በአንዱዓለም ሰለሞን
ተጓዥ ነኝ፤ መነሻዬ ሳውላ መዳረሻዬ የባስኬቶ ዞን ርዕሰ ከተማ ላስካ ናት፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ሳውላ መነኻሪያ ተገኝቻለሁ። ከብዙ ጊዜ ልምዴ እንደማውቀው ማልጄ መነሀሪያ በመገኘቴ መኪና በቶሎ እንደማገኝ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ የሆነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር፡፡
ትኬት ለመቁረጥ ወደ ትኬት መቁረጫው ቦታ አመራሁና የምሄድበትን ከተማ በመንገር ዋጋውን ጠየኳት፤ ትኬት ቆራጯን፡፡ ወደ እዚያ ለሚሄድ መኪና ትኬት ከጽህፈት ቤቱ እንደማይቆርጥ ነገረችኝ፡፡ ምላሿ ጥያቄ ቢፈጥርብኝም ምክንያቱን አልጠየኳትም። የሞላ መኪና እንዳያመልጠኝ በማለት በአንድ የመኪና ረዳት ጥቆማ ወደ መኪናው አመራሁ። የመኪናውን በር በመክፈት ላይ የነበረውን ረዳት፡-
“ላስካ ነው?” ስል ጠየኩት፡፡
“አዎ፤ ግባ” አለኝ፤ በሩን እየለቀቀልኝ፡፡ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ መኪናው ባዶ ነበር፡፡
“የመጀመሪያው መኪና ወጥቶ ነው?” ስል ጠየኩት ረዳቱን፤ የልብስ ቦርሳዬን ወንበሩ ላይ እያኖርኩ፡፡
“አልወጣም ይሄ የመጀመሪያው ነው” አለኝ፡፡ ቀጠለና፡-
“ይቆያል ከፈለክ ቁርስ በልተህ መምጣት ትችላለህ” አለኝ
“ብዙ ይቆያል እንዴ ለመሙላት?” አልኩት የልብስ ቦርሳዬን ከወንበሩ ላይ እያነሳሁ፡፡
“እንደ ተሳፋሪው ሁኔታ ነው፤ አይታወቅም፡፡”
የረዳቱ አነጋገርና ሁኔታ ጉዞ በቶሎ እንደማንጀምር የሚጠቁም ነበር፡፡ እናም የልብስ ቦርሳዬን ይዤ ከመኪናው ወረድኩ፡፡ ቁርስ በልቻለሁ፣ በጠዋት ቡና የመጠጣት ልማድ ስላለኝ እሱንም አድርሻለሁ፡፡ ግን ደግሞ ባዶ መኪና ውስጥ ዝም ብሎ ከመጎለት ዞር ዞር ማለትን መርጬ ከመነሀሪያ ወጣሁ፤ ማን ያውቃል ምናልባትም ለሥራ የሚሆን ነገርም ይገጥመኝ ይሆናል በማለት ራሴን እያጽናናሁ፡፡
ከመነሀሪያ ውጪ ዞር ዞር እያልኩ ቆየሁና የመኪናውን ሁኔታ ለማየት ወደዚያው ተመለስኩ፡፡ መኪናው ውስጥ ሁለት ሰዎች ተቀምጠው ነበር፡፡ አንደኛዋ ሴት በእድሜ የገፉ ናቸው፡፡ የልብስ ቦርሳዬን አንደኛው ወንበር ላይ አኖርኩና ሴቲዮዋ እንዲያዩልኝ አደራ ብዬ ተመልሼ ወጣሁ፡፡
ከቆይታ በኋላ ስመለስ አሁንም ሌላ ሰው አልነበረም፡፡ እንዴት ነው ይሄ ነገር ስል ረዳቱን ጠየኩት፡፡
“ያው እንግዲህ ሲሞላ ነው የምንወጣው” አለኝ፡፡
“መቼ የሚሞላ ይመስልሀል?”
ከረዳቱ ምላሽ እንደተረዳሁት በትዕግስት ከመጠበቅ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረኝም።
ከመኪናው ልወርድ ስል አንድ ሰው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ተገጣጠምን፡፡
“ገና ባዶ ነው እንዴ?” አሉ ከአንዱ ወንበር ላይ አረፍ እያሉ፡፡
“ያው እንግዲህ ቀስ እያለ ይሞላል” አልኳቸው አፌ እንዳመጣ፡፡
“መሙላቱ መች ይቀራል፤ ሰዓታችንን እንገድላለን እንጂ” አሉ፡፡ በዚያው ጨዋታ ጀመርን፡፡ የማይከብዱና ጨዋታ አዋቂ ሰው ናቸው፤ በተለይም ደግሞ ታሪክ ነክ ነገር የሚመስጣቸው፡፡ ከሰውዬው ጋር ለመግባባት ብዙም አልከበደኝም፡፡ አንዱን እያነሳን፣ ሌላኛውን እየጣልን ስናወጋ ከቆየን በኋላ፡-
“ይሄ ነገር የሚቆይ ይመስለኛል፤ ወይ ወጣ ብለን ዞር ዞር እንበል” አሉ፡፡ በሀሳባቸው ተስማምቼ ከመኪናው ወረድንና ከመነሀሪያ ወጣን፡፡ አንድ ቦታ ላይ ሻይ ቡና እያልን ስናወጋ መኪና ውስጥ ሆነን አስቤው የነበረውን ሀሳብ አነሳሁላቸው፡፡ ሳያመነቱ ነበር በሀሳቤ የተስማሙት፡፡ እናም “ባለታሪክ” ለሚለው የጋዜጣችን አምድ ላሰብኩት ጽሁፍ ቃለ መጠይቅ አደርጋቸው ዘንድ ከአንድ ጸጥ ያለ ቦታ አረፍ ብለን እንጨዋወት ጀመር፤ እኔም ላስካ ከመድረሴ አስቀድሞ ሥራዬን ጀመርኩ፡፡
ከቃለ ምልልሱ በኋላ ሁኔታውን ለማየት ወደ መኪናው አመራን፡፡ ብዙም የተለየ ነገር አልነበረም፡፡
“እስከ ስምንት ሰዓትም ከወጣን ጥሩ ነው” አሉ መኪና ውስጥ ድንገት የተወዳጀኋቸው ወዳጄ፡፡
“ስምንት ሰዓት! እስከዚያ ያቆየናል!?”
“በዚህ ዓይነት እንደዛ ይመስለኛል::”
“እንደዛማ ከሆነ ምሳ እንብላ” አልኳቸው። ተያይዘን ወጣን፡፡ ከአንድ ምግብ ቤት ምሳችንን በላን፡፡
ከዚያም ሻይ ቡና እያልንና እየተጨዋወትን ቆየን፡፡
“ወደ ላስካ ለመሄድ ሌላ አማራጭ አልነበረንም” ስል ጠየኳቸው፤ በጨዋታችን መሀል፡፡
“ወደ እዚያ የሚሄዱ ሞተሮች አሉ፡፡ መነሀሪያ ከመምጣቴ አስቀድሞ አንድ ሞተረኛ ጠይቄ ነበር፡፡ 400 ብር አለኝ” አሉ፡፡
“በመኪና ስንት ነው የምንከፍለው?”
“መቶ ሀምሳ ብር፡፡”
“ላስካ ከዚህ ስንት ኪሎ ሜትር ነው?”
“ሀምሳ አምስት::”
ይህን ያህል ኪሎ ሜትር በንፋስ እየተመቱ ተጉዞ 400 ብር መክፈል አዋጪ ሆኖ አልታየኝም፡፡ አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭ መኪናው እስከሚሞላ በትዕግስት መጠበቅ ነው፡፡ በጥበቃው ሂደት እሳቸውን ባላገኝ ኖሮ ጥበቃው ምን ያህል አሰልቺ ሊሆን እንደሚችል አሰብኩት፡፡ በእርግጥም ነገሩ ትዕግስት አስጨራሽ ነበር፡፡ ስምንት ሰዓት ላይ መኪና ውስጥ ተቀምጠን መኪናው ሞልቶ፣ “ትርፍ ሰው” አሳፍሮ ጉዞ እስኪጀምር እንጠባበቅ ጀመር፡፡
ከቀኑ 8፡30 ላይ ጉዞ ጀመርን፡፡ መኪናው ውስጥ የነበረው ሁኔታ የከተማ አውቶቢስን የሚያስታውስ ነው፡: የቆሙ ሰዎች ነበሩ፤ ያውም ስምንት፡፡ ከዚህ ባሻገር ሁለት ሰዎች ደግሞ ዱካ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ሞተሩ ላይ ደግሞ አራት ሰዎች ነበሩ፡፡ አንደኛዋ እንደውም ጨቅላ ህጻን ይዛለች፡፡ የእሷን ሁኔታ ስመለከት በነገሩ መማረሬን ተውኩት፡፡
ከመነሀሪያ ወጥተን ብዙም ሳንርቅ ሾፌሩ መኪናውን አቆመና ሌላ ህጻን ልጅ የያዘች ሴት ተሳፈረች፡፡ እሷ እንኳ ቦታ ተይዞላት ነበር፡፡ እርሷን ተከትሎ የገባው ሌላ ተሳፋሪ ግን ከፊት ለፊታችን ቆመ፤ ከበሩ ፊት ለፊት፣ ረዳቱ የሚቆምበት ቦታ ላይ፡፡ መኪናውም እንደቆመ ነበር፡፡ አንድ ወፍራም ሴት ከሞተር ወርደው ወደ መኪናው ገቡና ሞተሩ ላይ ተቀመጡ፡፡ የማይሞላ ሞተር !
የወምባ ወንዝ ስንሻገር ረዳቱ፡-
“ከዚህ በኋላ ለማንም አልቆምም” በማለት ተናገረ፡፡ እና ድሮስ ለማን ሊቆም ኖሯል፤ ለትራፊኮች? እንደዛ ቢሆን ኖሮ እንዲህ በኮንቴይነር ውስጥ እንዳለ ዕቃ ያጉረን ነበር? … ሌላ ሰው ለመጫን ከሆነ መቸስ ከላይ፣ ከዕቃ መጫኛው ላይ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ቦታ የለ፤ እና ታዲያ ለምን ይቆማል!? …
ለሰው መተላለፊያ ስላልነበር ረዳቱ ሂሳብ የሚቀበለውና መልስ ይሰጥ የነበረው “በሰሚ ሰሚ”፣ ከተሳፋሪዎች ጋር እየተቀባበለ ነበር፡፡
“የመኪናው ትክክለኛ የመጫን አቅም ምን ያህል ነው?” ስል ጠየኩት ረዳቱን፤ በሁኔታው እየተገረምኩ፡፡
“ሰላሳ ሶስት ሰው” ሲል መለሰልኝ፡፡
“አሁን አንተ የጫንከውስ?”
“እስከ 43 ድረስ እንጭናለን” አለኝ እንደዋዛ፡፡
አርባ ሶስት ሰው ማለት 10 ሰው ትርፍ ማለት ነው እንግዲህ፡፡ በእርግጥም መኪናዋ ውስጥ የነበረው ሰው ብዛት ከዚህ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡
ሾፌሩ ግን መስሚያ አልነበረውም፡፡ የከፈተውን መዝሙር ድምጹን ከፍ አድርጎ ጉዞውን ተያያዘው፡፡
በእርግጥ በጉዟችን መሀል ትራፊኮች አግኝተውን ነበር፤ ከአንዴም ሁለት ጊዜ። የሾፌሩ ረዳት ግን ጉዳዩን “በተለመደው መልኩ” ተወጣውና ጉዟችንን ቀጠልን። የትራፊኮቹና የረዳቱ ነገር ራሱን የቻለ አንድ አጭር ትወና ነበር፤ ግን ደግሞ የታወቀና የተለመደ ዓይነት፡፡
ምንም እንኳ የምንጓዘው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ጉዞው ግን አሰልቺ አልሆነብኝም፡፡ ላስካን ከዚህ ቀደም አላውቃትም፡፡ ለዚህ በተራሮች የወገብ መቀነት ላይ ለማደርገው ጉዞም እንግዳ ነኝ፡፡ እናም በማየው የተፈጥሮ መስህብ እየተመሰጥኩ፣ በጠመዝማዛው መንገድ ሁኔታ እየተገረምኩ፣ ሙቀቱንና ምቾት የሚነሳውን የመኪና ውስጥ ትዕይንት ቸል አልኩት፡፡
ምንጮች የሚንፎለፎሉበት በዛፎች የተሞላ ጋራና ሸንተረር፣ የሰጡትን የሚያበቅል፣ ግን ደግሞ ሰፊ ያልሆነ ለም የእርሻ መሬት፣ እርጥበት የሚታይበት በውሀ የወረዛ ድንጋይ፣ እንደ ዘንዶ የሚጥመለመል፣ በተራሮቹ ወገብ ላይ የተሰመረ የሚመስል ቀጭን መንገድ፡፡ ይህንን እና ይህንን መሰሉን ነገር ማየት ዐይንን ከመሰልቸት የሚያርቅ፣ ውስጥን ዘና የሚያደርግ ነገር ነው፡፡ ከከፍታ ላይ ሆኖ ቁልቁል ወደ ገደሉ መመልከት ልክ ወደ ማረፊያው ደርሶ ቁልቁል ከሚያዘቀዝቅ አውሮፕላን ላይ ሆኖ ወደ ታች እንደማየት ያለ ስሜትን የሚፈጥር ነው፡፡
በዚያ ላይ መኪና ላይ የተዋወኳቸው ወዳጄ ስለ መንገዱ እና በመንገዳችን ስለሚያጋጥሙን ነገሮች ማብራሪያ ይሰጡኛል። በዚህ የተነሳ ከአንድ አስጎብኚ ጋር ወደ አንድ ወደማላውቀው ቦታ ለጉብኝት እየሄድኩ እንዳለሁ ያለ ስሜት ነበር የሚሰማኝ፡፡
በመንገዴ የማየው ትዕይንት ማራኪ፣ አስገራሚ ብሎም አስፈሪም ጭምር ነበር። ከአንድ ከፍተኛ ቦታ (ተራራ) ላይ ሆኖ ታች ያለውን ገደል መመልከት የፍርሀት ስሜትን የሚፈጥር ነው፤ በተለይም እንደ እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚያ መንገድ ለሚጓዝ ሰው፡፡ ከዚህ ባሻገር መንገዱ ያን ያህል ምቹ አለመሆኑና ሥራው አለመጠናቀቁ ሌላው ጉዞውን ፈታኝ የሚያደርገው ነገር ነው፡፡
ሁለት ጊዜ ያህል ተሳፋሪው በሙሉ ከመኪናው ወርዶ (ክብደት ለመቀነስ) ሾፌሩ መኪናውን እያሽከረከረ አስቸጋሪውን መንገድ አልፎ እንደገና ወደ መኪናው በመግባት ጉዞ ጀምረናል፡፡ በዚህ ወቅት የገጠመኝ ነገርም የሰውን መልካምነት የታዘብኩበት ነበር፡፡
ከመኪናው ወርደን በእግር በመጓዝ ላይ ሳለን ከፊት ለፊቴ የነበረን ተራራ ፎቶ ግራፍ ለማንሳት ተጣድፌ ካሜራዬን ከኪሴ ባወጣሁበት አጋጣሚ ኪሴ ውስጥ የነበረው ብር መውደቁን አላስተዋልኩም ነበር፡፡ ከኋላዬ የነበረ አንድ ሰው ግን “ወንድሜ ብር ጥለሀል” በማለት አንስቶ ሰጠኝ፡፡ በዚህ ዘመን 1800 ብር ከመሬት አንስቶ ለባለቤቱ የሚመልስ ሰው ማየት አስገራሚ ቢመስልም ይህ ግን ላስካ ላይ እኔን ያጋጠመኝና የተደሰትኩበት ነገር ነው፡፡
በመጨረሻም ላስካን አየኋት። ከምሽቱ 11፡30 ላይ ከከተማዋ ደረስን፡፡ ወይና ደጋ የዓየር ጸባይ ያላት፣ በቅርቡ የዞን ከተማ የሆነች፣ ጸጥታ የረበበባት ከተማ ነች፤ ሰላማዊ። ዙሪያዋን ምንጮች የሚፈልቁባትና በተራሮች የተከበበች ሆና ሳለ በከተማዋ የውሀ ችግር መኖሩ ግን አስገርሞኛል። ከውሀው ባሻገር በመንገዴ የታዘብኩት ወደ ሳውላ የሚወስደው አውራ ጎዳናዋም እንዲሁ ትኩረትን የሚሻ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን የላስካና የአካባቢዋ ምድር ለምና በርካታ አዝዕርቶችን፣ ቅመማ ቅመሞችንና ፍራፍሬዎችን የሚያበቅል ነው። ይህንንም በከተማዋ ዋንኛ ገበያ በሚቆምበት ቀን፣ በዕለተ ሀሙስ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡
ላስካ ላይ ሰብሰብ ብለው የጀበና ቡና ከሚጠጡ ወጣቶች አንድ ሁለቱ ቡናቸውን ፉት እያሉ በመሀል ማንጎ ሲገምጡ ቢመለከቱ እንዳይገረሙ፤ ምክንያቱም ይህ ላስካ ነውና፡፡ የፍራፍሬ ምድር፡፡ እኔም በቆይታዬ ከበረከቷ ተቋድሼ ሀሴት አድርጌያለሁ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው