“ጡረታ መውጣት ከሥራ ውጪ መሆን አይደለም” – መምህር በቀለ ሳፋ
በገነት ደጉ
መምህር በቀለ ሳፋ ይባላሉ፡፡ ትውልድ እና ዕድገታቸው በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በይርጋጨፌ ወረዳ ልዩ ስሙ ኢዲዶ ቀበሌ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ተከታትለዋል፡፡ ወላጅ አባታቸውን ያጡት በሁለት ዓመታቸው እንደነበር አጫወተውናል፡፡
በወቅቱ ትምህርታቸውን ለመማር የሚረዳቸው ሰው ባለመኖሩ ወላጅ እናታቸው የቀን ስራ በመስራት ነበር ያስተማሯቸው፡፡ “ሚስማር ሲመታ ይጠነክራል” እንደሚባለው ሁሉ ችግሮቹ አበረቱኝ እንጂ ለመድረስ ካቀድኩበት ቦታዎች ሁሉ አላስቀሩኝም በማለት ባለታሪካችን ይናገራሉ፡፡
በ1966 ዓ.ም አካባቢ ለደሃ ልጆች ወላጅ አልባ ተብሎ ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ እርሳቸውም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነው እየተረዱ ቢማሩም ትምህርታቸውን ግን ሊገፉ አለመቻላቸውን ነው ያጫወቱን፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ረዳት እንደሌላቸው ባወቁ ጊዜ እሳቸውንና እናታቸውን ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ወስደው ለማስተማር ሲጠይቋቸው ፈቃደኛ በመሆናቸው ወደ ሲዳማ አካባቢ ሄደው የ5ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተምረዋል፡፡
በኋላም የአባታቸው ቤተሰብ “ልጃችንን ሸጠች” በማለት እናታቸውን ሲያስጨንቁ ከሄዱበት ተመልሰው እዛው ኢዲዶ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መቀጠላቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በዓመቱም ከ5ኛ ወደ 6ኛ ክፍል ሲዛወሩ የ6ኛ ክፍል ትምህርት ኢዲዶ ባለመኖሩ ወደ ይርጋጨፌ ቢሄዱም ረዳት ስላልነበራቸው በእጅ ሹራብ ለሰዎች በመስራት ነበር ትምህርታቸውን መከታተል የቻሉት፡፡
ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ወጣቶችን ስለ ሀገር ፍቅር እንደሚያስተምሯቸው የተናገሩት ባለታሪካችን ከዚህም የተነሳ በርካታ ወጣቶች ብሄራዊ ወትድርና መዝመት ችለዋል፡፡
ይህም ለእሳቸው ትልቅ ስኬት ቢሆንም እንኳን እናቶች እርሱ እዚህ ተቀምጦ ልጆቻችንን ሸጦ ጨረሰ የሚል ወቀሳ ሲያቀርቡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በ1974 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ለቀበሌው ንብረት አስረክበው ከእንግዲህ ወዲህ ወጣቶችን አላሰለጥንም በማለት ጥለው ወደ ገደብ ወረዳ መመለሳቸውን ነው ያጫወቱን፡፡
በኋላም ብዙም ለኑሮአቸው ባለመመቻቸቱ ምክንያት ወደ ክብረመንግስት ዘመዶቻቸውን አፈላልገው መግባታቸውን የተናገሩት መምህር በቀለ፣ እግረ መንገዳቸው ትምህርታቸውንም ለመቀጠል ቢያስቡም ቦታ በማጣት ምክንያት የማታ ትምህርትን ለመጀመር ተገደዋል፡፡
“ዛሬን እዚህ መድረሴ ተቸግሬም ቢሆን ትምህርቴን በመማሬ ነው፡፡ መማር ሙሉ ሰው ያደርጋል፤ መቸገሬም ለዛሬ ህይወት መሰረት ሆኖኛል፡፡” ሲሉም መማራቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ፡፡
በችግር በተፈተነው ትምህርታቸው ከ11ኛ ወደ 12ኛ ክፍል ቢዛወሩም ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ ወትድርና ለመዝመት መገደዳቸውን ነው የጠቆሙት፡፡
ብሔራዊ ውትድርና ለአራት ተከታታይ ዓመታት በታጠቅ ሶስት እና ብር ሸለቆ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ በሰራዊት ቤት መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ከዚያም ወደ ገደብ ወረዳ በመመለስ በወቅቱ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው በመምህርነት ተቀጥረው ወደ መምህርነት ሙያ መግባታቸውን ነው የተናገሩት።
በወቅቱም 182 ብር ደመወዝ እየተከፈላቸው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ተማሪዎችን የመለየት ስራ እየሰሩ እንደነበር የሚናገሩት መምህሩ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳይኖር በራስ ጥረት ተማሪዎችን በእውቀት እያበቁ እንደነበር ነው የገለፁት፡፡
ውጤትም ለማምጣት ተማሪዎችን በአግባቡ ማብቃት እንጂ ሁሉም ተማሪዎች ይለፉ የሚለውን ብዙም አልቀበልም ነበር የሚሉት መምህር በቀለ በዚህም የመንግስት ፖሊሲ ትቃወማለህ በማለት ተቃዋሚ ይሉኝ ነበር፡፡
“በየዓመቱ የራሴን ፈጠራ እፈጥራለሁ፡፡ በተለይም በተማሪዎች ላይ ምን መስራት አለብኝ የምለው በጣም ያስጨንቀኛል፡፡ ምክንያቱም የሚቀረፀው ትውልድ ነው፡፡ 5ኛ ክፍል ሲሰጠኝ ደግሞ በራሴ ፈጠራ ከክፍል ውስጥ ሞዴል ተማሪዎችን ማውጣት ጀመርኩ፡፡ ይሄ ሰውዬው ጤናማ አይደለም እንዴ በማለት ይቃወሙኝ ነበር በማለት በወቅቱ የነበረውን የሰዎች ትዝብት ይናገራሉ፡፡
በጎ ስራ ለራስ ነው እንደሚባለው ሁሉ ጊዜው የእኔ ሆነና ሞዴል መምህር ተፈለገ፡፡ እኔ ግን በወቅቱ ድግሪም፣ ዲፕሎማም ይሁን ሰርትፍኬት አልነበረኝም፡፡ ሆኖም ግን ተመርጬ አርባምንጭ መምህራን ማሰልጠኛ በመግባት ስልጠና ስጀምር ተቃዋሚ ነው በማለት ከማስልጠኛ እንድወጣ ተደረኩ፡፡”ይላሉ፡፡
ይሁን እንጂ ድርጊቱን በመከራከር ወደ ማሰልጠኛ በመመለስ በ1994 ዓ.ም በሰርትፍኬት መመረቃቸውን ነው የገለፁት፡፡ ባለታሪካችን ዲፕሎማቸውን በግል ኮሌጅ ተከታትለው በቋንቋ የትምህርት ክፍል በሀዋሳ ዩኒየን ትምህርት ኮሌጅ መመረቃቸውን ነው የገለፁት፡፡
የመጀመሪያ ድግሪያቸውንም በቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ በርቀት በሊደር ሽፕ የትምህርት ክፍል በ2006 ዓ.ም መመረቃቸውን የተናገሩት መምህር በቀለ ሁልጊዜም ከእውቀት ጋር መሆን ለውጤታማነት መስራት ነው ብዬ አስባለሁ ይላሉ፡፡
የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በገደብ ከተማ ቃለ ህይወት ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ቦታ ተሰጥቶአቸው ሞዴል ተማሪዎችን እንዲያበቁ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ዕድሉን እንዳመቻቸችላቸው ነው ያስረዱን፡፡
ልጆችን በእውቀት እያበቁም ለቤተ-ክርስቲያኒቱ በመስጠት ጥሩ ደረጃ ላይ ማድረሳቸውን ይገልፃሉ፡፡ አሁን ለጡረታም እየተቃረቡ በመሆናቸው የራሳቸውን ነገር ለመስራት ማሰባቸውን ነው የጠቆሙት፡፡ የግል ትምህርት ቤት በመክፈትም ያላቸውን ልምድና እውቀት ተጠቅመውበታል፡፡
እቅዳቸው ተሳክቶላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የግል ትምህርት ቤት መክፈታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
በመንግስት ስራ በአጠቃላይ ለ27 ዓመታት ያህል የሰሩ መሆናቸውን የገለፁት ባለታሪካችን በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ ጡረታ መውጫቸው ቢሆንም አስቀድመው የራሳቸውን የግል ትምህርት ቤት ቁጥር-1 እና ቁጥር-2 በመክፈት ለበርካታ ሰዎች የስራ ዕድልም ፈጥረዋል፡፡
“በርካታ እህቶች እና ወንድሞች ከጡረታ በኋላ እቤታቸው ይቀመጣሉ” ያሉት ባለታሪካችን “እውቀት እያለ እንዴት ቤት መቀመጥ ይኖራል” ሲሉ ሃሳባቸውን የሰጡት።
ዊዝደም ቁጥር-1 ከ0 እስከ 7ተኛ ክፍል እና ቁጥር-2 ከ0 አስከ 2ኛ ክፍል የግል ትምህርት ቤት በ2008 ዓ.ም መክፈታቸውን የተናገሩት ባለታሪካችን በዚህም 1ሺ ተማሪዎች እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ ለ30 መምህራንም የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ነው የገለፁት፡፡
ትምህርት ቤታቸውም በእውቀት የታገዘ በመሆኑ ተማሪዎቻቸው እስከ ዞንም ሄደው ጠንካራ እና ተፎካካሪ ተማሪዎች በመሆናቸው እጅግ እንደሚኮሩባቸው የሚናገሩት ባለታሪካችን ባለድርሻ አካላት ቢያግዙአቸው ከዚህም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።
ሁለቱም ትምህርት ቤቶች ቦታው የራሳቸው ቢሆንም ያለባቸውን የቦታ ጥበት እና የመማሪያ መጽሐፍ ችግሮችን ወረዳው ለመቅረፍ የገባላቸው ቃል እስካሁን እንዳልተፈፀመላቸው ይገልፃሉ፡፡
ባለታሪካችን “መምህር ባይኖር ኖሮ የተማረ ሀይል እና ተተኪም አይኖርም ነበር” በማለት ለሙያው ክብር አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡
አንድ ሰው ስራውን አሸንፋለሁ ብሎ ቀድሞ እራሱን አሳምኖ ከጀመረ ምንም ጥርጥር ሳይኖር ውጤታማ ይሆናል፡፡
ጡረታ የወጡ ሰዎች ስራቸውን በተሻለ መጠንና ጥራት ከቀድሞው በበለጠ እና በተሻለ እሰራለሁ ብለው ቢሰሩ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡
በዚህም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም አርአያ መሆን ይችላሉ ያሉት ባለታሪካችን አርአያነቱ ለሀገርም ትልቅ ስኬት መሆኑን አምነው መስራት አለባቸውም ብለዋል። “ጡረታ መውጣት ማለት ከስራ ውጪ ማለትም አይደለም” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው