ፍርድ ቤቱ ለግጭቱ መፍትሄ ይሰጥ ይሆን?

ፍርድ ቤቱ ለግጭቱ መፍትሄ ይሰጥ ይሆን?

በፈረኦን ደበበ

በዓለም ላይ ረጅም ጊዜ የወሰደ ነው፤ የእሥራኤልና ፍልስጤም ግጭት፡፡ መንስኤው የማንነት እንደመሆኑ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ገጽታዎች አሉት፡፡

አሁን ደግሞ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መወሰዱ የሚያረጋጋ ወይ የሚያባብስ ለመሆኑ ብዙዎች የሚከታተሉት ነው፡፡ አዎን፤ ረጅም ጊዜ የወሰደውን ያህል መፍትሄ ያለማግኘቱ ካላሳሰበ ፖለቲካዊ ግጭትን በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት የሚደረገው ጥረት እንዴት ላያስደንቅ ይችላል?

ለዓመታት የሰው ህይወት ሲያጠፉና ንብረትን ሲያወድሙ የነበሩ ፍጥጫዎች ደግሞ ባለፈው ጥቅምት ወር ወደ ለየለት ቀውስ ተሸጋግረዋል፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የብዙዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ዜጐችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፡፡ የውጭ ኃይሎችንም ትኩረት ስቧል፡፡

በብዙ ሃገራት አሸማጋይነት አማካይነት ሠላም ለማምጣት የተደረገው ጥረት ስኬታማ ባልሆነበት አሁን ምን አማራጭ ዘዴ ይኖራል? ተፋላሚዎችም እርስ በርስ መስማማት ባልቻሉበት የትኛው የውጭ ኃይል ችግሩን መርምሮ መፍትሄ መስጠት ይችላል?

አሁን እንደ አማራጭ መፍትሄ የተወሰደው ዓለም አቀፋዊ ፍርድ ቤት ሲሆን እሱም አስተማማኝ መፍትሄ ለመስጠቱ ያሳስባል፤ ምክንያቱም የአስገዳጅነት አቅሙ እምብዛም እንደመሆኑ፡፡ በየዕለቱ በሚያልቀው የሰው ህይወት መነሻ በዓለም ዙሪያ በእሥራኤል ላይ ተቃውሞ ማይሉም እንዲሁ፡፡

በዚህም ተባለ በዚያ ፍልሚያው ቀጥሏል፡፡ ፍልስጤም በወታደርና በፖለቲካ የእሥራኤልን ጡንቻ መስበር ባለመቻሏ ችግሩን ወደ ፍ/ቤት ይዘው መጥተዋል፤ ብለዋል የረጅም ጊዜ ወዳጅና የጸረ- እሥራኤል አቀንቃኝ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ አማካይነት፡፡

አልጀዚራ ጉዳዩን አስመልክቶ በተከታታይ ባወጣቸው ዘገባዎች እንደገለጸው ክስ ያቀረበችው ደቡብ አፍሪካ የእሥራኤልን እጅ በሌላው መንገድ የመጠምዘዝ ውጥን አላት። ነገር ግን ኃያላን እርስ በርሳቸው ፍትጊያ በሚያደርጉበትና ፍጥጫዎች በዓለም ዙሪያ ናኝተው ባሉበት ህጋዊ መንገዱ ይጠቅማል አይጠቅም የሚለው አሁንም አሳሳቢ ነው፡፡

ሀገሪቱ ዝርዝርና የተደራጀ ክስ አዘጋጅታ ወደ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ያቀረበችና መጥሪያም አውጥታ ወንጀለኛ ነች የተባለችውን እሥራኤልን ወደ ፍ/ቤት መጎተት ችላለች፡፡

ገና እየተሰማ ያለው ክስ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ይዘረዝራል፤ በከሳሿ ሀገር በኩል በተሠማሩ የህግ ባለሙያዎችና አመራሮች አማካይነት። የጠቀሱት የህግ አንቀጽም እ.ኤ.አ. በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፀደቀውና የሰብአዊ መብት ጥሰት አካል በሆነው በዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ ያተኩራል፡፡

ሰሞኑን ቀናትን በፈጀው የክስ መስሚያ ችሎት ላይ ደቡብ አፍሪካ እሥራኤል በፍልስጤም ላይ ፈጽማለች ያለቻቸውን ወንጀሎች አንድ በአንድና በባለሙያዎች በተደገፈ አግባብ ያቀረበች ሲሆን በፍልስጤማዊያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ብላለች፡፡

እናቶችና ጨቅላ ህጻናትን ጨምሮ እንደገደለችና ከመኖሪያ ሠፈራቸው አፈናቅላ ለሞትና አካል ጉዳት ጭምር እንደዳረገች ነው ያመለከተችው፡፡ በእርግጥ ፋታ በማይሰጥ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት የዓለም ማህበረሰብ ስሜትንም የነካ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካ ፍትህ ሚኒስትርን ጨምሮ በርካታ የህግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ቡድን ያቀረበው ክስ እየተሰማ ይገኛል። ሊያመጣ የሚችለው ፋይዳም እንዲሁ ብዙ ተብሎለታል፤ በአጭር ጊዜ እሥራኤል ጥቃቷን አቋርጣ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንድትመለስና እንዲሁም ከረጅም ጊዜ አንጻር የፍልስጤሞችን ነጻ ግዛት ታክብር የሚለውን ጨምሮ፡፡

እሥራኤል ወንጀል እንዳልፈጸመችና ራሷን ከመከላከል ውጭ ምንም ጥፋት አልፈጸምኩም ብላ የምትሟገትበት ክስ ለየትኞቹም የደቡብ አፍሪካ ጥያቄዎች ምላሽ ለማስገኘቱ እርግጠኛ መሆን  ባልተቻለበት በአሁኑ ጊዜ የዓለም አቀፍ ፍ/ቤት አካል በሆነው በዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ችሎት ላይም ሌላ ክስ ቀርቧል በተለይ ጥፋተኛ ግለሰቦችን ለማስጠየቅ ተብሎ፡፡

የፓርቲ ወይም የግለሰቦች ሳይሆን የመንግሥታትን የእርስ በርስ ግንኙነት የሚዳኘው ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ግን ጉዳዩን መመልከት ለመቻሉም ጥርጣሬዎች ይሰማሉ ምክንያቱም ሀማስ መንግሥት ሳይሆን የፍልስጤማዊያንን ጉዳይ የሚያስተባብር ፓርቲ ነው ከሚል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ግን ጉዳዬ ነው ብላ ወደ ፍ/ቤቱ የሄደችው ይህንን ክፍተት ለመድፈን ነው፡፡ ይህ ውዝግብ በሀገር ውስጥ ብዙ ተቃውሞዎች እየቀረቡበት ያለውን የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ መንግሥትን ማነቃነቅ መቻሉም በአሁኑ ጊዜ ለመተንበይ ያስቸግራል፡፡

በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ያጋሩት የደብሊን ከተማ ትሪኒቲ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ሚካኤል ቤከር እንደሚያስረዱት ከሆነ ፍ/ቤቱ ቀደም ሲል በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ካሁኑ ይለያል፤ ምክንያቱም ሁለቱ ሀገራት ሉዓላዊ መንግሥታት በመሆናቸው በሩሲያ ላይ ውሳኔ አስተላልፏል።

ውሳኔውን ለማስፈጸም አቅም የሌለውና በሌላ በኩል የመጨረሻ የሆነ ብይን መስጠት ይችላል የተባለለት ፍ/ቤት በምን ያህል ፍጥነት ውሳኔውን ያስተላልፋል የተባለውም እንደዚሁ አጠያያቂ ነው ምክንያቱም ፕሮፌሰሩ እንደሚያስረዱት እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ የማይናማር መንግሥት ሮህንጊያ በተባሉ ስደተኞች ላይ የፈጸመውን ድርጊት ጋምቢያ ብታቀርብም እስካሁን ውሳኔ ሳያገኝ በመቆየቱ።

በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እና በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ጣምራ ተመርጠው ለዘጠኝ ዓመታት ያገለግላሉ የተባሉት 15 የፍ/ቤቱ ዳኞችም ከብዙ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ናቸው ለሀገራቸውና ለየትኛውም አካል ሳይወግኑ ይሠራሉ ተብሏል ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ የሚፈጸሙ ተግባራት ቅሬታዎችን ቢያስነሱም፡፡

ደቡብ አፍሪካና እሥራኤል ሉዓላዊ ሀገራት እንደመሆናቸው እያንዳንዳቸው በችሎቱ አንድ አንድ ወኪል ዳኛ መሰየም ይችላሉ በተባለው መሠረት አሀሮን ባራክ የተባሉ የቀድሞ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛን እሥራኤል ልካለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ ዲካንግ ሞሰንክ የተባሉትን ተወካይ ወደ ፍ/ቤቱ ልካለች ሀገራቱ እራሳቸው ለፍ/ቤቱ ውሳኔ ተገዢ ይሁኑ አይሁኑ የሚለው ሁሉ ገና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ፡፡

ሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የህግ አማካሪዎችን ጨምሮ ልዩ የተባሉ ተወካዮችን መላክ በሚችሉበት በዚህ ችሎት ላይ ክርክሮች ተነስተዋል፡፡ እንደ መደበኛ ፍ/ቤት በቃልና ፊት ለፊት ሳይሆን ምላሹ በነጋታው በጽሑፍ በሚሰጥበት በዚህ መድረክ ላይ ምስክር ማቅረብም እንደማይፈለግ ነው የተገለጸው፡፡

ፍ/ቤቱ እሥራኤልን ጥፋተኛ ብሎ ሊወስን እንደሚችል ግምቶች ባሉበት በዚህ ክርክር ወቅት ደቡብ አፍሪካ  ውሳኔውን እንዴት ማስፈጸም ትችላለች የሚለውም ጥያቄ ጭሯል፤ ምክንያቱም በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታው ጥበቃ ም/ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላት አሜሪካ በተቃርኖ መሥመር ላይ ሆና እሥራኤልን ትደግፋለች የሚሉ ሥጋቶችም ስላሉ፡፡

ከውሳኔው ባለፈ የፍርድ  ሂደቱ ለፍልስጤሞች የሚያስገኙላቸው ሌሎች ጥቅሞችንም ሁሉ ማይ- አል- ሳዳኒ የተባሉ በዋሽንግተን ታህሪ ኢንስትቲዩት የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ ተንታኝ ሲገልጹም የተጎጂዎችን ስም፣ መረጃዎቻቸውን ለማግኘትና እንዲሁም ጥቃት አድራጊዎችን በመለየት ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚረዳም ነው ለአልጀዚራ የተናገሩት፡፡

ከውሳኔው በኋላ ሌሎች ሀገራት እሥራኤልን ወይም ደቡብ አፍሪካን በመደገፍ ጣልቃ ይገቡ ይሆን ተብሎ የሚነሳውን ጥያቄ በተመለከተም በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ጊዜ 32ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ዩክሬንን እንደደገፉና ሩሲያን የደገፈችው ሀገር ደግሞ ሀንጋሪ ብቻ እንደሆነች ተገልጿል፡፡ አልጀዚራ የዚህ ድጋፍ አንድምታ ምን መሆን እንደሚችልም የትሪኒቲ ኮሌጅ ፕሮፌሰር በከርን አነጋግሯል፡፡

በዚህም ሆነ በዚያ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ መጠን የፍ/ቤቱ ውሳኔም ወደዚያ እንደሚያዘነብል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፤ ይህ በዋናነት ለደቡብ አፍሪካና ለፍልስጤሞች እንደሚጠቅም በማስረዳት፡፡

በአንጻሩ እሥራኤል በበኩሏ ክሱ የፈጠራና በውሸት ላይ እንደተመሠረተ ስትገልጽ የቆየችውን ስታጠናከር እራስን ከአሸባሪዎች ጥቃት መከላከል አድርጋም ነው የምትመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ እራሳቸው እንደተናገሩት፡፡

ሆኖም እሥራኤል ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም የፖለቲካ አሠላለፍና ጠንካራውን የደቡብ አፍሪካ ክስ ተቋቁማ ርትዕ ማግኘቷ አጠራጣሪ ነው፤ ከፍልስጤሞች ጉያ ብዙ ሀገራትም ስለተሰለፉ፡፡ ፖለቲካዊና ህጋዊ ትርጉም ያለው ክስ በእንዲህ ያለ ሁኔታ የመካከለኛውን ምሥራቅ ቀውስ መቀየር ስለመቻሉም በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡