የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት መመሪያን በመከተል ለልማት ተግባር የሚመደብ የመንግሥት ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ መዋል እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት መመሪያን በመከተል ለልማት ተግባር የሚመደብ የመንግሥት ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ መዋል እንደሚገባ ተገልጿል።
የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት የኦዲት ግኝት ክትትል ግብረ ኃይል የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ መሠረት በላይነህ መንግሥት ለልማት ሥራ የሚመድበውን ውስን ሃሀብት ለተፈለገው ዓላማ መዋል አለመዋሉን የሚከታተለውን አደረጃጀት በአዋጅ መቋቋሙን ጠቅሰው አደረጃጀቱ ውጤታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዚህ መድረክ በኦዲት ግኝት ግብረ-ኃይል የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቧል።
ከተከናወኑት ተግባራትም በኦዲት ግኝት ከተለዩ ግኝቶች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ተመላሽ እንዲሆን ቢደረግም ከግኝቱ አንፃር ዝቅተኛ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የፋይናንስ የህግ ማዕቀፍ አለማስከበር፣ የበጀት አጠቃቀም ከአሠራር ውጪ መሆን፣ የመረጃ አያያዝ ችግር፣ ተጠያቂነትን የማስፈን ሂደት ደካማ መሆንና የመሳሰሉት እንደ ችግር የተነሱ ነጥቦች ናቸው።
ከዓላማ ውጪ የዋለውን የመንግሥትን ሀብት ለማስመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን በየመስሪያ ቤቶች በሚታዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ ወቅታዊና አስተማሪ የእርምት እርምጃ በበቂ ሁኔታ መውሰድ፤ አመራሩ ለኦዲት ግኝቶች ትኩረት በመስጠት ለማረም ቁርጠኛ መሆን፤ ይህንን እንዲከታተል በየደረጃ የተቋቋሙ አደረጃጀቶችን በተገቢው መደገፍ እንደ አቅጣጫ ተቀምጠዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል ትዕግስቱ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ