የዋሳ ነገር…

በገነት ደጉ

በዓላት ሲደርሱ ሁሉም ነገር የሚቀመስ አልሆነም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑሮ እርካሽ ተብሎ በሚታሰብባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ለምግብነት የሚውሉ ሸቀጦች ዋጋቸው ሰማይ ነክቷል፡፡ ከእነዚህም አካባቢዎች አንዱ የጌዴኦ ዞን ይጠቀሳል፡፡ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ዋሳ በስፋት በቀዳሚነት ለምግብነት ይውላል፡፡

ዋሳ በጌዴኦፋ ቋንቋ ቆጮ ማለት ነው፡፡ የቆጮ ምርት በዞኑ በብዛት ስለሚመረት ዋጋው ርካሽ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ከተፈላጊነቱ የተነሳ ዋጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀመስ አልሆነም፡፡

ሰሞኑን ወደ ጌዴኦ ዞን ገደብ ከተማ ተጉዘን ነበር፡፡ የጌዴኦ ዞን ከምትታወቅባቸው ምግቦች መካከል  ቆጮ እና ስጋ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡

በሳምንት ማክሰኞ እና አርብ በሚውለው ትልቁ ገበያ ቆጮ ከአሰር እስከ አስራ አምስት የጭነት አይሱዚ መኪና ይወጣል፡፡ ቀድሞ በእስር ይጫን የነበረው ቆጮ ዛሬ በኩንታል ጭምር ተጠቅጥቆ እየተጫነ ስለመሆኑ ተመልክተናል፡፡  

ከገደብ አዲስ አበባ፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፣ ጩኮ እና ዲላ ድረስ ነጋዴው የሚጭነው ቆጮ ገበያ ውስጥ ተከምሮ ላየ መጨረሻው ይህ ነው ለማለት ይቸገራል፡፡ 

በአካባቢው የሚመረተው ቆጮ ብዛቱ ብቻ ሳይሆን ጥራቱ ጭምር ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ታዲያ ከአስራ አንድ ሰዓት በኋላ ያ የቆጮ ገበያ ለዓይን የለም፡፡

በአካባቢው ስላለው የቆጮ ገበያ ይህን ያህል ካልኳችሁ አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታ ደግሞ  ላስቃኛችሁ፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት የቆጮ ዋጋ በተለይም በዓልን ምክንያት በማድረግ ይሁን በሌላ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ብዙሀኑ በልቶ የማደሩ ጉዳይ ላይ ትልቅ ፈተና ደቅኗል፡፡

አካባቢው በእንሰትና ቆጮ ሀብት ይታወቃል ያሉን አስተያየት ሰጪያችን በተለይም በጌዴኦ ዞን ካሉት ወረዳዎች ገደብ ወረዳ በቆጮ ምርቷ እንደምትታወቅ ነው የነገሩን፡፡

የአካባቢው ህብረተሰብ ቆጮን ለምግብነት ገዝቶ አይበላም፡፡ ለአንዳንድ ጉዳዮች ከቤቱ አውጥቶ ይሸጣል እንጂ። አስተያየት የሰጡንን ጨምሮ በጌዴኦ አካባቢ የሚገኙ እናቶችም በቆጮ ንግድ ስራ እንደሚተዳደሩ ነው የገለፁት፡፡

“ልጆቻችንን የምናሳድገው እና ቤታችንን የምናስተዳድረው በቆጮ ንግድ ነው። ከልጅነታችን ጀምሮ ነው የቆጮ ንግድ የጀመርነው፤ ዛሬ ግን ነግደንም ይሁን በልተን የማደራችን ሁኔታ አደጋ ላይ ወድቋል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየታቸውን የሰጡን እናት ደግሞ ከአስር ዓመታት በላይ ቆጮ ነግጃለሁ ይሉናል፡፡  የዋጋው ጣሪያ መንካት ግን እንደ ዘንድሮው ሆኖ አያውቅም ሲሉ ንግግራቸውን ይጀምራሉ፡፡

“ቀደም ሲል በአንድ እና ሁለት ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው ቆጮ ዛሬ ከ10ሺ ብር በላይ በመድረሱ ነግዶ እራስን ማስተዳደር ከባድ ሆኗል በማለት ነው በምሬት የተናገሩት፡፡

በተለይም በበዓላት ወቅት ደግሞ የሚንረው ዋጋ እንዲህ ነው ተብሎ የሚነገር አይደለም ያሉት ወ/ሮዋ ለሚመለከተው አካል ከተናገርን ውለን አድረናል ይላሉ፡፡ ነገር ግን የሚሰማን እና ዋጋውን ለማረጋጋት የሚደረጉ ጥረቶች እምብዛም ሚዛን የሚደፋ እንዳልሆነ ነው የገለፁት፡፡

እኛም አንድ ጭነት ቆጮ እስከ 6 ሺህ ብር ሲሸጥ ተመልክተናል፡፡ ምናልባት አርሶ አደሩ እንሰት መትከል አቁሞ ወይም የተጠቃሚው ቁጥር ጨምሮ ይሆን በማለት የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረን ነበር፡፡

አቶ ታሪኩ ሮቤ የገደብ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በጌዴኦ እና ጉጂ ዞን በነበረው ግጭት ምክንያት ከገጠመው መፈናቀል ጀምሮ በቆጮ ገበያ ላይ የዋጋ ንረቱ እንዳለ ነው የገለፁት፡፡

የእንሰት ተክል በባህሪው ለመድረስ በትንሹ አምስት ዓመታት ይፈጃል፡፡ አርሶ አደሩም ተፈናቅሎ ወደ ቀዬው ከተመለሰ ወዲህ ከነበረው የስነ ልቦና ጉዳት አገግሞ ሙሉ ለሙሉ ማምረት ውስጥ የገባው ጥቂት ጊዜ ቢሆንም እንኳን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቆጮ ዋጋ መረጋጋት እንዳልቻለ ነው የጠቆሙት፡፡

ሌላውም የጤፍ እና የሌሎች ዋጋ መናርም በቆጮ ዋጋው መናር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተናገሩት ከንቲባው፡፡ በአማራጭም በልቶ እና ጠግቦ ለማደር የተሻለ ነው ብሎ ህብረተሰቡ የሚጠቀመው ቆጮ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እንዳይረጋጋ ማድረጉንም ነው የገለፁት፡፡

በወረዳው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ህብረተሰቡ ተረጋግቶ አለመስራት እና እንደ አያት ቅድመ አያቶች ወቅቱን ጠብቆ እንሰትን ከመትከል አንፃር መዘናጋቶችም እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡

በህብረተሰቡ ዘንድ ከጤፍ ይልቅ ከስጋ ጋር ቆጮ ተመራጭ ምግብ ነው፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌላ አካባቢዎች በስፋት ስለሚጫን ከጊዜ ወደ ጊዜ የቆጮ ዋጋው እየናረ መምጣቱ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡

የገደብ ከተማ አስተዳደር ንግድ ገበያ ልማት እና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተገኝ ተሰማ በበኩላቸው አሁን ላይ እየታየ ያለው የቆጮ ዋጋ መናር ከዓለም ዓቀፍ የሸቀጦች ምርት ዋጋ ጋር ተያይዞ የሚታይ ችግር እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡  

እንደ ሀገር፣ ክልልና ዞንም የዋጋ ጭማሪ መኖሩን የተናገሩት አቶ ተገኝ በተለይም የፋብሪካ ምርቶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋን ለማረጋጋት እንደ ገደብ ከተማ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ወደ ህጋዊ ስርዓት ለማስገባት ስራዎች መሰራታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

በተለይም ህብረተሰቡን ከሚጎዱት ሸቀጦች ወቅታቸው ያለፈባቸውን ምርቶች የማስወገድ ስራዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ መሰራታቸውን የሚናገሩት ኃላፊው እንደ ከተማ አስተዳደር ከሌሎች ከተሞች ጋር ስናነፃጽር ዛሬም የተሻለ መረጋጋት እንዳለ ነው የገለፁት፡፡

እንደ ጽህፈት ቤት በየጊዜው ግብረሀይል አቋቁመው እየሰሩ መሆናቸውን የሚናገሩት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊው በዚያን ልክ ግን ዋጋ ተረጋግቷል የሚል ነገር በድፍረት ለመናገር ከባድ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

በአግባቡ የሚሰሩ ነጋዴዎች ስለመኖራቸው የሚናገሩት አቶ ተገኝ አልፎ አልፎም እራስ ወዳድ እና ለህብረተሰቡ የማያስቡ ነጋዴዎችም መኖራቸውን ነው የገለፁልን፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በአቋራጭ ለመክበር ህብረተሰቡ ላይ ዋጋ ጨምሯል በሚል ያልተገባ ጭማሪ የሚጨምሩ ነጋዴዎችም ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራዎች መስራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በተለይም በበዓላት ወቅት በወፍጮ ቤቶች ላይ የዋጋ ዝርዝር አውጥተው እንዲለጥፉ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ተገኝ ለባለድርሻ አካላትም ከሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ጋር ተያይዞ በየጊዜው ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የቆጮ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ኃላፊው ከቆጮው ጥራት ጋር ተያይዞ ከገደብ እስከ አርባምንጭ እና አዲስ አበባን ጨምሮ ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መጫኑ ለዋጋው መናር አስተዋፅኦ አድርጓል ባይ ናቸው፡፡ 

በአካባቢያችን ላይ ትልቁ ምርት ቆጮ እና ቡና ነው ያሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ እንደ ቀድሞው እንሰት የመትከል ልምዱን እየረሳ የመጣበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ተገኝ ማንኛውም አርሶ አደር 100 እና ከዚያ በላይ እንሰት በየዓመቱ እንዲተክሉ እንደ ግዳጅ የተጣለ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ከአመራር ጀምሮ እንሰት እንዲተክል መደረጉን ጠቁመው የአካባቢው ህብረተሰብ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ  እንሰት እያነሱ በቦታው ቡናን እየተከሉ መሆናቸው የቆጮ ዋጋው እንዲንር አድርጓል ብለዋል፡፡

ሌላኛው ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመመጣጠን ትልቁ ፈተና ሲሆን ለቆጮው ዋጋ መናር አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ተናግረዋል፡፡

ዋጋን ለማረጋጋት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎችንና አትክልትን እንዲጠቀም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ስራዎች የተሰሩ መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡

በተለይም ለቀጣይ ከምግብ ዋስትና ጋር በጋራ በመሆን በአካባቢያችን በቀላሉ ልናገኛቸው በምንችላቸው ምርቶች በስፋት ለማምረት በአካባቢያችን የሚገኙትን የመንግስት ተቋማትን በመጠቀም ሰፋፊ እርሻዎችን ለወጣቶች በማህበር በማደራጀት የተጀማመሩ ስራዎችን በማጠናከር ገበያ ለማረጋጋት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው  እንደሚቀጥሉም ነው የጠቆሙት፡፡