ገበያውን ለማረጋጋት

በገነት ደጉ

አሁን አሁን በየአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው ሀብት ንብረት ሲያፈሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ወጣቶች ስራ ከመንግስት ጠባቂ የነበሩበት ወቅት እያከተመ የሄደ ይመስላል። ወጣቶች የመንግስት ስራ መጠበቅ በዚህ ኑሮ ውድነት አስፈላጊ አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ እኛም ሰሞኑን በጌዴኦ ዞን ገደብ ከተማ  በማህበር ተደራጅተው በጓሮ አትክልት እና በሰብል ማምረት ውጤታማ የሆኑ ወጣቶችን በአካል ተገኝተን  ተመልክተናል፡፡

ወጣት የሱፍ ዳውድ ይባላል፡፡ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ መሰናዶም ይሁን ወደ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ኮሌጅ ሊያስገባው የሚችል ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ነው የሚናገረው፡፡

ውጤት አልመጣልኝም ብሎ እጅ እግሩን አጣጥፎ መቀመጥን ግን አልመረጠም፡፡ ነገ ሌላ ቀን ነው ይላል፡፡ በስራ እራሱን መለወጥ እንደሚችልም ሙሉ እምነት እና በራስ መተማመን ነበረው፡፡

በገደብ ኢንዲስትሪያል ኮሌጅ ውስጥ ሰፊ ማሳ በመኖሩ ስራ አጥ ከመሆን ይህን ሰፊ ማሳ እናልማ፡፡ ለምን አንሰራም በማለት ከመሰል ጓደኞቹ ጋር  የመስራት ዕድሉን አግኝቶ  ወደ ስራ መግባቱን  ነው ያስታወሰን፡፡

ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ ግን በጥቃቅንና አነስተኛ በማህበር አምስት ወጣቶች መደራጀታቸውን ጠቁሟል፡፡ በዚህም የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ መንግስት በየተቋማቱ ባሉ ሰፋፊ ማሳዎች ላይ ማምረት እንዲቻል በተፈጠረው ዕድል ከመሰል ጓደኞቹ ጋር እራሱን ለመለወጥ ደፋ ቀና እያለ ስለመሆኑ ነው የሚናገረው፡፡

በማህበሩ ውስጥ ለአንድ ሴት እና አራት ወንዶች በድምሩ ለአምስት ወጣቶች የስራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን በተሰጣቸው አንድ ሄክታር መሬት በቆሎ እና ስንዴ ማምረት ችለዋል፡፡ ለመነሻ ይረዳቸው ዘንድ ዘር እና ማዳበሪያ በመንግስት እገዛ  ተደርጎላቸዋል፡፡ ወጣት ሳሙኤል ሀሮ በበኩሉ በ2015 ዓ.ም እርሱን ጨምሮ ስምንት ወጣቶች በጓሮ አትክልት ልማት ስራ መደራጀታቸውን ይገልፃል። የስራ ዕድል የፈጠረላቸው የገደብ ከተማ ኢንተርፕራይዝና የስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት መሆኑን ነው የገለፀው፡፡

ወደ ስራው ከመግባታቸው በፊት በቂ የክህሎት ስልጠና እንደተሰጣቸው የተናገረው ወጣት ሳሙኤል  ቦታውን የገደብ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ያስረከባቸው ሲሆን የጓሮ አትክልት ዘርና ግብዓት የኢንተርፕራይዙ ጽህፈት ቤት እንዳቀረበላቸው ነው የሚናገረው፡፡ አሁን ላይ እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ከተማው ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የኑሮ ውድነት እንዳለ የሚናገረው ወጣቱ ለቤተሰብም ይሁን ለአካባቢው ህብረተሰብ በበቂ ሁኔታ አትክልት እያቀረቡ ስለመሆናቸው ነው የገለፀው፡፡ ወጣቶች የራሳቸውን ሀብትና ንብረት  እንዴት ማፍራት እንዳለባቸው ስልጠና እየተሰጣቸው ስለመሆኑ የሚያስታውሰው ወጣት ሳሙኤል ሁልጊዜ መንግስትን ከመጠበቅ እሳቤ መውጣት እንዳለባቸው ነው መልዕክቱን ያስተላለፈው፡፡ 

የገደብ ከተማ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስምምነት ተሰማ በ2016 ዓ.ም ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው ተግባራቱን ለማስጀመር በሶስት ዘርፍ ወጣቶች እንዲደራጁ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በዚህም በ2016 ዓ.ም 1ሺ2 መቶ 12 ስራ አጥ ወጣቶች መለየታቸውን ተናግረው በልይታው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ 4 መቶ 13 ወጣቶች ወደ ስራ ገብተው ውጤታማ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡ 

በየዘርፉ ለወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመስጠት ዓላማውን አውቀው እና አምነው ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራዎችን በስፋት መስራታቸውን የሚያስታውሱት አቶ ስምምነት በከተማ ግብርና የተሰማሩ ወጣቶች በ21 ማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ ወጣቶች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት ከግብርና ጽህፈት ቤት ጋር በቅንጅት  ስልጠና መስጠታቸውን የሚናገሩት አቶ ስምምነት በዚህም እንዴት ሰርተው ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ የህይወት ክህሎት ስልጠና አግኝተዋል ብለዋል፡፡

ወጣቶችን ተቋሙ በቋሚም ይሁን በጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ያደራጃቸው ሲሆን መንግስት ለ21 ማህበራት መሬት እና ዘር በማቅረብ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ነው የተናገሩት፡፡ የስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ወደ 3 መቶ ሺ ብር በማውጣት የዘር ግዥ ድጋፍ  እንዳደረገላቸው አውስተው ወጣቶቹ በተቋማት ውስጥ ባሉት ክፍት የስራ   ቦታዎችን ወደ ምርታማነት ከማሳደግ በዘለለ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውን ነው ያጫወቱን፡፡

በተለይም ዘንድሮ ድጋፍ የተደረገላቸው ማህበራት በጓሮ አትክልት፣ ስንዴ እና በቆሎ በማምረት የተደራጁ ሲሆን  በስንዴ ለተደራጁ ለሶስት ማህበራት ደግሞ አምስት ሄክታር  መሬት እና አራት ኩንታል ተኩል ዘር እንደተሰጣቸው ነው የገለፁት፡፡

ለውጤታማነቱ ከግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ጋር በየወቅቱ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው የተናገሩት ኃላፊው ከቅድመ ዝግጅት እስከ አዝመራ ወቅት ድረስ ክትትል እንደተደረገላቸው አመላክተዋል፡፡ በቆሎ በማምረት  የተደራጁ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን የተናገሩት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ በስንዴ ላይ ከተከሰተው በሽታ አንፃር ስጋቶች ቢኖሩም እንኳን ርጭት ከተደረገ በኋላ ጥሩ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ ምልከታ ማድረጋቸውን ነው የገለፁት፡፡

በዘንድሮው ዓመት በወጣቶች የተሸፈነው ማሳ ከከተማው አልፎ ለሌሎች አጎራባች አካባቢዎች  ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት  የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ በተለይም በመሰናዶ ትምህርት ቤት እና በኢንዱስታሪያል ኮሌጁ ላይ የተዘራው ስንዴ ውጤታማ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ ከቲቪቲ ኮሌጅ ጋር ባለው ግንኙነት  የተዘራው ሰብል ከተነሳ በኋላ በቀጣይ በስንዴ ብቻ ሙሉ ኮሌጁን ቢጠቀሙ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ያስረዱት ኃላፊው መንግስት በያዘው አቅጣጫ መሰረት ስንዴን ከዚሁ ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ነው የጠቀሱት፡፡

ኮሌጁ ሰፊ ቦታ ከመያዙ ጋር ተያይዞ ወጣቶች ትምህርታቸውን ጨርሰው ስራ አጥ ሆነው በአልባሌ ቦታዎች ከመዋል ይልቅ በማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ ኃላፊነት እንዲወስድ እና ከኮሌጁ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ደግሞ በተማሩት ሙያ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው የማድረግ ስራዎችን መስራት እንዳለበትም ከኮሌጁ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውን ነው የገለፁት፡፡በኮሌጁ ያሉ መምህራን ማስተማር ብቻ ሳይሆን እሰከታች ወርደው ከማህበረሰቡ ጋር በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተመረቁ ተማሪዎችን እንዲደግፉ መስማማታቸውን አስታውሰው በተለይም በግብርናው ላይ በዶሮ እና በከብት እርባታ ዘርፍ ተረፈ ምርቶች ስላሉ ትኩረት ሰጥተው እንሚሰሩም ነው ያስረዱን።