የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ

የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ

በደረጀ ጥላሁን

የኅብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡን ችግር በማቃለል የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአገራችን የተለያዩ ዓይነትና ደረጃ ያላቸው የኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ይገኛሉ። ማህበራቱ በገጠርም ሆነ በከተማ ለሚኖረው ሕዝብ የሚያስገኙትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ በዚህ ዝግጅት እናስቃኛለን፡፡

በሲዳማ ክልል የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማህበራት ወጥ የሆነ የአደረጃጀት፣ የምዝገባ እና የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶላቸው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ 2 ሺህ 447 ህብረት ሥራ ማህበራት አሉ። እነዚህ ማህበራት በግብርና፣ በገንዘብ ቁጠባ፣ በሸማችና በሌሎች የተደራጁ ሲሆን 485 ሺህ 959 አባላት አሏቸው። ካፒታላቸውም 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መድረሱን የክልሉ ህብረት ሥራ ልማት ኤጄንሲ መረጃ ያሳያል፡፡

የሲዳማ ክልል ህብረት ሥራ ልማት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ሀጢሶ እንዳሉት ኤጄንሲው የህብረት ሥራ ማህበራትን የማደራጀት፣ የማጠናከር፣ እንዲቆጥቡ የማድረግ፣ አደረጃጀታቸውን የማስተካከልና የመከታተል፣ ትስስር የመፍጠር፣ ገበያ የማረጋጋት እንዲሁም ምርት ከሚበዛበትና ተመጣጣኝ ዋጋ ካላቸው አካባቢዎች የተሻለ ዋጋ ወደሚያወጣበት አካባቢ እንዲቀርብ የማድረግ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

የህብረት ስራ ማህበራት የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ቁልፍ ከሆኑ የልማት ሃይሎች መካከል ዋነኞቹ በመሆናቸው ለህብራት ስራ ማህበራት የሚያስፈልጓቸውን ድጋፍና እገዛዎች እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

በህብረት ሥራ ልማት ኤጄንሲው የህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደንበሎ ዳንጊሶ በበኩላቸው ማህበራት ግለሰቦች መፍታት ያልቻሉትን በጋራ ሆነው ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንደሚደራጁ እና ማህበራቱም አለም አቀፍ መርሆችና እሴቶች ያሉት ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ህብረት ሥራ ማህበራት መሰረቱ የሚጀምረው ከማደራጀት ነው” ያሉት አቶ ደንበሎ በክልሉ የተደራጁ ማህበራት የመጀመሪያ ደረጃ ህብረት ሥራ ማህበራትና ሁለተኛ ደረጃ የምንለው ዩኒየን በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህን ከማደራጀት በመነሳት የማጠናከር፣ የማስፋፋትና የመደገፍ ሥራ ይሰራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሂሳብ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ እንዲሁም ቁጠባቸውን እንዲያሳድጉ ይሰራል ብለዋል፡፡

በሰብል ምርት፣ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቁጠባ፣ በወተትና ወተት ተዋጽኦ፣ በሸማቾች የተደራጁ አጠቃላይ በአስር ዩኒየኖች አማካይነት አምራቾች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 63 ማህበራት በተለያዩ ዘርፎች መደራጀታቸውን የተናገሩት አቶ ደንበሎ የአደረጃጀት አፈፃፀሙ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና አዲሶቹንና ነባሮቹን የማጠናከርና የመከታተል ሥራው በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የህብረት ስራ ማህበራት የአምራች አርሶ አደሩንም ሆነ የማህበረሰቡን ወቅታዊና ዘላቂ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ሚናው ከፍተኛ ቢሆንም ሁሉም ዜጋ የህብረት ሥራ ማህበራት አስፈላጊነት ላይ ያለው ግንዛቤ እኩል ባለመሆኑ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ላይ በትኩረት መስራትን ይጠይቃል፡፡

ከዚህ አኳያ አሁን ላይ የክልሉ ህብረት ሥራ ልማት ኤጄንሲ ከፌደራል ጋር በመሆን የሪፎርም ሥራ እየሰራ ነው፡፡ የሪፎርሙ አስፈላጊነትም በማህበራት ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣት ያለውን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት ውጤታማ ለማድረግ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሥራን ለማዘመን እና በተማረ የሰው ኃይል ለመመራት ያስችላል ሲሉ ነው አቶ ደንበሎ ያስረዱት፡፡   

በኤጄንሲው የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርት ግብይት ባለሞያ የሆኑት ወ/ሮ ነፃነት ሙሉጌታ እንዳሉት የህብረት ሥራ ማህበራት ለግብርና ምርት እድገት የሚያገለግሉ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩን ተደራሽ በማድረግ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። የግብርና ምርት ግብይት ህብረት ሥራ ማህበራት የሚያመርቱትን ምርት ወደ ገበያ የማቅረብ እንዲሁም የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ ይሰራል። ለማሳያነትም የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ከዱቄትና ከሳሙና ፋብሪካዎች ጋር በማገናኘት ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ በማቅረብ የበያ የማረጋጋት ሥራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡ 

ማህበራቱ የሀገሪቱን የውጭ ግብይት በማሳደግ ረገድ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛል ያሉት ባለሞያዋ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡናን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት የጎላ ድርሻ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር በቡና ምርት ግብይት በአመቱ 59 የቡና ማህበራት ወደ ግብይት መግባታቸውን አውስተው በግማሽ አመቱ ከ 82ዐ ቶን በላይ ቡና ለውጪ ገበያ በመላክ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት ተችሏል፡፡ ቀደም ሲል ከባንክ የሚገኘው ገንዘብ በበቂ ደረጃ ባለመገኘቱ ከሲዳማ ቡና ዩኒየን 370 ሚሊዮን ብር ብድር በማመቻቸት ነው ወደ ግብይት የተገባው፡፡

ወ/ሮ ነፃነት የፋይናንስ ብድር ለህብረት ሥራ ማህበራት ማነቆ እንደሆነ ገልጸው በባንክ ህግ መሰረት የሚያስይዙት ቢኖራቸውም ብድር ለማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡ ማህበራት በቂ ፋይናንስ አግኝተው የተመረተውን ምርት ለገበያ ካቀረቡ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የገለጹት ባለሞያዋ ይህም ህገ ወጥና አላስፈላጊ ቅብብሎሽን በማስቀረት ህብረተሰቡን ከኑሮ ውድነት ማዳን ይቻላል ብለዋል፡፡ ይህን በመረዳት አበዳሪ ተቋማት ለህብረት ሥራ ማህበራት የተለየ ትኩረት ቢሰጡ የተሻለ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ይህም አምራቾች በህገ ወጦች እንዳይበዘበዙ እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን እንዲቋቋሙ የሚረዳ ሲሆን በተጨማሪም የዘይት አምራች ኢንዱስትሪ ፓርኮች በቂ ምርት እንዲሰበስቡ ያስችላቸዋል፡፡

ማህበራት ለአምራች አርሶ አደሩ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው የጠቀሱት ባለሞያዋ የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር፣ አርሶ አደሩ ላመረተው ምርት ተመጣጣኝ ዋጋ ያገኛል ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር አዲስ ባወጣው የግብይት ትስስር አዋጅ መሰረት የኮንትራት ፋርሚንግ ውል ከገቡት ውስጥ 32 የህብረት ሥራ ማህበራት ለኢንዱስትሪ ፓርክ 870 ቶን የአቮካዶ ምርት አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም ከ78 ሺህ ሊትር በላይ ወተት የቀረበ ሲሆን በዚህም 34 ህብረት ሥራ ማህበራት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እሁድ ገበያን በማስፋፋት በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡

የገበያ ትስስርን በተመለከተ መጀመሪያ የምርት ልየታ የሚሰራ ሲሆን በዚህም ማህበራቱ ከሚያመርቱት ምርት የገበያ ችግር ያለበት የትኛው እንደሆነ በመለየት የገበያ ትስስር ይሰራል፡፡ በተለይ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ቅድሚያ አማራጭ ስለሆነ ትስስሩ ከፓርኩ ይጀምራል፡፡ በዚህ መሰረት ለ54 ማህበራት ውል ተገብቶ ትስስር ተሰርቶላቸዋል፡፡ አሁን ላይ በቂ ነው ባይባልም የተሻለ ዋጋ እንዲገኝ እየተሰራ ነው፡፡

ከህገ ወጥ ግብይት ጋር ተያይዞ ችግሮች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን አርሶ አደሩ ያልተገባ የዋጋ ቅናሽ እንዳያጋጥመው እስከ ምርቶችን የሚረከቡ አካላት ጋር ትስስር ተፈጥሯል፡፡ ከኢትፍሩትና ሌሎች ተመሳሳይ ተረካቢ ድርጅቶች ጋር ትስስር በማድረግ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ምርቱን ማቅረብ ይጀመራል፡፡

ገበያ ትስስሩ በዋናነት የሚሰራው በአትክልትና ፍራፍሬ አቮካዶ እና አናናስ ላይ እንዲሁም  ለወተት ስድስት ማህበራት ትስስር የተመቻቸ ሲሆን ተጨማሪ ውል ለመግባት ቀጠሮ ላይ ያሉም ይገኛሉ፡፡ ሌላው የቢራ ገብስ ለሚያመርቱ አርሶ አደሮች በቀድሞ አሰላ ብቅል ፋብሪካ የአሁኑ የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ፌደሬሽን ለገዛው ፋብሪካ ለማቅረብ ለአራት ማህበራት ትስስር ተደርጓል፡፡ 

እንደ ባለሙያዋ ገለፃ ሰብል ግብይት ላይ ሲዳማ አሊቶ ዩኒየን አባል ማህበራት በቆሎና ቦሎቄ ምርት የሚያቀርብ ሲሆን ዩኒየኑ ደግሞ ለአለም ምግብ ፕሮግራም፣ ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነትና ለሌሎችም ያቀርባል ብለዋል፡፡

የህብረት ሥራ ማህበራት የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ከሚያደርጉት ተግባር በተጨማሪ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በሚደረገው ጉዞ ጉልህ ድርሻ እየተጫወቱ በመሆናቸው ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ በማመቻቸት ለሀገር ኢኮኖሚ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መስራት ያስፈልጋል፡፡