ጥምቀትን በሀዋሳ ጀልባዎች

ጥምቀትን በሀዋሳ ጀልባዎች

በአንዱዓለም ሰለሞን

ጥምቀት የአደባባይ በዓል ነው፡፡ በዓሉ የሀይማኖት ስርዓት የሚከወንበት ከመሆኑ በሻገር ባህላዊ ገጽታን የተላበሰ መሆኑ የተለየ ድባብ እንዲኖረውና ልዩ ስሜት እንዲፈጥር ያደርገዋል፡፡ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንዲሉ፣ ቆነጃጅቱ በተለያዩ አልባሳት ደምቀው፣ በተለይም ደግሞ በባህላዊ ቀሚሶቻቸው ተውበው ይታያሉ፡፡

በዕለቱ ከመንፈሳዊ ዝማሬዎች ባሻገር የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎች በየቦታው ይቀልጣሉ፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ በዓሉ ለየት ያለ ገጽታን የሚላበስበት አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ወንዱ በሆታ፣ ሴቷ በእልልታ ታቦታቱን አጅበው የሚያደርጉት ጉዞ አስደሳች ትዕይንት የሚስተዋልበት ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ጥምቀት ወጣቶች የሚተጫጩበት እንደመሆኑ በብዙዎች ዘንድ የተለየ ትውስታ ማኖሩ አልያም በገጠመኝ መታጀቡ አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ አሁን አሁን እየቀረ የመጣው የሎሚ ውርወራ ጉዳይም አብሮ የሚታወስና ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የሚነገር ታሪክ ያለው ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ናቸው እንግዲህ የጥምቀትን በዓል ከሌሎቹ በዓላት በተለየ መልኩ እንዲታይ የሚያደርጉት፡፡

ሌላው የጥምቀትን በዓል የተለየ የሚያደርገው ነገር ከውሀ ጋር ቁርኝት ያለው መሆኑ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የከተራ ዕለት ታቦታቱ ከየደብራቸው ወጥተው የሚያድሩበት ቦታ (ጥምቀተ ባህር) በወንዝ አቅራቢያ የሚገኝ ነው፡፡ በእንደነዚህ ያሉ ቦታዎች የሚከናወነው ሀይማኖታዊ ክዋኔ እጅግ አስደሳች ነው፡፡ የዛን ዕለት ወንዙ እንደ ተባረከ፣ ውሀውም እንደ ጸበል ነው የሚታሰበው፡፡

ይህ ነገር ከወንዝ ዳር ባሻገር፣ በሀይቅ ላይ ቢሆን ብላችሁ ደግሞ አስቡት፡፡ በእርግጥም በዚህ መልኩ የሚከናወነው ሀይማኖታዊ ክዋኔና ታቦትን አጅቦ የሚደረገው ጉዞ እንዴት አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም፡፡ ከዚህ አንጻር በዝዋይ ሀይቅ ላይ የሚደረገውን የጥምቀት በዓል አከባበር ተጠቃሽ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ይህን መሰል ክስተት አስተናግዳ ነበር፡፡ የከተራ ዕለት የሀይማኖቱ ተከታዮች ከሎቄ ደብረ መድሀኒት መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ታቦቱን አጅበው፣ በሀዋሳ ሀይቅ ላይ በጀልባ ወደ ጥምቀተ ባህር ተጉዘዋል፡፡

ምዕመናኑ የተጓዙት በግምት ከ8 እስከ 10 ኪሎ ሜትሮችን ሲሆን በሀይቁ ላይም የአንድ ሰዓት ቆይታ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች ከተለቀቁና ካየኋቸው ቪዲዮዎች እንደተመለከትኩት የነበረው ድባብና ትዕይንት አስደሳች ነበር፡፡

ይህ የዛሬ ዓመቱ በሀዋሳ ሀይቅ ላይ የተከናወነው የጥምቀት በዓል ልዩ ገጽታ እነሆ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከወን ይሆናል። ለዚህ ደግሞ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ እኔም ወደ ፍቅር ሀይቅ ተጉዤ፣ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ምን የተለየ ነገር አለ በሚል ባለፈው ዓመት ታቦቱን አጅበው ከተጓዙ የተወሰኑ የጀልባ ዘዋሪዎች ጋር ጥቂት ቆይታ አድርጌያለሁ፡፡

ስሙን መላኩ ጋምቡራ በማለት ያስተዋወቀኝ የጀልባ አሽከርካሪ በሀይቁ ላይ ለረጅም ጊዜ በስራ መቆየቱን ገልጾልኛል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በሀዋሳ ሀይቅ ሁለገብ የህብረት ሥራ ማህበር አባል ነው፡፡ ከስራው ጋር በተያያዘ የተለያዩ ገጠመኞች ያሉት ቢሆንም የአምናው የታቦት ሽኝት ግን የተለየ ስሜት የፈጠረበት ክስተት እንደነበር ይገልጻል፡-

“ጉዟችን ደስ የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ ተሰምቶኝ የነበረውን ስሜት በቃላት ለመግለጽ ይከብደኛል፡፡ ብቻ ግን እንደ አንድ የሀይማኖቱ ተከታይ በሁኔታው በጣም ነበር የተደሰትኩት፡፡ የሲዳማ አባቶችን ጨምሮ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ታቦቱን አጅቦ ደስ በሚል ሁኔታ ነበር የመጣው፡፡ እዚህ (ጥምቀተ ባህር) ስንደርስ ሲጠብቀን የነበረው ህዝብ ያደረገልን አቀባበል ደግሞ የተለየ ነበር፡፡ የዘንድሮውን በጉጉት እንድጠብቀው ያደረገኝ ልዩ ትዕይንት የታየበት አስደሳች ጉዞ ነበር፡፡”

ግዛቸው ጥላሁን ደግሞ ከፍቅር ሀይቅ ማህበር በጀልባ ታቦቱን አጅበው ከተጓዙት የጀልባ አሽከርካሪዎች አንዱ ነበር፡፡ እሱም ጉዞው የተለየ ስሜት እንደፈጠረበትና በእጅጉ መደሰቱን ነግሮኛል፤ እንዲህ በማለት፡-

“ፈጽሞ የማይረሳና ደስ የሚል ትዕይንት ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ዝዋይና ባህር ዳር ላይ ነበር ይህን የምናየው፤ ያውም በቴሌቪዥን፡፡ በሀዋሳ ሀይቅ ላይ ይህ መሆኑና እኔም በዚህ ጉዞ ላይ በመሳተፌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በማየው ነገር እየተደነቅሁ ፎቶ ሳነሳና ቪዲዮ ስቀርጽ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ከአምናው የተሻለ አስደሳች ጉዞ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። ለዚህም እንደ አምናው ሁሉ የማስተባበሩን ሥራ እየሰራን ነው፡፡”

የማህበራቱ አባለት በዕለቱ የጀልባ አገልግሎት የሚሰጡት ያለክፍያ እንደሆነ ገልጸውልኛል፡፡ አንሙት ፈይሳ ተጓዦቹ ታቦቱን አጅበው ሲመጡ ከተቀበሏቸው የማህበሩ አባላት አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ እና በነጻ ስለሰጡት አገልግሎት የተሰማውን እንዲህ በማለት ይገልጻል፡-

“ታቦት የሚያጅቡ ሾፌሮችን ልከን ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር እዚህ እየጠበቅን ነበር፡፡ የህዝቡ አቀባበልና ድባቡ የሚገርም ነበር፡፡ እኛም እንዲህ ሰው ለተደሰተበት ነገርና ለቤተ ክርስቲያን የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማድረጋችን ደስተኞች ነን፡፡”

ሳሙኤል ጥላሁን ደግሞ የካላሞ ማህበርን ከወከሉት ባለጀልባዎች መካከል አንዱ ነበር። እሱም እንደሌሎቹ አስተያየት ሰጪዎች ሁሉ ጉዞው አስደሳች እንደነበር ይገልጻል። “በተለይ እኔ ዕድለኛ ነበርኩ” ያለበትን ምክንያት ጨምሮ ስሜቱንና ትውስታውን እንዲህ በማለት አጫውቶኛል፡-

“ከዚህ ቀደም በሌላ አካባቢ የሚደረገውን በቴሌቪዥን ከማየት ባለፈ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የታቦት ሽኝት ላይ ተሳትፌ አላውቅም ነበር፡፡ ይህ ነገር በሀዋሳ በመሆኑና እድሉን በማግኘቴ ደስ ብሎኛል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ታቦቱ የነበረው እኔ በምነዳው ጀልባ ላይ ነበር። ይህ በራሱ የፈጠረብኝ የተለየ ስሜት አለ፡፡ ዕድለኛ ነበርኩ፡፡ የምዕመኑ ሁኔታ፣ ጉዞው በአጠቃላይ በጣም አስደሳችና የማይረሳ ትዝታን ጥሎ ያለፈ ነበር፡፡”

ወጣት ሳሙኤል እንደገለጸልኝ ባለፈው ዓመት እሱ ይሾፍረው የነበረውና ታቦቱን የያዘው ጀልባ 30 ሰዎችን የመጫን አቅም ያለው ነበር፡፡ ዘንድሮ እሱ የሚቀዝፈውና ታቦቱን የሚይዘው ጀልባ ደግሞ 80 ሰዎችን ለመያዝ የሚችልና በተሻለ ዲዛይን የተሰራ ነው፡፡

ከበዓሉ ጋር በተያያዘ የተለየ ገጠመኝ ይኖርህ ይሆን? ስል ወጣቱን መጠየቄ አልቀረም፡፡ እሱም እየሳቀ ገጠመኙን እንዲህ በማለት አወጋኝ፡-

“ታቦቱን የያዘውን ጀልባ የያዝኩት እኔ በመሆኔ ራሴን እንደ ዕድለኛ ነበር የቆጠርኩት። በእርግጥም በዚህ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ከበዓሉ ፍጸሜ በኋላ ግን ያልጠበኩት ነገር አጋጠመኝ። የጀልባ ተጠቃሚዎች ታቦቱ የነበረበት ጀልባ ላይ አንሳፈርም በማለታቸው (ለታቦቱ ክብር) ቢያንስ ለሳምንት ያህል ችግር አጋጥሞኝ ነበር፡፡”

ወጣቱ ዘንድሮም እንደ አምናው ታቦቱን የሚይዘውን ጀልባ ለመዘወርና አስደሳቹን መንፈሳዊ ጉዞ በሀዋሳ ሀይቅ ላይ ለማድረግ ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ አምና 12 ጀልባዎች ነበር በጉዞው የተሳተፉት፡፡ ዘንድሮ 3 ትልልቅ እና 27 አነስተኛ ጀልባዎች ታቦቱን አጅበው ለመጓዝ ተዘጋጅተዋል፡፡

ይህም በሀዋሳ ከተማ ለሚከበረው የዘንድሮው በዓለ ጥምቀት ተጨማሪ ድምቀት የሚሰጥ ልዩ ክስተት ይሆናል፡፡