ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ወጣቱ በአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሌሞ ጌንቶ ኮንስትራክሽንና ኢንዲስትሪያል ኮሌጅ አስታወቀ።
ኮሌጁ ለሁለተኛ ጊዜ በአምስት የሙያ ዘርፎች ከ2 መቶ በላይ ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ ይገኛል።
አሁን ላይ ኮለጁ በደረጃ 1 እና 2 ስልጠናውን እየሰጠ ያለ ሲሆን ዘርፎቹም የአካባቢውን ማህበረሰብ መሠረታዊ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድረጎ እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በኮሌጁ ስልጠና እያገኙ ካሉ ተማሪዎች መካከል ተማሪ መስከረም ቶጰያና ማርታ ታምራት ከዚህ ቀደም ወደ ወላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭና ጂንካ ከተሞች በመሄድ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የሚያገኙትን የትምህርት ዕድል በአቅራቢያቸው በማግኘታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት የተሻለ ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በ2015 በጀት አመት ከደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም በአምስት ሙያ ዘርፎች ፈቃደ አግኝቶ ስልጠና የጀመረው የሌሞ ጌንቶ ኮንስትራክሽንና ኢንዲስትሪያል ኮሌጅ አሁን ላይ ከሁለት መቶ በላይ ሳልጠኞችን ተቀብሎ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እያሰለጠነ እንደሚገኝ የኮሌጁ ዲን አቶ ባሕሩ ሙላት ተናግረዋል።
ተቋሙ ከመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ ከ30 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ጠቁመው በቀጣይ ኮለጁ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ መስኮች ላይ አጫጭር ስልጠናዎችን በመሰጠት የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ የፈጠራና የክህሎት ስልጠና እየሰጠ ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አቶ ባሕሩ ሙላት አሰረድተዋል።
በግቢው ውሃ አለመኖርና ሌሎች የግበዓት ችግሮች የተቋሙን ዓላማ ለማሳካት ማነቆ መሆናቸውን ጠቁመው መንግስታዊና መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ለኮሌጁ ድጋፊ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በማህበረሰቡ ዘንድ ይስተዋሉ የነበሩ ነባር ችግሮችን መቅረፍ የቻሉ ቴክኖሎጂዎች እያቀረበ መሆኑን የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ
ሃገሪቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የያዘችውን ውጥን በማሳከቱ ረገድ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራችዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተገለጸ
ዜጎች የተሻለ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ማንኛውም ተግባር እንዲያሳልጡ መንግስት ከሚሠራው በተጨማሪ የልማት አጋር አካላት ተግባር ወሳኝ መሆኑን የኣሪ ዞን አስታወቀ