ልናለማና ልንጠብቃቸው ይገባል

ልናለማና ልንጠብቃቸው ይገባል!!

በአለምሸት ግርማ

ጥምቀት በሀገራችን ትልቅ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው በዓል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዩሐንስ የተጠመቀበትን ዕለት ለማሰብ የሚከበር ሲሆን በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል።

ከባህላዊ ይዘቱ ጋርም ሲታይ ሰዎች በባህላዊ ልብስ ደምቀው ይታያሉ። ከዋዜማው ጀምሮ ህፃናት፣ አዋቂዎች ሁሉም በሀበሻ ልብስ ደምቀው በዓሉን ለማክበር ሽርጉድ ይላሉ። ለዚህም ነው ”ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ“ የሚባለው።

ዕለቱንም እንዲሁ በባህል ልብሳቸው ተውበው ያከናውናሉ። ከዋናው ይዘት ባሻገር ባህላዊ ትዕይንቱ የሰዎችን ቀልብ የሚገዛ ነው። ለዚህም ነው ከሀገራዊነት አልፎ የአለም ቅርስ ለመሆን የበቃው።

በአለም ቅርስነት ከመመዝገቡ በፊት ከተለያዩ የአለም ሀገራት ጎብኚዎች በዓሉን ለመታደም ወደ ሀገራችን ይመጡ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በዚህም መሰረት እንደቱሪዝም መስህብነት የሚታይ በዓል ነው።

የቱሪዝም ዘርፍ ለአንድ ሀገር ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ከቱሪዝም የሚገኝ ገቢ በሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ልክና በዚያ አገር በሚኖራቸው የጊዜ ቆይታ ይወሰናል።

ጎብኚዎች ወደ አንድ አገር  እንዲጓዙና በዚያ እንዲቆዩ ለማድረግ ሳቢና ማራኪ የሆኑ መስህቦች ሊኖሩ ይገባል። መስህብ በተፈጥሮ የሰዎችን ቀልብ የሚማርክ  ሲሆን የተፈጥሮ ሃብት /ደንና የእጽዋት/ የእንስሳት ዝርያዎች፤ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ባህል፣ ወግ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።

ጎብኚዎችን ለመሳብና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማርዘም ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችንና የመዝናኛ ተቋማትን ማሰናዳት ሌላው መስፈርት ነው። የህክምና አገልግሎት ተቋማትን፣ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ፣ የመጓጓዣና የመገናኛ መሰረተ ልማቶችም  አስፈላጊ ናቸው። ሀገራችን ከዚህ አንፃር ብዙ የውጭ ዜጎችና፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ስታስተናግድ ቆይታለች። በዚህ አመት የጥምቀት በዓልም ብዙዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባሻገር ሀገራችን የተፈጥሯዊና የታሪካዊ ቅርስ ባለቤት ናት።  ከነዚህም ጥቂት የማይባሉት በተባባሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግበዋል። የጥምቀት በዓልም በአለም ቅርስነት መዝገብ ከሰፈሩት መካከል ተጠቃሽ ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ አገር ነች። የኤርታሌ የእሳተ ገሞራ ሀይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃታማ ስፍራ ዳሎልም ከቱሪስት መስህቦቻችን ተጠቃሾች ናቸው። በተጨማሪም ለመዝናናት አመቺ የሆኑ በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች፣ እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና መኖሪያዎች ይገኛሉ።

በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና የአርኪዎሎጂ ሥፍራዎች እንዲሁም ሃይማኖትን እና ባህልን መሰረት ያደረጉ የማይዳሰሱ እያሌ ሃብቶች ባለቤት ናት። መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት መስጠቱ ይህን እምቅ ሀብት መጠቀም እንዲቻል ያደርጋል። ይህም ኢኮኖሚውን ወደፊት ለማራመድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

የመስህብ ሃብቶችን የማስተዋወቅ፣ ገበያ የማፈላለግ፣ የማልማትና የመጠበቅ ተግባር ከማከናወን ባሻገር የአገር ውስጥ ቱሪዝምን የማበረታታትና ንቅናቄ የመፍጠር ድርሻውንም መወጣት አለበት። በተለይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማበረታታት ዘርፉን ማነቃቃት ያስፈልጋል። የሀገራችን አንዱ እሴት የሆነውን የጥምቀት በዓልም ከባህላዊ ይዘቱ ጋር አጣምሮ በማክበር ለአለም እንዲታወቅ ተደርጓል። በዚህ ሊበረታታ የሚገባው ተግባርም ተከናውኗል።

ሃገራችን እምቅ የቱሪዝም አቅም እያላት ከዚህ ዘርፍ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኘ ብትቆይም በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ጥሩ መነቃቃት ይታያል። ጥምቀትን ጨምሮ በአለም የቅርስ መዝገብ የሰፈሩ ቅርሶች ቁጥር መጨመር ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታል።

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ የተጀመረው መነቃቃትና ተስፋ ተጠናክሮ መቀጠል እንዲችል በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ትልቅ ነው። ያሉንን በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና የአርኪዎሎጂ መስህብ ሃብቶችን እንዲሁም ሃይማኖትን እና ባህልን መሰረት ያደረጉ የማይዳሰሱ አያሌ ሃብቶችን ልናለማና ልንጠቀምባቸው ይገባል!