“ሴቶች ድብቅ ሀብትና ዕውቀት አለን” – ወ/ሮ እመቤት አረጋ
በደረሰ አስፋው
“ሽንፈት አልሻም፡፡ ታግሎ ማሸነፍን የኑሮዬ አንዱ ጣዕም አድርጌ እቆጥረዋለሁ። ትግል የሌለበት ስኬት ምን ጣዕም አለው? በትግል ውስጥ ማሸነፍን ባህል አድርጌ ነው ያደኩት፡፡ ሴቶች ድብቅ ሀብትና ዕውቀት አለን፡፡ ይህን አውጥተን ከተጠቀምን ውጤታማ ከመሆን የሚገድበን ነገር የለም፡፡
“በስራህ ተስፋ ስትቆርጥ በህይወትህ ውስጥ የሽንፈት አስተሳሰብን ትጋብዛለህ። ይልቁንም ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ መንገዶችን ፈልግ እና ችግሩን እስክታሸንፍ ድረስ ስልቶችህን ቀያይር፡፡ የሚመጣውን ማንኛውንም ችግር መቋቋም እችላለሁ ብለህ ካሰብክ የማትፈታው ችግር አይኖርም፡፡”
ንግግራቸው የመንፈስ ጥንካሬያቸውን የሚያጎላ ነበር፡፡ “ሴቶች ድብቅ ሀብትና ዕውቀት አለን” ሲሉም እንዲሁ አለዋዛ መሆኑን የሚያመላክተው ብዙ ነው፡፡ አሁን የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ፈታኝ የሚባሉ መንገዶችን ተጉዘዋል፡፡ ተደጋጋሚ የሆነ ሀዘን ሊጥላቸው ቢያስብም አልተሸነፉለትም፡፡ ፈተናውን አለፉት እንጂ፡፡
በአነስተኛ የሻይ ቡና የጀመረው ስራቸው አድጎና ተመንድጎ ወደ ሆቴል ደረጃ እያኮበኮበ ነው፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ደግሞ ስራውን ሲጀምሩ መነሻ ካፒታላቸው 90 ብር ብቻ መሆኑ ነው፡፡ እሱንም ቢሆን የራሳቸው ሳይሆን ከእናታቸው የተደበሩት ነበር፡፡
ወ/ሮ እመቤት አረጋ ይባላሉ፡፡ ትውልድና ዕድገታቸው ጅማ ነው፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በጅማ ተምረዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ግን ወደ ሙዱላ ከተማ በመምጣት ኑሯቸውን ከእናታቸው ጋር አደረጉ፡፡ እህል ውሃቸውም እዚሁ ሆነ፡፡ በከተማው ትዳር መስርተው 2 ልጆች ወልደው ከብደውበታል፡፡
ወደ ሙዱላ እንደመጡ የመንግስት ስራ ተቀጣሪ ለመሆን ተደጋጋሚ ማስታወቂያዎችን ተከታትለዋል፡፡ ውጤቱ ግን ተጠባባቂ የሚል ብቻ እየሆነ የተመኙትን የመንግስት ስራ ማግኘት አልቻሉም፡፡
በዚህም ወደ ሌላ ስራ አይናቸውን አዞሩ። “በመንግስት ስራ ብቻ ነው እንዴ ህይወቴን የምመራው?” በማለት ራሳቸውን በመጠየቅ የግላቸውን ስራ ለመፍጠር ተነሳሱ። በሙዱላ እና አካባቢው በ1990ዎቹ የሻይ ቡና ስራ እንዳሁኑ አልተስፋፋም ነበር። ይህ ጥሩ ስራ እንደሆነም በዳሰሳ ጥናታቸው አረጋገጡ። ለዚህም ከወላጅ እናታቸው ጋር መከሩ፡፡ ከሻይ ቡናው ጎን ለጎን ምግብም መጀመር እንደሚቻል አማከሯቸው፡፡ ይሁን እንጂ በእናታቸው በኩል ጥርጣሬ መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በአካባቢው ይህ ዓይነቱ የስራ ልምድ ስለሌለ ትከስሪያለሽ በማለት፡፡ ምኑን ከምኑ አድረገሽ ነው በ90 ብር ወደ ስራ የምትገቢው በማለት፡፡
እሳቸው ግን “እለወጣለሁ ብዬ ከተነሳሁ የሚገድበኝ የለም” በማለት ሞገቷቸው፡፡ 90 ብር ለጀማሪ ስራ ፈጣሪ ከበቂ በላይ ነው በሚል፡፡ በወቅቱ ለስራው የሚያስፈልጉ ግብአቶች እህልን ጨምሮ ዋጋ ቅናሽ ስለነበር ለስራቸው እንቅፋት አላጋጠማቸውም። “ዘመኑ ወርቅ ነበር፡፡ ተሰርቶም ወርቅ የሚገኝበት ጊዜ ነበር” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
ወ/ሮ እመቤት ግን ስራ ፈላጊ ሳልሆን ስራ ፈጣሪ መሆን አለብኝ በማለት ሀሳብን በሃሳብ ሞገቱ፡፡ የእሳቸው ሀሳብ አሸንፎም ወደ ስራው ገቡ፡፡ በ60 ብር ቤት ተከራዩ፡፡ ሻይ ቡናውንም ምግቡንም ጀመሩ፡፡ ለስላሳ መጠጦችንም አቀረቡ፡፡ ስራቸው ኪሳራ ሳይሆን ትርፋማ አደረጋቸው፡፡ በሞቀው ጅምር ስራቸው ላይ ግን ውሃ የሚቸልስ ችግር አጋጠማቸው፡፡ የወላጅ እናታቸው ሞት፡፡ ሀዘኑ በረታባቸው፡፡ የጀመሩትን ስራ አቋርጠው ወደ ጅማ ለመሄድ አሰቡ። ይሁን እንጂ ያሰቡት ሳይሆን ቀረ፡፡ “እህል ውሃቸው ጅማ አልነበረምና ትዳር መሰረቱ፤ ኑሯቸው እዚያው ሙዱላ ከተማ ሆነ፡፡ ሀዘኑ ሊሰብራቸው ቢሞክርም የኋላውን ሳይሆን የፊቱን መመልከት እንደሚገባ ለራሳቸው በመንገር በረቱ፡፡ ወደ ስራቸውም ተመለሱ፡፡ የህዝቡም ሁኔታ አጽናናቸው፤ አበረታቸው፡፡
“ስራዬም ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ አለብኝ፡፡ ሁሌም የወንድን እጅ መጠበቅ ተገቢ አይደለም አልኩ፡፡ ለዚህም የራሴ ጥረት ቀዳሚው የህይወቴ መርህ ሊሆን ይገባል በማለት ስራውን አጠናክሬ ጀመርኩ።”
ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ እቁብ መሰረታዊ ነገር እንደሆነ አሰቡ፡፡ በስራ ቦታቸው አካባቢ የነበሩ በጫማ ማሳመር ስራ ላይ የተሰማሩትን እና ሱቅ በደረቴ የሚሰሩ ልጆችን አሰባሰቡና ዓላማችን ሰርቶ ለመለወጥ እስከሆነ ድረስ እቁብ እንሰብስብ በማለት አማከሯቸው፡፡ እነርሱም በሀሳቡ ተስማሙ፡፡ ከዚያም በቀን 3 ብር ዕቁብ መጣል ጀመሩ፡፡ ስለሁኔታው ሲያስታውሱም፡-
“ልጆቹ ከሊስትሮ ህይወት እንዲወጡ ምክሬን እለግሳቸው ነበር፡፡ እኔም ከሻይ ቡና ስራ ወጥቼ የተሻለ ህይወት መምራት አለብኝ አልኩ፡፡ በወቅቱ ባንክ ባለመኖሩ ከጣውላ በተሰራ ሳጥን ውስጥ ነበር የምንቆጥበው። 10 ልጆች በቀን 30 ብር እንቆጥባለን፡፡ ሳጥኑ የሚከፈተው በዓል ሲመጣ ብቻ ነበር። ልጆች በገንዘቡ በግ እና ፍየል እየገዙ ሀብት ያፈሩበት ነበር፡፡ እኔም ቤት ገዛሁ፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች በመግዛትም ስራውን አደራጅ ነበር። በሂደትም ጎበዝ ነጋዴ ሆንኩ” ይላሉ፡፡
የስራ ፈጣሪዋ ወ/ሮ እመቤትና የሊስትሮ ሠራተኞቹ ህይወት እየተቀየረ መጣ፡፡ በ3 ብር የተጀመረው ዕቁብም በሳምንት 3 መቶ ብር ወደ መጣል አደገ፡፡ በዕቁቡ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ሺህ ብር ደረሳቸው፡፡ በአስር ሺህ ብር የሚከራዩ ክፍሎችን ገነቡ፡፡ ተጨማሪ የገቢ ምንጭንም ፈጠሩ፡፡ የመጀመሪያው እቁብ ሲያልቅ ብሩን ከ3 መቶ ወደ 6 መቶ ብር ከፍ አደረጉት፡፡ ይህ እቁብ ሲደርሳቸው ደግሞ ተጨማሪ ቤት ገዙ፡፡ ስለልጆቹ ሁኔታ ሲናገሩም፡-
“ዛሬ ላይ እነዚህ ልጆች ጥሩ ህይወት እየመሩ ነው፡፡ ሳያቸውም በህይወቴ አንድ ቁም ነገር እንደሰራሁ እቆጥረዋለሁ፡፡ አንዳንዶች ከሀገር ውጪ ሄደው ሰርተው ባለሃብት የሆኑም አሉ፡፡ እናታችን ነሽ ይሉኛል ዛሬ ሲያዩኝ፡፡ እኔም ህይወቴ ከቀድሞው እጅግ ተለውጧል፡፡ በዚህም ሁላችንም ደስታ ይሰማናል” ብለዋል
ወ/ሮ እመቤትም የሻይ ቡና ስራቸውን ከፍ ወዳለ ደረጃ አሳደጉት፡፡ ቤት ተከራይተው ወደ ግሮሰሪ እና ምግብ ቤት ቀየሩት፡፡ ምግብ ቤታቸው ከሽሮ ባሻገር ስጋ ነክ ምግቦችን እንዲያካትት አደረጉት፡፡ በግና ፍየል በማረድ ተጨማሪ ደንበኞችን አፈሩ፡፡ ከሩቅ የመጣ እንግዳ ማረፊያም ሆኑ፡፡ በተለይ በጣፋጭ እጃቸው ተወዳጅ ሆኑ፡፡ እራስን ወደመቻል ደረጃ ላይ ተሸጋገሩ፡፡
“ሴቶች ድብቅ ሀብትና ዕውቀት አለን ስል እንዲሁ በቀልድ አይደለም፡፡ ሴት ልጅ ዘዴኛ ነች፡፡ አቅዳ ከተነሳች እቅዷን እውን የማድረግ ተሰጥኦም ሆነ አቅም አላት። ችግርን በብልሃት ታሸንፋለች፡፡ ለዚህም አንዷ እማኝ እኔ ነኝ፡፡ ከምን ተነሳሁ አሁን የት አለሁ ሲባል ድሮና ዘንድሮ ለየቅል ናቸው፡፡ በርካታ ሴቶች ይህን እምቅ እውቀት ባለመጠቀም ለችግር እንጋለጣለን፡፡ እኔ የሰውን እጅ ማየት አልፈልግም፡፡ ልጆቼም እኔ ያለፍኩበትን ህይወት እንዲያዩ አልፈልግም፡፡ በጥሩ ትምህርት ቤት ተምረው ህይወታቸው እንዲለወጥ እንጂ፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠንክሮ መስራት ነው መፍትሄው፡፡ ጊዜዬን መጠቀም የምፈልገው ደረጃ ለመድረስ እተጋለሁ፡፡”
በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ በድጋሚ ሌላ ሀዘን ውስጥ ገቡ፡፡ ባለቤታቸውንም በሞት ተነጠቁ፡፡ ተደራራቢ ሀዘን ቢጫጫናቸውም ጠንካራ ማንነትን መላበስ ግድ የሚልበት ጊዜ እንደሆነም ተገነዘቡ፡፡ ስንፍናን ያለፈ ነገርን ማየት ተገቢ አለመሆኑን ተረዱ፡፡
“ክብር የማገኘው ለራሴ በሚኖረኝ ጥረት እንደሆነ ተገነዘብኩ፡፡ መንገዱ ረጅም ቢሆንም ስኬታማ መሆን እንደምችል ውስጤን አሳመንኩ፡፡ ልልበስ፣ ላጊጥ ማለት ሳይሆን የሚቀድመውን አስቀደምኩ፡፡ የቀድሞ ህይወቴ እንዲደገም አልሻም፡፡ 30 ሴቶችን በማስተባበር በሳምንት 400 ብር እቁብ አሰባሰብኩ፡፡ በዚህም ብር ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት ገነባሁ፡፡” ሲሉም የገጠማቸውን ፈተና የተወጡበትን መንገድ አብራርተዋል፡፡
ወ/ሮ እመቤት ሁሌም ለየት ያለ ስራን ፈጥረው ተጠቃሚ የመሆን ልምድን አዳብረዋል፡፡ በከተማው የዶሮ ወጥ ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ በምግብ ቤታቸው የጀመሩት የዶሮ ወጥ በርካታ ደንበኞችን አፈሩበት። በተለይ በመንገድ ግንባታ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በወቅቱ ደንበኞቻቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ድሮ፡- አንድ ዶሮ በአስር ብር ይገዙ እንደነበር እያስታወሱ። በ20 ብር ሽንኩርት አራት ዶሮ ይሰሩበት እንደነበርም እንዲሁ፡፡ አንድ የዶሮ ምግብ አንድ እንቁላል፣ አንድ የዶሮ ብልትና ወጥን ጨምሮ በ5 ብር ይሸጣሉ፡፡ ይህ ስራቸው ተጠቃሚ አደረጋቸው፡፡ ተመግበው ብቻ ሳይሆን ይዘውም የሚሄዱት በርካቶች ናቸው። ተደውሎ በትዕዛዝ ያዘጋጃሉ፡፡ በቤታቸውም በትእዛዝ የሚያዘጋጇቸው ተጨማሪ የምግብ አይነቶች በርካታ ናቸው፡፡ አይብ፣ የበግና የፍየል ስጋ ነክ ምግቦች፣ አይብ በጎመን እና ፈጣን ቁርሳ ቁርሶችንም ያዘጋጃሉ፡፡
“በስራ አለም ከሰዎች ጋር ነው የምትኖረው። በስራ ቅን ልቦና ይዘህ ከሰራህ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትንና ተወዳጅነትን ታገኛለህ፡፡ እንስሳ እንኳ በባህሪው ይወደዳል። በጎም ነገር ይደረግለታል፡፡ ከፍርፋሪው ሳይሆን ተቆርሶ ይሰጠዋል፡፡ መጥፎ ባህሪ ያለው ደግሞ ወደ ገበያ ተወስዶ ይሸጣል፡፡ ከቤትም ይባረራል፡፡ ሰዎችም በተመሳሳይ ጥሩ ባህሪ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በሰዎች መወደድ ሰርተህ ውጤታማ ለመሆን ይደግፋል፡፡” ይላሉ፡፡
በስራቸው ለ4 ሠራተኞች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ 2 የቤተሰብ ልጆችንም ያሳድጋሉ፣ ያስተምራሉ፡፡ የራሳቸውም 2 ልጆች አሏቸው። ታናናሽ ወንድሞቻቸውንም አስተምረው፣ ስራ ይዘው ኩለው ድረዋል፡፡ ይህ የሆነው በዚሁ በ90 ብር በተጀመረው የሻይና ቡና ስራቸው ፍሬ አፍርቶ ነው፡፡ በከተማውም መልካም ስም ገንብተዋል፡፡
“የኔ ህይወት በዚህ አያበቃም፡፡ ይቀጥላል። ወደፊትም በሙዱላ ከተማ ላይ ለብዙ ሴቶች አርአያ ሆኜ ለመታየት እፈልጋለሁ፡፡ የሴቶችን ጥንካሬ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ በማህበራዊ ዘርፍ በመሰማራት በበጎ አድራጎት የመሰማራት ፍላጎቱም ሆነ እቅዱ አለኝ፡፡ በእድሜ መግፋት የተንገላቱ፣ ወላጅ አልባ ህጻናት፣ ደጋፊ ያጡና መጠለያ አጥተው የሚንገላቱትን በማሰባሰብ ለመርዳት ነው ሀሳቤ፡፡” ሲሉም የወደፊት ህልማቸውን ያጋራሉ፡፡
ወይዘሮ እመቤት በ35 እናቶች የተቋቋመ ማህበር መስርተዋል፡፡ ይህ ማህበር ትኩረቱ በልማት ላይ ነው፡፡ በከተማው ልማት ላይ የራሳቸውን አሻራ የማሳረፍ ዓላማ፡፡ ማህበሩ አቅሙን ካሳደገ ደግሞ በበጎ አድራጎት ተግባር በመሰማራት አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልበትን አቅም መፍጠር ላይ እንዲሰማራ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት፡፡
ያሰሩትን ቤት መሰረቱ ለፎቅ እንዲሆን አድርገው ነው ያስገነቡት፡፡ አቅማቸው እያደገ ሲመጣ ደግሞ ይህንኑ ቤት በማሳደግ ስራቸውን ወደ መዝናኛ ዘርፍ የመለወጥ እቅድ አላቸው፡፡ ህንጻውም ቢሆን በሙዱላ ከተማ የገጽታ ግንባታ ድርሻ እንዲኖረው ማድረጉንም ጎን ለጎን የሚታይ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ ያፈሩትን ካፒታል ሲገልጹም፡-
“በአጭሩ ተባርኬያለሁ፡፡ በራሴ ጥረትና ትጋት ያመጣሁት በመሆኑ እርካታን ፈጥሮልኛል” ያሉ ሲሆን ከሚኖሩበት ቤት በተጨማሪ ሌላ ቤትም ገዝተዋል፡፡ ግንባታ ሲያከናውኑም በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት እንዳፈሰሱበት በመግለጽ፡፡ ስኒና ብርጭቆ ብቻ ይዘው ወደ ስራው የገቡት ወ/ሮ እመቤት የንግድ ስራቸው በሙሉ ግብአት የተሞላ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሀብቱ ብዙ ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
“ሴት ልጅ ለስራ የተዘጋጀ ልብ ሊኖራት ይገባል፡፡ እኔ ሰርቼ መቀየር እችላለሁ ብሎ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ በሚሰራ ሰው ከመቅናት አስተሳሰብ በመውጣት መስራት ያሻል፡፡ ሰርተው የተለወጡት ከሰማይ ወርዶላቸው ሳይሆን ሰርተው ያመጡት ለውጥ ነው፡፡ አንዱ የጀመረውን መልሶ መስራት ሳይሆን አዳዲስ የስራ ዘርፎችን በመፍጠር መስራትም ይበልጥ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ አንዱ ላንዱ ተደጋጋፊ በሆኑ የስራ ዘርፎች በመሰማራት ተደጋግፎ ማደግ ይቻላል፡፡
“በኑሮ ችግር የበርካቶች ትዳር ሲናጋ ተመልክቻለሁ፡፡ ‹ሴት ልጅ ለባሏ ዘውድ ናት› እንደተባለው ነው መሆን የሚገባው፡፡ ለወንዱ አጋዥ መሆን አለባት እንጂ ሁሌም እጅ የምትዘረጋ መሆን የለባትም” ሲሉም ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው