ታሪካዊቷ ጊዶሌ

በፈረኦን ደበበ

ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ አቅጣጫ በ525 ኪሎ ሜትር፣ ከአርባ ምንጭ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ከተማዋ ከበስተ ጸሀይ መውጫ በኩል የጫሞ ሀይቅና ነጭ ሳር ሰንሰለታማ ተራሮችን ተንተርሳ ተመሥርታለች፡፡

የቀድሞ ጋርዱላ የአሁኗ ጊዶሌ ከተማ አመሠራረት የሚጀምረው የአጼ ምኒልክ ጦርን ይመሩ የነበሩት ደጃች አመነ እና ደጃች ገነሜ የተባሉ መሪዎች በጋርዱላ ተራራ በ1883 ዓ.ም በሠፈሩ ጊዜ ሲሆን በወቅቱ እስከ ቦረና ያለውን አካባቢም በማዕከላዊነት እንዳገለገለች ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ዳግማዊ አጼ-ምኒልክ ከሶማሊያ እስከ ሱዳን የሚዘልቀውን ደቡባዊ የሀገራችንን ድንበር በወቅቱ የኬኒያ ቅኝ ገዢ ከነበረችው እንግሊዝ ጋር የተካለሉት በጋርዱላ ከተማ እንደሆነና የእንግሊዝ ቆንስላ ጽ/ቤትም እስከ 1929 ዓ.ም የጣሊያን ወረራ ድረስ በጋርዱላ መሆኑንም የካቲት 2011 ዓ.ም ለ8ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የተዘጋጀው ልዩ እትም መጽሄት ያወሳል፡፡

በጊዜው የመንግሥት የአስተዳደር ማዕከል ሆና ስታገለግል የነበረው ጋርዱላ የአርበኞች የስንቅና የመረጃ ምንጭ ነች በሚል በ1929 ዓ.ም የጣሊያን ወራሪ ኃይል የአውሮፕላን ድብደባም ሠለባ ሆናለች፡፡

የታሪክ፣ የተፈጥሮ ገጽ፣ ቅርስና ነፋሻማ አየር ያላት ከተማይቱ በባህላዊ ዕሴቶችና በሀይማኖት መስተጋብርም ትታወቃለች፡፡ በተለይ በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ አማካይነት በ1945 ዓ.ም የተተከለው የደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ተጠቃሽ ሲሆን የ1929 የጣሊያን ወረራ ሰለባ የሆኑ አርበኞች አጽምም በ1968 ዓ.ም በዚሁ ቤተክርስቲያን አርፎበታል፡፡

በ1933 ዓ.ም ጣሊያን ተሸንፎ ከሀገር ሲወጣ ጋርዱላ የአካባቢው የተለያዩ አውራጃዎች ጠቅላይ ግዛት መሆኗን የቀጠለች ሲሆን በደርግም ሆነ ከዚያ ወዲህ የአስተዳደር መዋቅሮች ማዕከል ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

በዞኑ የሚኖሩ ህዝቦች ባላቸው የእርስ በርስ መስተጋብር ብሔረሰቦቹ የራሳቸው የሆነ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጸጉር አሠራር፣ ቤት አሠራር፣ እምነት ፣  የጋብቻ ሥርዓት፣ ጭፈራ፣ ለቅሶ እና ሌሎች ዕሴቶች ቢኖራቸውም ተቻችለውና ተሳስበው አብረው መዝለቃቸውን ነው በመጽሄቱ የተወሳው፡፡

በብሔረሰቦች መካከል ስላለው አንድነት ያነጋገርናቸው የሀገር ሽማግሌዎችም እንደሚያብራሩት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በብዙ መስተጋብሮች የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ያነጋገርናቸው አቶ ብሩ ስማሎ የተባሉ አባት እንደገለጹልን ከሆነ ብሔረሰቦቹ በርካታ የጋራ ዕሴቶች አሏቸው፡፡

ብሔረሰቦቹ ሁሉም በዘጠኙ የጎሳ ቤተሰቦች ውስጥ እንደሚታቀፉና ክትባ በተባሉ ባህላዊ መሪ እንደሚመሩ ጠቅሰው እሳቸውም በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከቦረና መጥተዋል ብለዋል። እሳቸው ሲመጡ ጠፍቶ የነበረው ዝናብ መዝነብ እንደጀመረና ህዝቡም በዚህ መነሻ ተቀብሏቸዋል ብለዋል፡፡

በመካከላቸው የሚነገረው ቋንቋ ተወራራሽ እንደሆነና በአመጋገብ፣ ባህልና በአኗኗር መመሳሰላቸውንም ነው ያስታወቁት፡፡

ከባህላዊና ታሪካዊ መስተጋብር ወጣ ብለን የከተማይቱ አሁናዊ ገጽታ ስንመለከትም ምን ያህል ዕድገት አግኝታ እንደተሻሻለችና ምን ምን እጥረቶች እንዳሉባት መመልከት ችለናል፡፡ ከሌሎች የሀገራችን ከተሞች ጋር ሲነፃፀርም ስኬቶችና ጉድለቶች ይታዩባታል፡፡

የማህበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽነትን ስንመለከት የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ቢኖሩም ከከተማዋ ዕድሜ አንጻር ግን ተመጣጣኝ እንዳልሆኑ መመልከት እንችላለን፡፡ 

የህዝቡን መሠረታዊ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከቀድሞው የተሻለ የከተማ ፕላን ቢኖርም የሚሰጡ አገልግሎቶች ግን በቂ አይደሉም፡፡ ይህንን በምግብ እና በመኝታ አገልግሎቶች በኩል ያለው ውስንነት በማንሳት መመልከት እንችላለን፡፡

ከከተማ ልማት አንጻርም ሲታይ ጠባብ በሆነው የከተማዋ ማዕከል ላይ ያሉ ሱቆች ቁጥርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በውስጣቸው የያዙት ዕቃዎች መጠንም እንዲሁ፡፡ ባንክና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ቢኖሩም አዳዲስ ግንባታዎች በሌሉበት ሁኔታ የከተማ ውበትንም መጠበቅ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ እንግዶችን ለመሳብም አመቺ ሁኔታ አልተፈጠረም ምንም እንኳን በ2022 የከተማዋን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በአስተዳደሩ ዕቅድ ቢያዝም፡፡

ከከተማዋ ማዕከል እየራቅን ወደ መንደሮች በገባን መጠን በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎች የተዋቡ መኖሪያ ሠፈሮች ጥሩ ገጽታ አላቸው፤ መንደርን ከመንደር ጋር የሚያገናኙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችም አሉ ምንም እንኳን ዋና የከተማዋን ማዕከል ጨምሮ የመንገድ መብራቶች ያለመኖር አመሻሽ ላይ ጉዞን አዳጋች ቢያደርግም፡፡

ውኃም ቢሆን እንደዚሁ በእጥረት የሚገለጽ ነው፡፡ ነዋሪዎች ጀሪካን ይዘው ጠዋት ውኃ ወዳለበት ሲዘዋወሩ መመልከትም የተለመደ ነው፡፡ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም ያለውን ችግር ገልጸው አገልግሎቱን በፈረቃ የሚያገኙ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

እነዚህ የአገልግሎትና አቅርቦት ችግሮችን እናንሳ እንጂ ሌሎች የአገልግሎት ችግሮችም እንደሚኖር መገመት ይቻላል፡፡ ሀገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያለው ይህ ችግር የኑሮ ውድነትና የዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ ሲሆን በተለይ ፍላጎቱ ሲያድግ ጉዳቱም አብሮ ይጨምራል፡፡ ችግሩን መከላከልም ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡

ከማህበራዊ መስተጋብሮች ወጣ ብለን ስንመለከት የምናገኘው ከተማዋ ከገጠሩ ማህበረሰብ ጋር የምትፈጥረው መስተጋብር ሲሆን ይህም በንግድና በግብይት ሥርዓቶች ይገለጻል፡፡ ተዳፋታማ የመሬት ገጽታ ወደሚበዛባት ጊዶሌ የአካባቢው ማህበረሰብ በብዛት የሚመጡት በገበያ ቀን ሲሆን ሌላው ደግሞ ሩቅ ወደ ሆነው እርሻ ማሳቸው ጠዋት ሲሄዱና ማታ ማታ ከሥራ ሲመለሱ ነው፡፡

በተለይ ማክሰኞና ሐሙስ ዕለታት በሚውለው ትልቁ ገበያ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ሲገቡ እነዚህም የአካባቢው ታዋቂ ምርት ከሆነው ማሽላ በተጨማሪ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ገብስ እና ሌሎችን ሲያጠቃልል ለውጭ ገበያ የሚውሉ እንደ ሱፍ፣ ማሾ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 እነዚህ ምርቶች “ታታሪ ሠራተኛ” ከሆኑት የዞኑ ህዝቦች ዕለት ተዕለት ህይወት ጋርም የተቆራኙ ሲሆን በተለይ አሁን እየተከናወነ ባለው የምርት ስብሰባ ወቅት በቡድን በቡድን እየሆኑ ከተማዋን ያልፋሉ፡፡ በተለይ ሴቶችና ልጃገረዶች ከወንዶች እኩል ስንቅና ለውኃ ጥም የሚጠጡበትን እቃ ይዘው  ወደ ማሳ የሚሄዱ ሲሆን እርሻቸውን ሲሠሩ ውለው ማታ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

የከተማዋ ሌላው የኑሮ ዘይቤ ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ሥራዎች ሲሆኑ እነዚህም መንግሥት ባመቻቹላቸው ሼዶች እንዲሁም በተመረጡ ቦታዎች በአንድ ላይ ተቀምጠው በሚያከናውኑት ሽያጭ ይፈጸማል፡፡

በእነዚህ ቦታዎች ምግብና ምግብ ነክ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ማገዶ እንጨትና እንዲሁም በአካባቢው እንደጎመን ሆኖ በስፋት ለምግብነት የሚውለው “የሽፈራው ቅጠል“ ተጠቃሽ ሲሆኑ ብዙ ጊዜም ወደ ከተማው የሚቀርቡት በአካባቢው ማህበረሰብ አማካይነት ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከልም አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

ባደረግነው ቅኝትም ጊዶሌ ታሪካዊ ከመሆን ባለፈ ብዙ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አቅሞች እንዳሏት መገንዘብ ችለናል። ዙሪያ ገባዋ በደኖች፣ በከብቶች ሣርና ይህንን መከወን የሚችሉ ሠፊ ወጣት የሰው ኃይል መኖራቸው ያኮራል፡፡

ሆኖም ይህ አቅም ወጥቶ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አመጣ ወይ የሚለው ጥያቄ ከተነሳ መልሱ አይደለም ነው፤ ምክንያቱም ከተማዋ ብዙ የልማትና ሌሎች ክፍተቶች ስለሚታዩባት። ለዚህ ዋነኛው መንስኤ ምን እንደሆነም ያነጋገርናቸው የሀገር ሽማግሌ አቶ ብሩ ስማሎ እንደገለጹት የሠላም እጥረት ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት አካባቢው ግጭት ውስጥ እንደዘለቀ ጠቅሰው መንግሥትም ይህንን ለመከላከል ጠንካራ የጸጥታ አስከባሪ ኃይል አሰማርቷል ብለዋል። ወ/ሮ ፍጹም ስንታየሁና ሌሎች የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ባለሙያዎችም ችግሩን ገልጸዋል በመንግሥት ንብረትና ቅርሶች ላይ ያደረሰውን ጉዳት ሁሉ በመናገር። ድሮ በጣሊያን እንደተገነባ የሚነገርለት ትልቁ ቢሮአቸውም ከዚህ በፊት የያዛቸው ቅርሶችን እንዳጣ ገልጸዋል፡፡