“የምሁራን የጥናት ውጤት የመልማት አቅምን የሚያጎለብት ነው” – አቶ አበራ አርፊጦ
በደረሰ አስፋው
ውድ አንባቢያን የዛሬው የንጋት እንግዳችን የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ ናቸው፡፡ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ለበርካታ አመታት እራስን በራስ የማስተዳደር የመዋቅር ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቶ በቅርቡ ምላሽ አግኝቷል፡፡ በዚህም ልዩ ወረዳው የህዝቡን የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ? ለማደግ ምን እድሎች አሉት? የሚሉትን እና ሌሎች ተያያዥ ሀሳቦች በማንሳት ከዋና አስተዳዳሪው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ንጋት፡- ለቃለ መጠይቁ ስለተባበሩን በቅድሚያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አበራ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመስግናለሁ፡፡
ንጋት፡ በመተዋወቅ እንጀምር?
አቶ አበራ፡- አቶ አበራ አርፊጦ እባላለሁ። የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ነኝ። የተወለድኩት ጠምባሮ ልዩ ወረዳ፣ ሰሜን አምቡኩና ቀበሌ፣ ዋሊያ ጎጥ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ሰሜን አምቡራ ትምህርት ቤት፣ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን ደግሞ ሶያሜ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት። ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ጊምቢቾ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ፡፡ ከሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በቋንቋና ሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ዲፕሎማዬን አግኝቻለሁ፡፡ መንግስት ባመቻቸልኝ የስራ ላይ የትምህርት ዕድል ከዲላ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በትምህርት አመራር፣ ከሶዶ ዩኒቨርስቲም በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ 2ኛ ዲግሪየን አግኝቻለሁ፡፡
ንጋት፡- የስራ ቆይታዎን ቢገልጹልኝ
አቶ አበራ፡- ለ10 ዓመታት በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት በሶያሜ አገልግያለሁ፡፡ የቴክኒክና ሙያ ኃላፊ፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ፣ የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግያለሁ፡፡ በአጠቃላይ በኃላፊነትና በባለሙያነት ለ30 ዓመታት ያህል ህዝብን አገልግያለሁ፡፡ በአሁን ወቅት ደግሞ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
ንጋት፡- የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ቀደም ሲል በወረዳነት የተዋቀረው ከመቼ ጀምሮ ነው?
አቶ አበራ፡- ወረዳው ቀደም ሲል ከሌሎች ወረዳዎች ጋር ተጠቃሎ ይኖር ነበር፡፡ በ1985 ዓ.ም የኦሞ ሸለቆ ወረዳ በመባል በከምባታ ጠምባሮ ዞን ውስጥ ተዋቅሮ ነበር፡፡ የዶንጋ ወረዳ እራሱን ችሎ ሲወጣ የጠምባሮ ወረዳ በከምባታ ጠምባሮ ዞን ከተዋቀሩ ወረዳዎች መካከል አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ የጠምባሮ ወረዳ ተብሎ ሲጠራ ሌሎች ቀበሌዎችን ጭምር ያካተተ ነበር፡፡
ንጋት፡- የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የልዩ ወረዳነት መዋቅር ያገኘው ከመቼ ጀምሮ ነው?
አቶ አበራ፡- የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የልዩ ወረዳነት መዋቅር ሲጠይቅ የቆየው ለረጅም አመታት ነው፡፡ ኢህአዲግ ሀገሪቷን በ1983 ዓ.ም ሲቆጣጠር ከሀዲያ ጋር አብሮ ዋና ከተማውን ጊምቢቾ ላይ አድርጎ ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ተብሎ የመካለል ጥያቄ ነበረው፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜው የነበረው አስተዳደር ውይይት አድርጎ ከምባታ፣ ሀላባና ጠምባሮን አንድ ላይ አድርጎ ከምባታ ሀላባ ጠምባሮ ዞን በሚል ተዋቀረ፡፡ ህዝቡ በዚህም መዋቅር ባለመስማማቱ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር በሚል ለረጅም ዓመታት ጥያቄ ሲያነሳ ነበር። ከክልል እስከ ፌደራል መንግስት፣ ህዝብ በወከላቸው ሽማግሌዎች አማካኝነት ጥያቄዎች ሲቀርቡ ቆይቷል፡፡ የነበረው ጥያቄ በተደጋጋሚ በዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ምክር ቤቶች ተወስኖ በሰላማዊ መልኩ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳ ነበር፡፡
በዚህም የብልጽግና ፓርቲ ለጥያቄው አፋጣኝ ምላሽ ሰጥቶ ክልሉ ለሁለት ሲከፈል የጠምባሮ ህዝብም በልዩ ወረዳነት የመደራጀት የመዋቅር ጥያቄ አብሮ ምላሽ አግኝቷል፡፡ ነሀሴ 13 አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሲደራጅ አስቀድሞ ምላሽ የሰጠው ለጠምባሮ ልዩ ወረዳ ህዝብ ነው፡፡ ህዝቡም በምላሹ ደስታ ተሰምቶታል፡፡ አጎራባች የሆኑ አካባቢዎችም አብረው የተደሰቱበት ነው፡፡ በሰላማዊ መልኩ ተጠይቆ በሰላማዊ መልኩ ምላሽ ያገኘ በመሆኑ የሚደነቅ ነው፡፡
ንጋት፡- የጠምባሮ ልዩ ወረዳ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ማቅረብ ያስፈለገበት መሰረታዊ ጉዳይ ምንድን ነው?
አቶ አበራ፡- ከዚህ በፊት የስልጣን ክፍፍሉ ፍትሃዊ አልነበረም፡፡ የሀብት ክፍፍልም በተመሳሳይ ፍትሃዊነት የጎደላቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ በመንግስት የሚሰሩ የልማት ተግባራትም የፍትሃዊነት ችግር ነበረባቸው። ጥያቄው የመነጨው ከነዚህ መብቶች መጓደል ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደርና በራስ አቅም የመልማት ጥያቄ ነው ማለት ነው። እራስን በራስ ማስተዳደር ማለት እነዚህን ማነቆዎች መቅረፍ ነው፡፡ ሌላው በራስ አቅም ሀብት አመንጭቶ ማልማት ነው፡፡ የህዝቡ የዘመናት ጥያቄዎች በመመለሳቸው እራስን በራስ በማስተዳደር በራስ አቅም ለመልማት የሚያስችል ዕድል የሚፈጥር ሆኖ ነው የታየው፡፡
ንጋት፡- የልዩ ወረዳነት መዋቅር ጥያቄ ምላሽ ካገኘ በኋላ የተሰሩ ስራዎች ምንድናቸው?
አቶ አበራ፡- አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መቀመጫውን ካደረገ በኋላ ምን ሀብቶች አሉ? ምንስ ዕድሎች አሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት አቅጣጫ ተቀምጦ ነው ወደ ስራ የተገባው፡፡ ይህ ዕድል ለእኛ ጠቃሚ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ ከክልሉ አደረጃጀት ጋር ተያይዞ እኛም ልምድ እየቀሰምን ተግባራትን እናከናውን ዘንድ አግዞናል፡፡ በልዩ ወረዳነት ስንዋቀር የእኛን ቁርጠኝነት እና አንድነት የሚጠይቁ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩብን። ከበጀት ውስንነት፣ ከደመወዝ ክፍያ ጋር የተያያዙ፡፡ የልዩ ወረዳነት አደረጃጀት ሲሰጥ ብዙ እዳም አብሮ ነው የመጣው፡፡ በመሆኑም ይሄን እዳና የወደፊቱን ተስፋ እንዴት አድርገን ማስማማት እንችላለን በማለት አቅደን እየሰራን ነው፡፡
ልዩ ወረዳነት በእርግጥም ያስፈልጋል፤ ዕድልም ነው ብለን ነው የተቀበልነው፡፡ ህዝቡ እራሱን በራሱ ማስተዳደር በልማት ካልተደገፈ ትርጉም የለውም፡፡ ለዚህም በመቶ ቀን ዕቅዳችን ውስጥ አካተን እየሰራን ነው። ከአመራሩና ከህዝቡ ጋር ውይይት አድርገን ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ የልዩ ወረዳነት ጥያቄው ምላሽ ባገኘ ማግስት ጀምሮ የተሰሩ ስራዎች በርካታ ናቸው፡፡ በሙዱላ ከተማ በቅርቡ የተሰሩ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ከፈታ፣ ከተማውን የማስዋብ የልማት ስራዎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ የአካባቢው ተወላጆች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች እና የንግዱን ማህበረሰብ በማሳተፍ ህዝቡ የጠየቃቸው የልማት ጥያቄዎች እውን እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡ ህዝቡ ከልዩነት ወደ አንድነት የመጣበት ነው፡፡ የዘመናት የመብራት መቆራረጥ ችግር እንደነበረው የሀይል መስመሩን ወደ ሶዶ አቅጣጫ በመቀየር ችግሩ የተቀረፈው አሁን ነው፡፡ መብራት ከገባበት ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ሲጠየቅ የነበረው ይህ ጥያቄ በአንድ ሳምንት ነው ምላሽ ያገኘው፡፡
ዛሬ ላይ የሙዱላና ሌሎች የልዩ ወረዳው ከተሞች የመብራት መቆራረጥ ችግር ተቀርፏል፡፡ በተመሳሳይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ነው፡፡ የለማው የውሃ አቅም ከሙዱላ ከተማ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ነው፡፡ በቴክኒክ ችግር የመቆራረጥ አዝማሚያዎች ቢኖሩም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የመቶ ቀን ዕቅዳችን አካል አድርገን እየሰራን ነው፡፡ አዳዲስ መስመሮች እየተዘረጉና የነበሩትንም በመጠገን በከተማው በሁሉም አቅጣጫዎች ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በመቶ ቀን እቅዳችን የመብራት ችግር እንደፈታነው ሁሉ በቀጣዩም የውሃ መቆራረጥ ችግር ይቀረፋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ለውጦች የመጡት የልዩ ወረዳው ጥያቄ ምላሽ ካገኘ ማግስት ጀምሮ በተፈጠረ መነሳሳት ነው።
ንጋት፡- በልዩ ወረዳው የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችስ ምን ይመስላሉ?
አቶ አበራ፡- የስራ አጥ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ እንደሀገር ችግር እንደሆነ ሁሉ በልዩ ወረዳውም ትልቅ ችግርና ስጋት ነው፡፡በርካታ ምሩቃን ወጣቶች ያሉበት ልዩ ወረዳ ነው፡፡ ብዙ የተማረ የሰው ሀይል ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ለስራ ዕድሜው ደርሶ ስራ ያጣም እንዲሁ አለ፡፡ በልዩ ወረዳው አሳሳቢ ብለን ከለየናቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይህን ችግር እንዴት መቅረፍ ይቻላል? በማለት ውይይት አድርገናል፡፡
ከዚህ በፊት በገጠር በእርሻ ዘርፍ፣ በእንስሳት እርባታና በንግድ ተደራጅተው ብድር ወስደው የተሰማሩ አሉ፡፡ የተበደሩትን ገንዘብ ግን አልመለሱም፡፡ ብዙ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ሀብት በሰዎች እጅ አለ፡፡ ይህንን ሀብት የማስመለስ ስራ በ2ኛው የመቶ ቀን እቅዳችን ውስጥ አስገብተናል። ያለው ሀብት ካልተሰበሰበ ከየትም አይመጣም። በከፍተኛ ንቅናቄ ሀብቱን የማሰባሰብ ስራ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ጎን ለጎን ስራ አጥ ወጣቶችን የመለየትና የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው፡፡
መሬት ወስደው ያልመለሱ አሉ፡፡ መሬቱን ከነዚህ በማስመለስ የተመለሰውን መሬት ወጣቶችን አደራጅቶ በእርሻ፣ በንብ ማነብና በእንስሳት እርባታ እንዲሰማሩ እየተሰራ ነው። የስራ አጥነት ጉዳይ ከአምስቱ የትኩረት መስኮች አንዱ ሆኖ የሚሰራበት ነው፡፡
ንጋት፡- የሙዱላ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አበራ፡- የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ትልቁ አቅምና ሀብት ያለው ሙዱላ ከተማ ላይ ነው። ሌሎቹም ሳይዘነጉ ማለቴ ነው፡፡ ከተማዋ ያለባትን የፕላን ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ነው፡፡ ከህዝቡ ጋር ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ የመንገድ ከፈታውና የፕላን ችግሩን ከፈታን ከተማው የተፈለገውን ሀብት ያመነጫል፡፡ ከዚህም ያለውን የገቢ አቅም አሟጦ በመጠቀም የተፈለገውን ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መፍታት ይቻላል፡፡
ገቢ ከሌለ ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም። በዚህ አመት በህዝብ ተሳትፎ ከመንገድ ከፈታው ጎን ለጎን የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የውሃው ችግር እየተፈታ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ በከተማው የመብራት የሀይል እጥረትን ለመቅረፍም ተጨማሪ 2 ትራንስፎርመሮች የመግዛት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ የስልክ ኔት ወርክ ችግርንም ለመቅረፍ ከሶዶ ዲስትሪክት ጋር ተነጋግረን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ እነዚህ ችግሮች ከተቀረፉ የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ይመለሳሉ፡፡ በዚህም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው፡፡ የሙዱላ ከተማም የምትለወጥበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እምነት አለኝ፡፡
ንጋት፡- የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመልማት አቅም እስከምን ድረስ ነው?
አቶ አበራ፡- የወደፊት የልዩ ወረዳው የመልማት አቅም ምን ያህል እንደሆነና ምንስ ሀብቶች እንዳሉት ጥናት እየተደረገ ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ወደ ልዩ ወረዳው ገብተው አጥንተው ዶክመንት የመሰነድ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ጥናት ተደርጎ ወደ ተግባር ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ያሉ ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡ የወረዳው ሀብት በዘላቂነት ተመርቶ ወደ ገበያ የሚቀርብበት ዕድል አልነበረም፡፡ ቡና እና ዝንጅብል በስፋት ይመርታል፡፡ ነገር ግን ወደ ማዕከላዊ ገበያ አይቀርብም፡፡ መዳረሻው ሌላ ቦታ ነው፡፡ ለዚህም ችግር ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም ቡናን ወደ ማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ባለሀብቶች እራሳቸውን ጠቅመው በአካባቢው ልማት ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ተቀናጅተን የምንሰራበትን መንገድ ዘርግተናል፡፡
ይህን እድል በስፋት ለመጠቀም የቡና የችግኝ ጣቢያዎችን በማስፋፋት ቡናን በስፋት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ሌላው በቅመማ ቅመም ዘርፍም ከፍተኛ የዝንጅብል ምርት በየአመቱ ይመረታል፡፡ ይህንም ምርት በሚፈለገው መጠንና ጥራት ማምረት እንዲቻል ተገቢ ባለሙያዎችን የማፍራት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በርካታ የልዩ ወረዳው ህዝብ ህይወቱን የሚቀይረው በዝንጅብል ምርት ስለሆነ፡፡ እነዚህ ሀብቶች ውጤታማ የሚሆኑት ህጋዊ የንግድ ሰንሰለትን ሲከተሉ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ከማዕከላዊ ገበያ ጋር ትስስር መፍጠር ይገባል፡፡
ከዚህ ሌላ ሰፋፊ ለአልሚዎች ምቹ የሆኑ የእርሻ መሬቶች አሉ፡፡ እነዚህንም በአግባቡ በማስተዳደር በተፈለገው ልክ ለምተው የሚፈለገውን ገቢ እንዲያመነጩ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህንንም ለማድረግ አልሚዎች የወሰዱትን መሬት በሙሉ አቅማቸው እንዲያለሙ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ የስራ ዕድል ለመፍጠር አማራጭ ዘርፍ በመሆኑ ማበረታቻም ይደረጋል፡፡
በቅርቡም አንድ አልሚ ባለሀብት 750 ሄክታር መሬት ተረክቧል፡፡ ለዚህም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ስራውን ለማሳደግና አልሚዎችን ለመሳብ ጥረት ተደርጓል፡፡ የሚያመርቷቸው ምርቶች በቀጥታ ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች ናቸው፡፡ ይህም ከአካባቢው አልፎ ለሀገርም ዘላቂ የሀብት ምንጭ የሚሆን ነው፡፡ ሌላው የልዩ ወረዳው የመልማት ተስፋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ካጠናቸው ጥናቶች መካከል ከፍተኛ የዓሳ ሀብት መኖሩ ነው፡፡ አካባቢው ይህን ሀብት ለገበያ ለማቅረብ ቅርበት አለው፡፡ ተደራጅተው ሲሰሩ የነበሩትን ወጣቶች ማጠናከር እና ማዘመንም ይገባል፡፡ የአካባቢውንም የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በጥናቱም የዓሳ ምርትን ከአካባቢው ዉጪ ከመላክ ባለፈ የአመጋገብ ባህሉ እንዲያድግ ጭምር አቅዶ የመስራት እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ፡፡ የጊቤ ግድብ ጥሩ በረከት ይዞ የመጣ ነው፡፡ ይህን መጠቀም ደግሞ ከኛ ይጠበቃል፡፡
ሌላው በጥናት የተረጋገጠው የድንጋይ ከሰል ማዕድን ነው፡፡ ከፍተኛ ምርት እንዳለም የማእድን ሚኒስቴር በጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ይህም ለገበያ የሚውልበት አማራጭ ቢፈለግ ሌላው የመልማት አቅማችን ነው ማለት ይቻላል፡፡ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ በእርሻው ዘርፍ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ክረምት ከበጋ የሚፈሱ የበርካታ ወንዞች ባለቤትም ነው፡፡ በቱሪዝም ሀብትም እምቅ ሀብት አለው። የሚገነቡ የአስፓልት መንገዶችም ልዩ ወረዳውን ከተለያዩ ክልሎችና ዞኖች ጋር የሚያገናኙ በመሆናቸው የልማት ኮሪደርን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ምርቶችን ለመለዋወጥ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህም ለጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመልማት አቅምን የሚፈጥር ነው፡፡
ንጋት፡- ልዩ ወረዳው ያለውን እምቅ ሀብት ለአልሚዎች ከማስተዋወቅ አኳያ እየተሰራ ያለው ስራ ምን ይመስላል?
አቶ አበራ፡- የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት እስካሁን በነበረው መዋቅር ከሌሎች ሴክተሮች ጋር ተደርቦ ነበር የሚሰራው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ጽ/ቤቱን እራሱን ችሎ ማዋቀር ይገባል፡፡ በአመራርና በባለሙያዎች በማደረጃት ስራውን በኃላፊነት እንዲወጣ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ የተቋሙ መደራጀትና ስራውን መጀመር ከላይ የጠቃቀስናቸውን ሀብቶች በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ለማልማት ዕድል ይፈጥራል፡፡
ንጋት፡- የልዩ ወረዳው መስተዳደር አደረጃጀት ብዝሃነትን ያከበረ ነው ይላሉ?
አቶ አበራ፡- የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ብዝሃነትን ማክበር ውዴታ ሳይሆን የግዴታ ነው፡፡ አንድ ብሄረሰብ ያለው ቢሆንም በርካታ ማንነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉበት አካባቢ በመሆኑ ይህን ያካተተ ብዝሃነት ያለበት አስተዳደር መመስረት የግድ ነው። በእኩልነትና በፍትሃዊነት የስልጣን ክፍፍል ማድረግ ይገባል፡፡ ይህን ስርዓት ያልዘረጋ መዋቅር መሻገር አይችልም፡፡ ጊዜው በውስን የቤተሰብ አባላት ላይ ብቻ የሚዋቀርበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ችግሮች የታዩባቸው መዋቅሮች እየተፈተሹ ማስተካከያዎች ተደርገዋል፡፡ የሚሰሙ የህዝብ ቅሬታዎችን መፍታት ተችሏል፡፡ በዚህም በወረዳው በአንጻራዊነት የተሻለ ብዝሃነትን ያከበረ መዋቅር መፍጠር ተችሏል፡፡
ንጋት፡- የልዩ ወረዳውን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ከህዝቡ ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ አበራ፡- ህዝቡ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረው እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ዛሬ እውን ሆኗል፡፡ ጥያቄዬን መንግስት መልሶልኛል ብሎ በትብብር፣ በአንድነት ተሳትፎ አድርጎ የወረዳውን እድገት ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡ ከሌሎች አቻ መዋቅሮች ጋር እኩል ማድረግ ነው፡፡ እየገጠሙ ያሉትን ጊዜያዊ ፈተናዎችን በመተባበር ማገዝ ከህዝቡ ይጠበቃል፡፡ ለእድገት እንቅፋት የሚሆኑ ወገኖችንም በማረም በእውነታ ላይ በመቆም መተባበር ያሻል፡፡ በራስ ጥረት ሀብት አመንጭቶ በአካባቢው እድገት ላይ አሻራን ማሳረፍም እንዲሁ፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ የንግዱ ህበረተሰብም ሆነ አርሶ አደሩ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎችም ውጤታማ ተግባር በማከናወን የልዩ ወረዳውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል፡፡ ለጠምባሮ ህዝብ ያለው አማራጭ ተባብሮ መስራት ነው።
ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡
አቶ አበራ፡- እኔም እዚህ ተገኝታችሁ ለዚህ ዕድል ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”