ከ2010 ዓ.ም አንስቶ በቡና ዘርፍ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ታስቦ የተደራጀ ማህበር ነው – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር፡፡
በወቅቱ ከአምራች አርሶ አደሮች ውጪ በሰንሰለቱ ላይ የሚሳተፉ አካላት ከአምስት ሺህ በላይ በመሆናቸው አንድ እንዲሆኑ ከጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተቀመጠው አቅጣጫ መነሻ ባለፉት አራት ዓመታት ወጥ ለማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ነው የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሁሴን አንቦ የተናገሩት፡፡
የነበረው ክፍተት ጠቦ አሁን ላይ በመላው ሀገሪቱ ቡና ያለበትን አካባቢ በመወከል ሰባት ማህበራት በጋራ ተደራጅተው የመሰረቱት ማህበር ሲሆን ዓላማው ከምርቱ ጀምሮ ያሉ የቡና ችግሮች ገበያው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ለመፍታት ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር የሁለትዮሽ የምክክር ፎረም ላይ ተገኝተው ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ፍስሃገነት ቅርንጫፍ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ቡናን ማምረት የራሱ ሳይንስ አለው ያሉት ዶ/ር ሁሴን፣ በዓመት አንድ ጊዜ የሚመረተው ቡናችን ከአርሶ አደሩ እጅ በዝቅተኛ ዋጋ ሲወጣ በኑሮው ላይ ጫና የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
የቡና ግብይቱ ምርትን፣ የዓለም ተጠቃሚ ዋጋን ያገናዘበ፣ በእውቀት የሚመራ መሆን አለበት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የቡና መገኛ የሆነችውን አገራችንን ኢትዮጵያን ማስተዋወቁ ባለቤት እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከአደረጃጀት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም ማህበሩ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ስለመሆኑ ያነሱት ዶክተር ሁሴን፣ ይህም በዕውቀት የሚመራ፣ ወጥ የሆነ ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ያለውን የቡናን ችግር ለመፍታት ገበሬው፣ ማህበሩ፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና መንግስት ችግሮችን በምርምር፣ ሳይንሳዊ መፍትሄን በማስቀመጥ መተግበር ይጠይቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ገበሬው ግንባር ቀደም ሆኖ ምርምሩን በማሳው ላይ እንዲቀበል እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
እንደ ማህበሩ ፕሬዝዳንት ገለፃ፣ ባለፉት ዓመታት የጥራት ደረጃን ከፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ቡና ተወዳዳሪ ሆኖ ገዢ ሀገራትም ተገዝቶ በማይታወቅ ዋጋ የገዙበትና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪም የተገኘበት ነው፡፡
አሁን ላይ የዓለም የቡና ዋጋ መፈራረቆች የሚታዩበት ነው፤ በአካባቢያዊ ገበያ እርስ በርስ ከመወዳደር በዕውቀት ላይ የተመሠረተና የዓለምን ገበያ ባገናዘበ መልኩ መገበያየት ያስፈልጋል፤ ባለፈው ምርት ወቅት ይህን ባለመከተላችን የዓለምን የቡና ዋጋ መቋቋም አልቻልንም ብለዋል።
በዚህም ቡናችን ከእጃችን ሳይወጣ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ተሽጦ ገንዘብ ባለመቅረቡ በዘንድሮ ግዥ ላይ ተጽዕኖ ማምጣቱን አመልክተዋል፡፡
ገበሬው የቡና ዋጋ ቀነሰ ብሎ መደናገጥ የለበትም፤ አሁንም በዓለም ላይ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና በትክክል ከተዘጋጀ ዋጋው ትልቅ ነው ብለዋል፡፡
ስለዚህ ገበሬው ስፔሻሊቲ ቡናን በትኩረት በማዘጋጀት በጥሩ ዋጋ መሽጥን ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲያስብ ጠይቀዋል፡፡
ከምርት አንስቶ እስከ ግብይት፣ ከገበሬ አንስቶ እስከ ተጠቃሚ ባለው ሂደት ቡናችንን በምርምርና በዕውቀት መምራት አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከፍስሃገነት ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ