል ብትል ይገባልሀል!
አንዲት ህፃናትን ሂሳብ የምታስተምር መምህርት ናት። ሂሳብ የምታስተምራቸውን ህፃናት እንዲህ ስትል ጠየቀቻቸው:-
“ልጆች ልብ በሉ። ልብ በሉ። አንድ ጉረኖ ውስጥ አስር በጎች ነበሩ። ከአስሩ ሁለቱ ከጉረኖው ወጡ። ስንት ቀሩ?”
ከህፃናቱ መካከል አንደኛው እጁን አነሣና:-
“ሚስ ምንም በግ አይቀርም”፣ አላት።
አስተማሪዋ እንዴት ምንም ይሆናል ብላ ህፃኑን በኩርኩም አናቱን አርገበገበችው።
ሂሳብ ማወቁ አይደለም። ሀሳቡን አለማወቅም ኮርኳሚ እጆችን ያስነሳል። ይኸው ነው ያለው እውነት።
አስተማሪዋ ከኩርኩሙ በዃላ ህፃኑን” እንዴት ምንም ይሆናል?”፣ ስትል መልሳ ጠየቀችው። ምን ብሎ ቢመልስላት ጥሩ ነው።
“ሚስ አንቺ የኛን ቤት በጎች አታውቂም። እናታቸው ከወጣች ሁሉም ናቸው የሚወጡት”
በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ታወሰኝ። እኛ ሀገር ውስጥ እንደ ጎረኖ በግ የመሆን ችግር አለ።
አንዱ አንዱን ተከትሎ ይበራል እንጂ ለምን እንደሚበር አይበረብርም። እንደሚያባርርም አያውቅም። ለምን የሚል ሀሳብ የለም።
እኛ ሀገር ውስጥ ያለው ችግር፣ ሀሣብህ የሚታወቀው በኩርኩም አናትህ ከወረደ በዃላ ነው።
እኛ ሀገር ውስጥ ከሃሳብ ይልቅ ለሂሳብ ቅድሚያ የሠጡ ሠዎች ነግሠው አልነበር። የሠዎቹ ዋነኛው ችግር ምን መሠለህ? የቅደም ተከተል። ሀሳብ ነው ሒሳብን የፈጠረው። ይህን ባለማወቃቸው ሀሳብን ከትምህርት ስርዓት አጠፉት። ሒሳብ ሂሳብ የሚል ትውልድ አባዝተው አረፉት። ሒሳብ ካገኘ ሠው ያርዳል። ህንፃ ያፈርሳል። ግንብ ያቃጥላል። አገር ለማፍረስ ይሮጣል። ምክንያቱም ሀሳብ የለውማ።
ችግሩ የሚጀምረው ከታች ነው። ህፃናትን የተጠየቅ ሂሳብ ማስተማር ላይ ከፍተኛ ክፍተት አለ።
አሁንም አንዲት የኬጂ ሂሳብ አስተማሪ ናት። ልጆቿን መደመር እያስተማረች ጥያቄ ጠየቀቻቸው።
“ልጆች ባንድ እጄ አራት ብርቱካን አለኝ። በሌላኛው እጄም አራት ብርቱካን አለኝ። እኔ ምን አለኝ?”
ተማሪዎቿ በአንድ ድምፅ ምን ብለው ቢመልሱላት ጥሩ ነው?
“ትላልቅ እጆች!!”
ሂሳቡን እንጂ ሀሳቡን ያለማወቅ ችግር።
የኛ ሀገር ትልቁ ፈተናም ይኸው ነው። ሂሳብ ያለው ሀሳብ የሌለው ነጋዴ አባዛንና የኑሮ ሂሳብ ናላችንን በጠበጠው። የዚች ሀገርም ትልቁ ፈተና ይኸው ነው። ሂሳብ እንጂ ሀሳብ የሌለው፣ ስለሀገሩ ስለዜጎቿ የማይገደው ስግብግብ ነጋዴ በበዛበት ከተማ ግብግብ ነው። ግብግብ ዋጋ፣ ሂሳብ ያስከፍላል። ገቢ ትንሽ አንገብጋቢ በዙ።
ስኳር ሳሎን ታውቃላችሁ? ስኳር ሳሎ እኛ ሀገር ውስጥ የኖረ፣ ሂሳብ የሌለው ሃሳብ ያለው ሠው ነበር። እኛ ሀገር ውስጥ ሂሳብ የነበራቸው ብዙ ሠዎች ኖረው አልፈዋል። የሚያስታውሳቸው ግን የለም።
ስኳር ቤትም ሂሳብ የለውም። ለምኖ ነው የሚኖረው። ለምኖ ሠው የሚበላው ነገር ሲሠጠው። የተሠጠውን የሚበላ ምግብ ከመመገቡ በፊት እኩል ሁለት ቦታ ይከፍለዋል። ግማሹን ይበላና ግማሹን ለወለደች ሴት ወስዶ ይሰጣል። መውለዷን እንጂ የማን ወገን ነች ብሎ ሂሳብ አይሠራም።
ስኳር ሣሎ። ሂሳብም ሀሳብ ያለው ሠው። አካፍሎ ያካፍላል። እኛ ከተማ ውስጥ ግብግብ የገነነው በገብጋባነት ነው። ሀሳብ ሂሳብም ያለው እየተጠፈጠፈ።
ገብጋባነት ክህደት ይወለዳል። ሂሳብ ሂሳቡን ማሰብ ብቻ ከሆነ ነገርህ የመታመን ሀሣብም ተግባርም ድሀ ትሆናለህ። ጠማማ ፍርድም ጠያቂ ትሆናለህ።
ሀገራችን ውስጥ ስኳር ሳሎ፣ የሀሳብ ከፍታ ከሞተ በዃላ ነው ፍርድ የተጣመመው። ፍርድ ጠያቂም ፈራጁም ሂሳብ እንጂ ሀሰብ የሌለው ሆኖ። ይኸው ነው እውነታው። ሂሳብም ሀሳብም ያለው ሠው አድርገኝ ያለበለዚያም ሂሳቡን እንጂ ሀሳብ አትንፈገን።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው